Tuesday, March 5, 2013

የከበሮ ክፍል ምሳሌያዊ ትርጉም

የከበሮ ክፍል ምሳሌያዊ ትርጉም አለው ምሳሌውን ግልጽ ለማድረግ የሚከተለውን ስዕላዊ መግለጫ እንመለከት እና ወደ ትንታኔው እንሂድ።
ከበሮ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው። ግራና ቀኝ ሲመታ ስንመለከልት ጌታችን በአይሁድ እጅ በጥፊ መታቱን ያስታውሰናል።




. ሰፊው የከበሮው አፍ
 
የመለኮት ምሳሌ ነው።ይህ የከበሮ አፍ የጌታችንን የባህሪ አምላክነት ምሉዕ በኵለሄ መሆኑን አስልጣኑ ወሰን ድንበር እንደሌለው የሚያስታውሰን ነው።የ አፉን መስፋት ስንመለከት አጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በህልውና በመለኮት ባሕርይ አባቱ ከአብ ባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተስተካከለ ሁሉን የያዘ ሁሉን የሚገዛ መሆኑን እናስባለን።

. ጠባቡ የከበሮው አፍ
 
የትስብእት ምሳሌ ነው በመዝሙር ጊዜ እየተቁረቁረ ድምጽ የሚሰጠው ጠባቡ የከበሮ አፍ የወልድ እግዚአብሔርን በጠባብ ደረት አጭር ቁመት ተወስኖ መገለጥ የሚያመለክተን ነው።ፍጥረታትን ሁሉ የሚገዛ እሱ በስልጣኑ ሽረት በመለኮቱ ኅልፈት የሌለበት ቢሆንም ስጋን ተዋህዶ ተገልጧል።ይህንን ጠባብ የከበሮ አፍ ስንመለከት ሁሉን የሚገዛ እሱ አጭር ቁመት በጠባብ ደረት መወሰኑን እናስባለን። ዩሐ፤፩፡፩-፩፬

. ከበሮው የሚለብሰው ጨርቅ
 
ከበሮ የጌታችን ምሳሌ እንደሆነ ከላይ አይተናል። ከዚህ አንጻር የለበሰው ጨርቅ ደግሞ በዕለተ ዓርብ አይሁድ ጌታችንን ያለበሱት ጨርቅ (ቀይ ከለሜዳ)ምሳሌ ነው።
''
ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት'' ማቴ 26:28

. በከበሮው ላይ የተለጠፈው ጠፍር
 
በጌታችን ጀርባ ላይ የታየው የግርፋት ሰንበር ምሳሌ ነው። ጠፍሩን በከበሮው ላይ ስንመለከት በጌታችን ጀርባ ላይ የታየውን ሰንበር እናስታውሳለን።
''
እጆቼን እና እግሮቼን ቸነከሩኝ አጥንቶቼ ሁሉ ተቆጠሩ'' መዝ 21(22):16 እንዲል ጌታችን አጥንቱ እስኪቆጠር ጀርባው እስኪቆስል ተገርፏልና የዚያ ምሳሌ ነው።

. የከበሮው ማንገቻ
 
የከበሮውን መምታት ስናስብ አንገታችን የምናስገባው ማንገቻ ጌታችንን አስረው የጎተቱበት ገመድ ምሳሌ ነው። አይሁድ ጌታችንን ወደ ቀራኒዮ ሲወስዱት የእጁ መጋፊያና መጋፊያ እስኪገጥም ድረስ በገመድ የእንግርግሪት አስረው ጎትተውታል መንገቻውን ከበሮው ላይ ስናይ ይኽንን ጌታችን የታሰረበትን ገመድ እናስታውሳለን።

1 comment: