Saturday, August 31, 2013

ነሐሴ 25



በዚህች ቀን እንድርያኖስ በሰማዕትነት አረፈ፤ ይህ ሰማዕት ቀድሞ የጣኦት አምላኪው ንጉስ የመክስምያኖስ መኮንን ነበር፤ 24 ቅዱሳን መክስምያኖስ ላቆመው ምስል አንሰግድም ብለው መከራ ሲቀበሉ ተመለከተ የልባቸውንም ጽናት አደነቀ፡፡ ይህንን ሁሉ መከራ የምትቀበሉት ምን እናገኛለን ብላችሁ ነው ሲልም ጠየቃቸው፤ እነርሱም ስለሚጠብቃቸው ተስፋ ስለክርስቶስ ሁሉንም ነገር ነገሩት፤ በዚህም የእንድርያኖስ ልቡ ተሰበረ፤ ወደ ንጉሱም ሄዶ በክርስቶስ ማመኑን ተናገረ፤ ንጉሱም አብደክ መሆን አለበት አለው፤ አንድርያኖስም የለም ቀድሞ ነበር ያበድኩት አሁን ግን ከእብደቴ ተመልሻለው አለው፡፡ ከዚህ በኃላ እስረት ቤት ወረወረው፤ የሆድ እቃው እስኪዘረገፍ አስደበደበው፤ በድጅኖ ጭኑን አስቀጠቀጠው ልዩ ልዩ መከራ አደረሰበት በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በሰማእትነት አረፈ፡፡ በረከቱ ይደርብን፡፡
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ነሐሴ ፳፬ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት


አቡነ ተክለኃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት መጋቢት ፳፬ ቀን ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታሕሣሥ ፳፬ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡

ወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡ ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ
«አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡»
/ገድለ ተክለ ኃይማኖት ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ኃይማኖት መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ ተብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲገልፅ:-
«እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈሳዊ ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ ቀጥቅጠዋል።
«ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .» በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችንለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡ እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር


Friday, August 23, 2013

+የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ሞትና ትንሣኤዋ +



የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን) ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማክረው መጡ፡፡
ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ 14 (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ 12 ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእመቤታችን ትንሣኤ አስቀድሞ በትንቢት መስታወትነት ታይቶት «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅድስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት» (መዝ.1318)፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን ቃለ ትንቢት አስቀድሞ ክርስቶስ እንደሚነሣ ከገለጸ በኋላ ቀጥሎ የመቅደሱ ታቦት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደምትነሣ ይናገራል (ማቴ535 ገላ 4 26 ዕብ 1222 ራዕ 312)፡፡