Monday, January 7, 2013

«ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ»

ልደቱ ለእግዚእነ

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ

ጠንካሮች የሃይማኖት አባቶቻችን «እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ በጥፋቱ ወድቆ የነበረውን ዓለም ያዳነበት ጥበቡ ይደንቃል» ይላሉ፡፡ አነጋገሩ አርቆ አራቅቆ ከማሰብ የመነጨ መሆኑን እኛም እረጋ ብለን ስናጤነው እናገኘዋለን፡፡ እርግጥም ዓለማትን የፈጠረ ከረቂቃኑ ፍጡራን አስከ ግዙፋኑ ድረስ በየቦታቸው ያደራጀ፣ አንዱንም ፍጥረት ያለ ምግብ ያልተወው አምላክ በግእዘ ሕፃናት በቤተ ልሔም መወለዱ እጹብ ነው፡፡
በሰማያዊ መንበሩ በዘባነ ኪሩብ እያለ በጎለ እንስሳ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተገኘ፡፡ ምንኛ ሰውን ቢወድደው ነው? ቅድመ ዓለም ያለ እናት ከአብ ድኅረ ዓለም ያለ አባት ከእመቤታችን ሁለት ልደትን ተወለደ፡፡ 
«ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይ ወፎች በምድር የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው» ተብለው የነበሩት ሰዎች በበደላቸው የተነሣ ተመልሰው ተገዢዎች ሆኑ፡፡ ዘፍ. 1ኮ28፡፡ ጸጋ እግዚአብሔርን ለብሶ የተወለደው ሰውነት ዕርቃኑን በመሆኑ አፈረ፣ በረደውም፣ ሊገዛቸው የተፈጠሩት አራዊት መልሰው አስፈራሩት የሚያሳድዱትም ሆኑ፡፡ ምድር እንኳን ሳትቀር እሾህና አሜከላን አበቀለችበት ክቡር የነበረው ተዋረደ፡፡ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ ትቶ ተሰደደ፡፡ በምድርም ላይ መጻተኛ ሆኖ ኖረ፡፡ 
ሁለተኛው አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው አዳም በመብል ምክንያት ያጣውን የልጅነት ጸጋ ሊመልስለት ክሦም ሊታረቀው ሰው ሆነ፡፡ ምንም ምን የሚወስነው የሌለ ምሉዕ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወሰነ፤ የማይዳሰሰው ተዳሰሰ፤ የአዳምን ዕርቃን የሚሸፍነው በበረት ተወለደ፤ በጨርቅም ጠቀለሉት፡፡

አዳም ዕጸ-በለስን ዐይቶ በተመኘበት ዐይኑኮ ግርማ አይሁድን በማየት፣ አዳም ወደ በለሷ በተጓዘበት እግሩኮ እግሮቹን ተቸንክሮ፣ በቆረጠበትና በበላበት እጁኮ እጆቹን ተቸንክሮ፣ ባጣጣመበት ጉሮሮውኮ መራራ ሀሞት ጠጥቶ፣ የሲኦል ስቃይ አስመርሮት አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ ብሎ ለጮኸው ጩኸትኮ እርሱ ጮኾ፣ አዳም በተቀበረበትኮ እርሱ ተቀብሮ ባጠፋው ሁሉ ሊክስለት ሰው ሆነ፡፡ አንክሮ ተዘክሮ ለዚህ ይገባል፡፡

የፍቅር አምላክ የሰውን ልጅ የወደደበት ምሥጢር ታላቅ፣ ለማዳንም ያደረገው ጉዞ ረቂቅ ነው፡፡ በኃጢአት ምክንያት የተዋረደውን ከክብሩ ያነሰውን ሰው ከፍ ለማድረግ እንደመጣ ሲያጠይቅ ከእመቤታችን ፣ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ቀጥሎ የምሥራቹን የላከው ወደ ተናቁት እረኞች ነው፡፡ «መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡» ሉቃስ 3፣10-12፡፡ ይህም ወንጌላዊው ሉቃስ እንደ ጻፈው «ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምሥራች» ነው፡፡

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ይሆን ዘንድ ሰው ሆነ፤ ስሙም አማኑኤል ተባለ፤ ትርጉሙም «እግዚአብሔር ከእኛ ጋር» ማለት ነውና፡፡ ማቴ. 1፡23፡፡

ስለ ድኅነተ ምእመናን፣ ነዳያንን ሊመግባቸው በሥጋና በነፍስ ደዌ የተያዙትን ሊያድናቸው፣ ለተማረኩት ነፃነትን ይሰብክ ዘንድ ዕውራን ያዩ ዘንድ /እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ እንዳለ ዮሐ. 8፡12፡፡/ የተናቁት ዓሣ አጥማጆች፣ ቀራጮች ይከብሩ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡• ለፍጥረቱ መሪ የትሩፋት ጀማሪ ይሆን ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ዮሐ. 13፣14፡፡
• ሕዝብና አሕዛብን አንድ ሊያደርግ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡ ገላ. 3፡28፡፡
• ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ሆነ፡፡ 1ቆሮ. 1፡20፡፡
• በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ የመጣውን ዲያብሎስን በመስቀሉ ድል ይነሳው ሥልጣኑንም ይገፍፈው ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ ቆላ. 2፡14፡፡
• ሀብታም ሲሆን፣ እኛ በእርሱ ድህነት ባለጠጎች እንሆን ዘንድ ስለእኛ ድሀ ሆነ፡፡ 2ቆሮ. 8፡9፡፡
• አዳምን ወደ ክብር ቦታው ለመመለስ እርሱ ማደሪያ ስፍራ አጥቶ በግርግም /በከብቶች በረት - በበጎች ጉረኖ/ ተወለደ፡፡ ሉቃስ 2፡7፡፡ 

ጌታችን ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ጠብቆ ከዕለቱ አንድ ቀን ከሰዓቱ ደቂቃና ሰኮንድ ሳያሳልፍ ተወለደ፡፡ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ «የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ» እንዳለ፡፡ ገላ. 4፡4፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ የተባለው ዓመተ ኩነኔ ወይም ዓመተ ፍዳ አዳም በሲኦል እንዲቀጣ የተፈረደበት ጊዜ እንዳለቀ ማለት ነው፡፡

ስለ ጌታችን መወለድ ብዙ ትንቢቶች ተነግረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹን እንጠቅሳለን፡፡ «ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤ ከእሥራኤል በትር ይነሣል» ዘኁ. 24፡17፡፡ ኮከብ በሰማይ የሚኖር ሲሆን ይኸኛው ኮከብ ግን ከሰማይ ወርዶ ከአብርሃም ዘር ከያዕቆብ ወገን ሥጋን ተዋሕዶ የተወለደው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ «እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ» እንዳለ፡፡ ራዕይ 22፡16፡፡ ከእሥራኤልም በትር ይነሣል ተብሏል፡፡ በሰው ልጆች ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ዲያቢሎስን በመስቀሉ ጠርቆ የሚያስወግድ ነውና፡፡

«የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም» እንዳለ ሐዋርያው ጌታችን ቀድሞ መልአክ የነበረ አሁን ሰው የሆነ አይደለም፡፡ ዕብ. 2፡16፡፡ ጌታችንም እየደጋገመ ራሱን «የሰው ልጅ» እያለ ሲጠራ እንመለከታለን፡፡ ማር. 8፡31፣ ማቴ. 16፡13፣ ማቴ. 7፡6፡፡

«ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር» በማለት ያስረዳል፡፡ ራዕይ 5.5፣ ዮሐ. 7፣42፡፡ «ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል» ኢሳ. 11፣1፡፡ ይህ ትንቢት የተነገረው ለእመቤታችን ሲሆን በትር ደረቅ እንደ መሆኑ መጠን ያፈራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህችኛዋ ከእሴይ ግንድ ከዳዊት የተገኘችው በትር እመቤታችንም ድንግል ሳለች ያለ ወንድ ዘር ቁጥቋጦ የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስን የመውለዷ ምስጢር ነው፡፡

እንዲሁም ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ይላል፡፡ «እነሆ ለዳዊት ጻድቅ ቁጥቋጦ የማስነሳበት ዘመን ይመጣል» ኤር. 23፡5፡፡ ያ በጻድቅ ቁጥቋጦ ሰው የሆነው አምላክ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

«ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች» የተባለው ለጌታ ነው ሚል. 4፡2፡፡ ከአማናዊት ምሥራቅ ድንግል ማርያም የተወለደ ነውና፡፡ «በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን ዐየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው፡፡» ኢሳ. 9፡2፡፡ ተብሎ የተነገረለት «ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበረ»፣ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም»፣ «በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር እኔ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ» ላለው ለወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዮሐ 1፡90፣ 8፡12፣ 12፡46፡፡

«አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፤ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፡፡ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፣ በእሥራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል፡፡» ሚክ. 5፡2 እንደተባለ ጌታችን በቤተ ልሔም በከብቶች በረት ተወለደ፡፡ ቤተ ልሔም ማለት የእንጀራ ቤት ማለት ነው፤ የሕይወት እንጀራ ኢየሱስ ክርስቶስ /ዮሐ. 6፡35/ ተወልዶባታልና፡፡ ኤፍራታም ትባላለች በያዕቆብ ዘመን ትጠራበት ነበር፡፡ ዘፍጥ. 35፡19 ትርጓሜዋም የፍሬ መያዣ /ጸዋሪተ ፍሬ/ ነው፡፡ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል የተቀባባት ሥፍራ ናት፡፡ /1ሳሙ. 16፡2/ ነገር ግን ከዳዊት ወዲህ ለንጉሥነት ማንም ስላልተቀባባት ታናሽ መስላ ነበርና፤ ነቢዩ የነገሥታት ንጉሥ ቅቡዕ ክርስቶስ /መሢህ/ የሚወለድባት መሆኑን አስረዳ፡፡ ከአብ ያለ እናት የተወለደውን ቀዳማዊ ልደቱንም ለማጠየቅ «አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ» በማለት ተናግሯል፡፡ በትንቢቱም መሠረት ጌታችን በዚያ ተወለደ፡፡ ሉቃስ 2፡5-7፡፡ እንደ ተወለደም አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተተነበየ ስሙ አማኑኤል ተባለ፡፡ «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች» ኢሳ. 7፡14፡፡ የሚለው ቃል ተፈጸመ፡፡ ማቴ. 1፡23፡፡

«ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፡፡ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» ኢሳ. 9፡5፡፡

የተወለደው ሕፃን አለቅነት በጫንቃው የሆነ ከማንም ያልተቀበለው የባሕርይው ነው፡፡ እርሱም ኃያል አምላክ፣ ሁሉን የሚገዛ፤ ሁሉንም ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ነው አለ፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ ኃያል አምላክ የለም፡፡ በግእዘ ሕፃናት ቢታይም እርሱ ግን እግዚአብሔር መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ አባትነቱ ለዘላለም የሚሆንም እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የሰላም አለቃም እርሱ ነው፡፡ «ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደ ሚሰጠው አይደለም» ያለው ከእርሱ በቀር ማንም ማን እውነተኛውን ሰላም መስጠት እንደ ማይቻለው «እኔ የምሰጠው ዓለም እንደ ሚሰጥ አይደለም» በማለት ያረጋገጠው የሰላም አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነቱን አረጋግጧል፡፡ «እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም» እንዲል፡፡ ዮሐ. 14፡27፡፡

የእግዚአብሔር ሰው መሆን በሕፃንነት ዕድሜም መገኘት ያስደነቀው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡፡ «ምን እላለሁ) ምንስ እናገራለሁ) ከዘመን አስቀድሞ የነበረ እርሱ ሕፃን ሆኗልና፤ እኔ ፈጽሜ አደንቃሁ፤ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚሆን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፣ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሠሥ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሠሠ፣ ኃጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን፤ በጨርቅ ጠቀለሉት፣ ይህን ወድዷልና፡፡» ሃይ. አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ 66፡17፡፡
• በዚህች የከበረች ዕለት እንስሶች እንኳን ሳይቀሩ ዘምረውባታል፡፡
• ተለያይተው የነበሩት ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ» እያሉ ዘመሩ፡፡ ተራርቀው የነበሩት ሰማይና ምድር በጌታችን ልደት አንድ ሆኑ፡፡
• ዛሬም ምእመናን ይህችን የዓመተ ምሕረት መጀመሪያ እና የዕርቅ ቀን ከዋዜማው ጀምሮ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው በመገኘት ጧፍ እያበሩ በደስታ እየዘመሩ ያከብሯታል፡፡ የተቻላቸው ደግሞ ወደ ላሊበላ አብያተ መቅደስ ተጉዘው «ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ - የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ» እያሉ ዕለቷን ያከብሯታል፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ከወጭው ዓለም በተወረሰ አጓጉል ሥልጣኔ መሳይ ነገር ብዙዎችን ሰዎች ወደ ሞት ጐተራ ሲከትታቸው ይታያል፡፡ «የልደትን በዓል ምክንያት በማድረግ በእገሌ ሆቴል የዳንስ ምሽት፣ በእገሌ አዳራሽ ወይም ኤግዚቢሽን ማዕከል የሙዚቃ ትርዒት» እየተባለ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ .. ወዘተ ይለፈፋል፡፡ በዚያም ተሰብስቦ በስካር መንፈስ ሕሊናውን ስቶ አንደ እንስሳ ሲተረማመስ ያድራል፣ በአንዲት ቀን የሁል ጊዜ ጸጸት በገንዘቡ ገዝቶ ይሸከማል፡፡ እኛ የምናውቀው ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚያስተምሩን «ደስ የሚለው ማንም ቢኖር ይዘምር፡፡» የሚል ነው ያዕ. 5፡13፡፡ እረኞቹ መላእክት የጌታን መወለድ ካበሠሯቸው በኋላ «እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ» ተባባሉ፤ ሄደውም የጌታን ልደት ተመለከቱ፣ ዘመሩም እንደ ተባለ /ሉቃስ 2፡13-20/ ዛሬም ወደ አማናዊት ቤተ ልሔም ቤተ ክርስቲያን ተጉዘን ደስታችንን በእልልታ እና በዝማሬ ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡

በአማናዊት ቤተ ልሔም ቤተ ክርስቲያን የሕይወት እንጀራና መጠጥ ኢየሱስ ክርስቶስ አለና እርሱን በልተን ጠጥተን የዘላለም ደስታን እንድናገኝ ሰው የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ይስጠን፤ አሜን፡፡ 

source: http://eotc-mkidusan.org/

ዓለምን የፈጠረው ተወለደ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment