Wednesday, March 6, 2013

የካቲት 28


በዚህች ቀን ሮማዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ አረፈ። በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን አሉ፤የሰራዊት አለቃ የተሰኘውና በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት የሞተው ቴዎድሮስ ዋነኛው ነው እረፍቱ ሐምሌ 20 ሲሆን በአገራችን በስሙ አብያተክርስቲያናት ታንጸውለታል፤ ቢሾፍቱ መስመር የረር በዓታ ጽላቱ አለ። በየዓመቱ ግንቦት 21 ቀን ግብጽ በደብረ ምጥማቅ እመቤታችን ለክርስቲያኑ ለአህዛቡ ተገልጻ ትታይ ነበር፤ ታዲያ ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አባታችን አዳምን አሳዪን ሲሏት አዳምን ታሳያቸዋለች፤ ሄዋንን፤ ዳዊትን ሙሴን አብርሃምን... የጠየቋትን ከገነት እየጠራች ታሳያቸው ነበር ይላል ተአምረ ማርያም፤ ሰ...ማዕታትን አሳዪን ሲሏት ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ መርቆርዮስንና ይህንን ቅዱስ ቴዎድሮስን ነበር ጠርታ ይምታሳያቸው ስለዚህም በ3ኛ ደረጃ ያለ ሰማዕት ነው። ምስራቃዊ ቴዎድሮስ የሚባል ሰማዕትም አለ፤ ቴዎድሮስ ሳልሳይም ( ቴዎድሮስ 3ኛው) ኢትዮጰያዊ ነው ታሪኩን ግን እዚህ መጻፍ የተመቸ አይደለም ምነዋ ቢባል ዘመኑ ክፉ ነውና፤ ዳሩ ግና ታሪኩ ገድለ ፊቅጦር፤ድርሳነ ኡራኤል፤ትልቁ ፍካሬ እየሱስ ላይ በስፋት ተጽፏል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ ቴዎድሮሶች ይህንን አልን፤ ለመሆኑ ዛሬ መታሰቢያውን የምናደርግለት ቴዎድሮስ ታሪኩ እንዴት ነው ቢሉ፤ በመክሲሞስና መክስምያኖስ ዘመን የነበረ ነው አገሩ ሮም ነው፤ እንሾምሀለን እንሸልምሀለን ለጣኦት ስገድ አሉት፤ ሹመት ሽልማታችሁ ለጥፋት ይሁንባችሁ ከእግዚያብሔር በቀር አምላክ የለም አላቸው ዘለፋቸው እረገማቸውም፤ ዘቅዝቀው ሰቀሉት ደሙ እንደ ውኃ እስኪፈስ ገረፉት ደሙ የነካቸው ብዙ በሽተኞች ዳኑ ይህንንም ያዩ ብዙዎች አመኑ፤ዳግመኛ የእሳት ምድጃ ውስጥ ከተቱት ነፋስ ነፈሰ ነጎድጓድም ሆነ ምንም ሳይነካው ከእሳት ወጣ፤ ዳግመኛ አፉን ለጎሙት እጆቹን እግሮቹን ቸንክረው ለአንበሳ ጣሉት፤ አንበሳው እንባውን አፈሰሰ ይላል ተንበርክኮ ሰገደለት ዳን 6፤22። በዚህ ጊዜ ጌታችን ተገልጾ “ስምህን የሚጠራ መታሰቢያህን የሚያደርገውን እምርልሃለው” ሲል ቃል ኪዳን ገባለት ማቴ 10፤41 ፤ ከዚህ በኃላ የሁለት መቶ ሸክም እንጨት መቶ ልጥር ባሩድ፤የዶሮ ማር፤ነሐስ አመጡ፤ እጅግ እስከሚግል አነደዱት እሳት ውስጥ ወረወሩት፤ምስክርነቱን በዚህ ፈጸመ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ገብርኤል ነፍሱን ተቀብለው በሶስት አክሊል አቀዳጇት፤ስጓውንም አውሳብያ የተባለች የመኮንን ሚስት ወስዳ በገላትያ ቀበረችው ቤተክርስቲያንም ሰራችለት። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።

No comments:

Post a Comment