Tuesday, November 6, 2012

ምሥጢረ ተዋሕዶ

 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን


ምስጢረ ተዋሕዶ (ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው?)

ተዋሕዶ ማለት የቃል በቃል ትርጉሙ ተዋሀደ አንድ ሆነ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ተዋሕዶ ሲል አንድ መሆን ማለት ነው። ምስጢራዊ ፍቹ ግን ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው።


- ሁለት አካላት የተባሉተ አካል መለኮትና አካለ ሥጋ ናቸው።

- ሁለቱ ባህርይ የተባሉትም ባሕርየ መለኮትና ባሕርየ ሥጋ ናቸው።

እንደሚታወቀው ሁለቱ አካላትም ሆነ ሁለቱ ባሕርያት ፈጽመው የማይገናኙ የማይመሳሰሉ ናቸው። ይኸውም አንደኛው ፈጣሪ ሌላው ፍጡር ከመሆናቸውም ባሻገር የመለኮት አካል የማይጨበጥ፣ የማይዳደስ፣
ቂቅ ሲሆን የሥጋ አካል ደግሞ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ግዙፍ ነው። እንግዲያውስ ከሁለቱ አካል አንድ አካል ሆነ ሲባል ረቂቁ መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፤ ግዙፉ ሥጋም ግዙፍነቱን ሳይለቅ: ይህ ማለት ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ሳያረቅቀው፣ ግዙፉ ሥጋም ረቂቁን መለኮት ሳያገዝፈው በተዓቅቦ አንድ ሆኑ ማለት ነው።

የመለኮት ባሕርይ: የማይሞት፥ የማይታተም፥ የማይደክም፥ የማይለወጥ ሲሆን የሥጋ ባሕርይ
ደግሞ መዋቲ ታማሚ፣ የሚደክምና የሚለወጥ ነው። ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት እንግዲህ መለኮት የራሱ ባሕርይ ያልሆነው የሥጋ ባሕርይ ሕማም ሞት ድካም ገንዘብ አድርጎ፣ ሥጋም የራሱ ባሕርይ ያልሆነው የመለኮትን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ሁለቱም ተዋሃዱ አንድ ሆኑ ማለት ነው። ተዋሕዶ መንታነትን አጥፍቷልና ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት ብሎ ነገር የለም። /ዮሐ 20፥26/

በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለትስብእት፣ የትስእትም ገንዘብ ለመለኮት ሆኗል።

ይህም ቀደም ሲል እንደተገለጠው መለኮት ትስብእትን /ሥጋን/ በመዋሀዱ ምሉእ ውሱን፣ ሰጪው ተቀባይ፣ የማያንቀላፋው የሚተኛ፣ ኃያሉ ደካማ፣ ሕያው መዋቲ ሆኗል።

በግርግም አስተኛችው (ሉቃ 2፥7)

እርሱም ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር (ማር 4፥38)

ይችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበለሁ (ዮሐ 10፥18)

ውኃ አጠጩኝ (ዮሐ 4፦........)

ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለወጎች ትሁኑ ዘንድ ስለእናንተ ድሀ ሆነ:: (2ቆሮ 8፥9)

ኢየሱስም መንገድ ከመሔድ ደክሞ....... (ዮሐ 4፥6-8)

ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ መቼም ነበርሁ እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ ---- /ራእ 1፥17/

ትስብእትም መለኮትን በመወሃዱ ውሱን ምሉእ፣ ተቀባዩ ሰጪ፣ ደካማው ኃያል፣ መዋቲው ሕያው ተባለ

ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸውም አልፎ ሔደ:: /ዮሐ 8፥59/

ሰላሜን እስጣችኃለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም:: /ዮሐ 14፥27/

በስሜ የምትለምኑትም ሁሉ አደርገዋለሁ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አድርገዋለሁ:: /ዮሐ 14፥13፣14/

በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ:: /ጴጥ 3፥18/

ይህ ሁሉ የተመለከትነው በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረና ስለ እርሱ የተነገረውን ነው:: ታዲያ ከጥቅሶቹ የምንመለከተው አንድነትን እንጂ ሁለትነትን አይደለም። በመለኮት የሥጋን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ ሲባል ባሕርዩ ተለውጦ ትስብእቱ /ሰው/ የሆነ፤ ትስብእትም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ ሲባል ባሕርዩን ለቅቆ መለኮት የሆነ አይደለም። ተዋሕደው በተዓቅቦ /በመጠባበቅ/ የሆነ ነው እንጂ በተዋሕዶ ሁለትነትም ሆነ መለወጥ የለም። ምክንያቱም ውላጤ /መለወጥ/ በእግዚአብሔር አይስማማምና ነው።

እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም:: (ሚል 3፥6)

ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ፣ እስከ ዘለዓለምም ያው ነው:: (ዕብ 13፥18) እንዲል።

ክርስቶስን ከሁለት መክፈል እንደማይቻልና በተሕዶ ውስጥ ምንታዊ /መንታነት/ እንደሌለ ቅ/ጳውሎስ

''ክርስቶስ ተከፍሏልን?" (1ኛ ቆሮ 1፥13)

''አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው::" (1ኛ ቆሮ 12፥5) በማለት ያስረዳል። አሁንም ቢሆን የሚከተሉትን በጽሞና እንመልከታቸው። ነገረ ተዋሕዶንም ያስተምሩናል።

ያንቀላፋው ከእንቅልፉም ተነስቶ ማዕበሉንና ነፋሱን የገሠፀው አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ 8፥23-27/

ወደ ሠርግ ቤት የተጠራው፣ በዝያ ተገኝቶ ውኃውን ወደወይን ጠጅ የለወጠው አንዱ ሥግው ቃል ነው:: /ዮሐ 2፥1-11/

ምራቁን ወደ መሬት የተፋው: ምራቁንም በጭቃ ለውሶ ለዓይነ ሥውሩ ዓይን የፈጠረለትም እርሱ አንዱ ክርስቶስ ነው:: /ዮሐ 9፥1-10/

የተጠማውና የማያስጠማ የሕይወትን ውኃ የሚሠጠው አንዱ ኢየሱስ-ክርስቶስ ነው:: /ዮሐ 4፥6-15፣ ራእ 21፣6-7/

40 ቀንና 40 ሌሊት ከመጸሙ የተነሳ የተራበው ጥቂቱን ዓሣና እንጀራ ያበረከተውም አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ 4፥1-3፣ 14፣ 13-21/

መለኮትና ትስብእት ከጽንሰት ጀምሮ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነዋል። ለትምህርት ሲባል መለኮት፥ ትስብእት እያልን እንጠራለን እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ መለኮት፥ ትስብእት እያሉ መለያየት የለም።

የተዋሕዶ ተቃራኒዎች: ቢዚህ ዓለም ተቃራኒ የሌለው አንድም ነገር የለም። ስለሆነም ለተዋሕዶም ሰባት ተቃራኒ ነገሮች አሉት። እነሱም የሚከተሉት ናቸው።

1. ውላጤ፦ ውላጤ ማለት መለወጥ ማለት ነው። አንዳንዶች ቃል ተለውጦ ሥጋ ሆነ ይላሉ። ይህም ማለት

የሎጥ ሚስት ወደጨው ሓውልትነት (ዘፍ 19፦ ......)

የቃና ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት እንደተለወጠ /ዮሐ 2፥5/ ማለት ነው ብለው ያምናሉ።

ነገር ግን መለኮት ሥጋን በለበሰ ጊዜ ሥጋ ወደ መሆን አልተለወጠም በፍፁም ተዋሕዶ ፀና እንጂ። እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ጌታ ራሱ፦

- እኔና አብ አንድ ነን:: (ዮሐ 10፥30)

- እኔን ያየ አብን አይቷል ባለለም ነበር ዮሐ 14፥19

2. ኅድረት:- ኀድረት ማለት ''ማደር'' ማለት ነው። ይህም መለኮት በሥጋ ውስጥ አደረ የሚሉ መናፍቃን የሚከተሉት እምነት ነው። የሚያቀርቡት ማስረጃም፦

- ውኃ በማድረግ - ዳዊት በማኅደር - ሰይፍ በሰገባ እንደሚያድር መለኮት በሥጋ አድሮ ወጣ ይላሉ።

ለመለኮት ግን እንዲህ አይደለም ተዋሕደው አንደ ነፍስና ሥጋ ነው እንጂ። ስለዚህም፦

- (ማቴ 3፦27) የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ እንጂ በእርሱ ያደረው ነው አላለም'' የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት በመከተል ብዙዎችን መስክሯል። ጴጥሮስ (ማቴ 16፥13-17፣ ዮሐ 6፥ ናትናኤል ዮሐ 1፥50)

No comments:

Post a Comment