Tuesday, January 22, 2013

ዘመነ አስተርእዮ/የመገለጥ ዘመን/




በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የቀን ቀመር መሠረት ከታህሳስ 29 ጀምሮ ያለውን ወቅት ዘመነ አስተርዮ ይባላል፡፡ አስተርእዮ ማለት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በዚህ ዓለም ኖሮ ሥራ ከሠራባቸው ዕለታት ከፍተኛ ምሥጢር የተገለጸበት ዕለት አንዱና ዋነኛው የጥምቀት ዕለት ነው፡፡ ድንቅ ምሥጢር ካሳየባቸው ቦታዎችም አንዱ ዮርዳኖስ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን ያሳታቸው እባብ ድል የሚነሳበት ዘመን እንደሚመጣ፣ ከሔዋን ዘር የሚገኘው/ የሚወለደው ጌታ የእባቡን ራስ ቀጥቅጦ እንደሚያጠፋው የተነገረበት (ዘፍ315) የእግዚአብሔር ቋንቋ የገባቸው አዳምና ሔዋን ይህንን አምላካዊ ተስፋ በማድረግ የተፈቀደላቸውን ዘመን በየዘመኑ የተነሱ ልጆቻቸውም ይህንን የተስፋ ቃል ሲጠባበቁ እግዚአብሔር እንደገለጸላቸው ስለርሱ ሰው መሆን ትንቢት ሲናገሩ ያንንም ቀን ለማየት ሲመኙ ነበር የኖሩት፡፡ ግን ሳያዩ አለፉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅ፣ የተናገረውን የማይረሳ ነውና የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ (ገላ44)፡፡
የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ፣ ያጣውን የልጅነት ጸጋ መልሶ ያድለው ዘንድ፣ ሁሉን ማድረግ የማይሳነው አምላክ በልዩ እና ድንቅ በተዋሕዶ ምሥጢር ሰው ሆነ፡፡ በሰላሳ ዘመኑ በባሕረ ዮርዳኖስ፣ በዕደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ተዘግቶ የነበረው ሰማይ ተከፈተ፣ የእግዚአብሔር ድምጽ ለሰው ልጅ ተሰማ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወረደ፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ምስጢር ተገለጠ (ማቴ316-17)፡፡ ስለዚህም ይህ ዘመን ዘመነአስተርእዮ ይባላል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት በመስራቱ ምክንያት እግዚአብሔርን የመሰለ ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጥቶ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አልነበረም አዳም በኃጢአቱ ምክንያት ጸጋው ተገፏል ባሕሪውም ጎስቁሏል ለ7 ዓመት በግልጥ ሲሰማ የነበረውን የአምላኩን ድምፅ እንኳ በኃጢአት ምክንያት መስማት ፈርቶ ‹‹በገነት ድምፅ ሰማሁ ዕራቁቴንም  ስለሆንኩ ፈራሁ ተሸሸግሁም›› ዘፍ. 31 እንዳለ ታዲያ ይህ ያለንበት ወቅት እርቅ የተጀመረበት' ሰው እና መላእክት በአንድ ቋንቋ የዘመሩበት' የእዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት' የሦስትነትን የአንድነትን ምሥጢር በግልጥ የታወቀበት' የነቢያት ትንቢታቸው ተስፋቸው የተፈጸመበት ወቅት ስለሆነ ቤተክርስቲያናችን የመገለጥ ዘመን ትለዋለች፡፡
በዚህ ዘመን ብሉይን ወደ ሐዲስ ዘመነ ፍዳውን ወደ ዘመነ ምሕረት የሚቀይር አንድ ጌታ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በኅቱም ድንግልና ያለ አባት በፍጹም ትሕትና ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነሳ፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት የዘመናት ጌታ እንዲቆጠርለት የማይወሰነው ጌታ ይጨበጥ ይዳሰስ ዘንድ ግድ ሆነ ግድ እንዲሆን ያደረገው እውነተኛ አምላክ ለሰው ልጅ የነበረው ፍቅር ነው፡፡ ‹‹እንዲሁ ወደድኳችሁ›› እንዳለ ‹‹ፍቅር ስሃቦ ለወልድ እመንበሩ›› ብሎ ሊቁ እንደተናገረው በፍጹም ካሳ ከፋይነት ያ ቃል እግዚአብሔር የነበረ ‹‹ቃል ሥጋ ሆነ፤ ጸጋና መንፈስን ተሞልቶ በኛ አደረ›› ዮሐ. 1፥14 ይህንን እውነተኛ ጌታ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዓለም ከስጦታዎች ሁሉ በላይ  የሆነውን ሕፃን አበረከተች፡፡ ‹‹ድንግሊቱ ሔዋን የእባብን ቃል ሰምታ አለመታዘዝንና ሞትን ፀነሰች ወንድሙን የሚገድለውን የሞትን ልጅ ገዳይ ቃየልን ወለደች ድንግል ማርያም ግን የብርሃናዊውን መልአክ የቅዱስ ገብርኤልን ቃል ብስራት ሰምታ ታዛዥ ሆነችና ሕይወት ክርስቶስን ፀነሰች ለሕዝብም የሚሞተውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደች ›› ሰማዕቱ ቅዱስ ዮስጢኖስ እንደተናገረው እውነተኛ የሕይወት መብልን ክርስቶስን ወለደችልን የመጀመሪያይቱ የማክሰኞ ምድር ያለምንም ዘር ለሥጋ የሚሆነውን አዝዕርቱን እፅዋቱን ፍራፍሬውን ስትሰጥ አማናዊት የሆነች የማክሰኖ ምድር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ያለ ወንድ ዘር የሥጋንም የነፍስንም ምግብ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደች፡፡ ‹‹ለዚህ ድንቅ ነገር ምሥጢር አንክሮ ይገባል ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው›› ሃይማኖተ አበው ይህ ያለንበት ወቅት የፍቅር መጀመሪያው የጥል ግርግዳ የመፍረሻው ዋዜማ ነበር፡፡ ለዚህ ነው መገለጥ የሚባለው እውነተኛ ፍቅር የተገለጠበት ስለሆነ በብሉይ ተሰውሮ የነበረው የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር ተገልጧል፡፡ ይህም በባሕረ ዮርዳኖስ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋው በማዕከለ ዮርዳኖስ በመለኮት የእዳ ደብዳቤውን ሲፍቅልን ከሰማይ አባት አብ የምወደው ልጄ ይህ ነው እሱን ስሙት ሲል መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ሲያርፍ ይህ ድንቅ ምሥጢር በድንቅ ስለታየ ዘመነ አስተርዮ ተብሏል፡፡ እንግዲህ የልደትም ሆነ የጥምቀት በዓል በተለይ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ለየት ያለ እይታ አለው ለምን ቢሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሕላዊ የአከባበር ወጉ ጥልቅና ከልብ የማይጠፋ ትውስታ ያለው ነው፡፡ ‹‹ፍቅር እግዚአብሔር ነው፡፡›› 1ዮሐ. 4፥8 ይህ ፍቅር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ባገኘንበት በዚህ ወቅት በዓሉን በመተሳሰብና በመረዳዳት በእውነተኛ ፍቅር ልናከብር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ‹‹በዓላችሁን ጠላሁት›› አሞ. 5፥21 ብሎ እንደወቀሰን እንደተናገረን የኛም በዓል አከባበር እግዚአብሔርን እንዳያስቀይም ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ 

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ ቤተክርስቲያናችንን ከፈተና ከመከራ ይሰውርልን፡፡

No comments:

Post a Comment