Thursday, February 21, 2013

የካቲት 2







በዚህች ቀን በግብጽ በርሃ ታላቅ አምድ ወደቀ፤ ይህም የባህታውያን ሁሉ አለቃቸው የሆነ አባ ጳውሊ ነው። ስርዓተ ብሕትውና በጳውሊ ስርዓተ ምንኩስና በእንጦኒ ተጀምሯል ይላል፤ ጳውሊ አባቱ ባለጸጋ ነበር ሲሞት ለታላቅ ወንድሙ በጴጥሮስ እጅ አድርጎ ኃላ አካለ መጠን ሲያደርስ ከፍለህ ስጠው ብሎት ተናዞ አረፈ፤ አባ ጳውሊ አካለ መጠን ሲደርስደረስሁ ልጅ ፈላሁ ጠጅየአባቴን ገንዘብ ከፍለህ ስጠኝ አለው አይሆንም አልሰጥህም አለው ምነው ቢለው ልጅ ነህ ታጠፋዋለህ ብዬ ነው ይለዋል አላጠፋውም ስጠኝ ይለዋል ግድማ ካልኸኝ ብሎ ብዙውን አስቀርቶ ጥቂቱን፤ መልካሙን አስቀርቶ ተራ ተራውን ሰጠው አባ ጳውሊ በዚህ ተበሳጭቶ ዳኛ ጋር ሄደ በመንገድ ላይ አንድ ባለጸጋ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት አየ አባቴ ባለጸጋ ነበር ሞተ ይሄም ባለጸጋ ነበር ሞተ እኔስ ነገ እሞት የለምን ብሎ ወደ ወንድሙ ተመልሶ ወንድሜ ገንዘቡ ላንተ ይሁን ትቼልሃለው ብሎ ከቤት ወጠ፤ መጀመሪያ 3 ቀን ከመቃብር ቤት ገብቶ ጸለየ 3ኛው ቀን ከሰማይ ግማሽ ህብስት ወረደለት፤ ገረመው፤ ፈጽሞ ሳይለዩ እንዲህ ከሆነማ ፈጽሞ ቢለዩማ እንደምን ያለ ተአምር በተደረገ ብሎ አናብስት አናምርት አካይስት አቃርብት ካሉበት ነቃዐ ማይ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ድሩክ ለተአቅቦ ይለዋል ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በርሃ ገባ፤ የሰው ፊት ሳያይ 80 ዓመት በተጋድሎ ኖሯል። ምግቡን ግማሽ ህብስት በየቀኑ የሚያመጣለት ቁራ ነበር።  የእረፍቱ ቀኑ ሲደርስ ከአባ እንጦንስ ጋር በእግዚያብሔር ፈቃድ ተገናኝተው ብዙ ነገር ተጨዋወቱ በተለይም በኃለኛው ዘመን ስለሚነሱት መነኮሳትና፤ ግብጽ በሙስሊሞች እንደምትወረር ብዙ ሚስጢር አወሩ ብዙ ትንቢትም ተናገሩ፤ ይህንንም በጥቂቱ ጥር 22 ቀን ጽፈነዋል። ከዚህ በኃላ አባ ጳውሊ አስኬማ መልአክ አምጣሊኝ ብሎ ይልከዋል፤ አባ እንጦስ ወደ ገዳሙ ሄደ 2 ቀን ጎዳና ነው ሲመለስ በርሃው ላይ ሰማያውያን መልአክ ሰፍረውበት ሲዘምሩ ሲያመሰግኑ አየ፤ ልብን የሚመስጥ የእጣን መዓዛም አሸተተ፤ ምንድር ነው ? ብሎ አንዱን መልአክ ይጠይቀዋል አባ ጳውሊ ሞቶ ነፍሱን እያሳረግን ነው ይለዋል ይሄን አስኬማ አምጣሊኝ ብሎኝ ነበር ምን ላድርገው ? ይለዋል፤ ጸሎት አድርሰህ አድርግለት፤ ደግሞም መቃብሩን የሚቆፍሩ አንበሶች ይመጣሉ ቦታውን ለክተህ ስጣቸው አለው፤ ወደ ገዳሙ ሲገባ እጁን መስቀልያ እንደዘረጋ ሞቶ አገኘው የሚጸልይ እንጂ የሞተ አይመስልም ነበር አስኬማውን አድርጎለት ሲያበቃ ከራስጌው ቆሞ ኤልያስ ልበልህ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ልበልህ እያለ አለቀሰለት፤ ሁለት አንበሶች መቃብሩን ቆፈሩለት ገንዞ ቀበረው። 80 ዘመን ሙሉ ለብሶት የኖረው የሰሌን ልብስ ነበረችው ወስዶ ለሊቀ ጳጳሱ ለአባ አትናቴዎስ ሰጠው፤ በዚህች ልብስ አባ አትናቴዎስ ብዙ ተአምራትን ሰረቶበታል ይልቁንም ሙት አስነስቶበታል። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከአባ ጳውሊ በረከት ያሳትፈን። በነገራችን ላይ የዚህ አባት ገድሉ በስፋት ከመጻፉ ባሻገር ግብጻውያን  ፊልም ሰርተውለታል  ይህን ፊልም ማህበረ ቅዱሳን ጥሩ አድርገው ወደ አማርኛ ተርጉመውታል። የበረታ ገድሉን ያንብብ የደከመው ፊልሙን ይመልከት።




No comments:

Post a Comment