Sunday, June 30, 2013

አባ ሙሴ ጸሊም

አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ
በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡ ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡
አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡
የአባ ሙሴ ጸሊም በረከት ይደርብን አሜን
ዋቢ ስንክሳር ሠኔ 24
በበረሓው ጉያ ውስጥ

No comments:

Post a Comment