Friday, August 23, 2013

+የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ሞትና ትንሣኤዋ +



የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሞትና ትንሣኤ ነገረ ማርያም፣ ስንክሳር እና ተኣምረ ማርያም እንደሚያስረዱት፤ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡ ሞቷ የሚያስደንቅ መሆኑን ታላቁ የቤተክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የሐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ሁሉ የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን) ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማክረው መጡ፡፡
ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ 14 (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ 12 ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእመቤታችን ትንሣኤ አስቀድሞ በትንቢት መስታወትነት ታይቶት «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅድስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት» (መዝ.1318)፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን ቃለ ትንቢት አስቀድሞ ክርስቶስ እንደሚነሣ ከገለጸ በኋላ ቀጥሎ የመቅደሱ ታቦት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደምትነሣ ይናገራል (ማቴ535 ገላ 4 26 ዕብ 1222 ራዕ 312)፡፡

No comments:

Post a Comment