Thursday, October 31, 2013

ጥቅምት 22



ጥቅምት 22

በዚህች ቀን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አረፈ፤ የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ስራን የጻፈልን አባት ነው፤ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድዕት ነው፤ቀድሞ ዶክተር ነበር መድሐኒት ቀምሞ የስጋ በሽታን የሚፈውስ በኃላ ግን ወንጌልን ሰብኮ የነፍስ ቁስልን የሚፈውስ ሆኗል፤ ወንጌሉን መቼ ጻፈው ቢሉ ጌታ ባረገ በ 22 ዓመቱ የት ጻፈው መቄዶኒያ በምን ቋንቋ በዮናኒ፤ማቴዎስ በዕብራይስጥ፤ ማርቆስ በሮማይስጥ፤ ዮሐንስ በጽርዕ ቋንቋ ነው የጻፉት። ቅዱስ ሉቃስ መጀመሪያ ዮሐንስን ተከትሎ ወንጌል ሰበከ በኃላም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሮም ሲሰብኩ ቅዱስ ጳውሎስ በኔሮን እጅ በሰማዕትነት ሞተ፤ ብቻውን እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ የክርስቲያኖች ቁጥር በዛ አብያተ ጣኦታትንም አፈራረሰ በዚህም ንጉሱ ተቆጣ ሸንጎ ፊት አቅርቦም፤ ወንጌልን የጻፈች እጅህ ይህች ነችን? ብሎ ቀኝ እጁን ቆረጠው፤ ቅዱስ ሉቃስም እየሱስ ክርስቶስ የተቆረጠ እጅ አይደለም የተቆረጠች ነፍስንም ይቀጥላል ብሎ በግራ እጁ የተቆረጠች እጁን አንስቶ እንደ ቀድሞ አደረጋት፤ በወንጌል ላይ ጌታችን የተቆረጠች የማልኮስን ጆሮ ወደ ቀደመ ቦታዋ እንደ መለሳት ልብ ይሏል፤በኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል ከኔም በላይ ያደርጋል ያለ ጌታ የታመነ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ያደረገውን ተአምር ተመልክተው 267 ወታደሮችና መኮንኑ በክርስቶስ አምነዋል፤ ንጉሱም በሰይፍ አስፈጅቷቸዋል፤ቅዱስ ሉቃስንም በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጦ በአሸዋ ከተሞላ ስልቻ ጋር አድርገው ወደ ባህር ጥለውታል፤ ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን፤

ምድረ ኢትዮጵያ ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም



ምድረ ኢትዮጵያ ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍና ሰሎሜ በደመና ተጭነው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ናግራን ከተባለ ሀገር ደረሱ፡፡ በናግራን ሳሉ ጌታ እንዲህ አለ፡፡ ከቀኝ ጎኔ የሚፈሰው ደሜ በብርሃናት አለቃ በዑራኤል እጅ ተቀድቶ በቅድሚያ በዚች ሀገር ይፈሳል ወይም ይረጫል፡፡ እናቱንም እንዲህ አላት አንቺ በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና እንደወለድሽኝ አምነው የሚያከብሩሽ በእኔም የሚያምኑ ብዙ የተቀደሱ ሰዎች በዚህ ሀገር ይወለዳሉ፡፡ ከናግራን ተነስተው ለትግራይ ትይዩ ከሚሆን ሐማሴን ከሚባለው ሀገር ሲደርሱ በምሥራቅ በኩል ከፍተኛ ተራራ ተመለከቱና ወደ ተራራው ሄዱ፡፡ ጌታም በተራራው ላይ ሳሉ እናቱን እንዲህ አላት ይቺ ተራራ ምስጋናሽ የሚነገርባት ቦታ ትሆናለች፡፡ የተራራዋም ስም ደብረ ሃሌ ሉያ ወይም ደብረ ዳሞ ይባላል፡፡ ትርጓሜውም የአምላክ ልጅ የመስቀሉ ቦታና የስሙ መገኛ ወይም አደባባይ ማለት ነው፡፡ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮን ወደምትኖርበት ወደ አክሱም ደረሱ፡፡ ታቦተ ጽዮን ባለችበት ቦታ ሳሉ ባዚን የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ታቦተ ጽዮንን ለመሳለም መጣ፡፡ የካህናቱ አለቃ አኪን ለንጉሡ የኢሳይያስን መጽሐፍ አነበበለት፡፡ የተነበበውም የመጽሐፍ ክፍል ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች የሚል ነበር፡፡ ስደተኞቹ ግን ለንጉሡም ሆነ ለካህናቱ ሳይገለጡ የመጽሐፉን ቃል ከሰሙ በኋላ በደመና ተጭነው ወደ ደብረ ዐባይ ሄዱ ፡፡ ጌታም እናቱን እንዲህ አላት ይህች ሀገር እንደአክሱም ለስምሽ መጠሪያ ርስት ትሁን በኋላ ዘመን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ሕጌን የሚያስተምሩ አንቺን የሚወዱ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ ከዚያም በኋላ ከደብረ ዐባይ ተነስተው ዋሊ ወደ ሚባለው ገዳም /ወደ ዋልድባ / ሄዱ፡፡ በዋልድባ በረሃም ሳሉ በራባቸው ጊዜ ጌታ በዮሴፍ ብትር የአንዱን ዕንጨት ስር ቆፈረ፡፡ ሦስት መቶ አስራ ስምንት ስሮችን አወጣና ለእናቱ ብይ ብሎ ሰጣት፡፡ እናቱም ይህን የሚመር ዕንጨት አልበላም አለችው፡፡ ጌታም በኋላ ዘመን ስምሺን የሚጠሩ አንቺን የሚያከብሩ ብዙ መናንያን ይህን እየበሉ በዚህ ቦታ ይኖራሉ፡፡ ዕንጨቱም የሚጣፍጥ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ ከዚህ በኋላ በደመና ተጭነው ከዋልድባ ወደ ጣና የባሕር ወደብ ሄዱ፡፡ በጣና ደሴትም ደጋግ ሰዎች ተቀብለዋቸው ሦስት ወር ከአስር ቀን ተቀመጡ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች በደስታ ተቀብለዋቸዋል እንደ ግብፃውያን አላሰቃዩአቸውም ፡፡ በጥር አስራ ስምንት /18/ ቀን ዑራኤል መጥቶ የሄሮድስን መሞት ነገራቸው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ በደመና ከተጫኑ በኋላ ጌታ እናቱን እንዲህ አላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎች ሁሉ ለስምሽ መታሰቢያ ይሆኑሽ ዘንድ አሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ ፡፡ ብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎችን ሜዳዎችን ኮረብታዎችን አሳያት፡፡ እመቤታችን ሁሉንም ቦታዎች እየተዘዋወረች እንድታይ ልጅዋን ጠየቀችው፡፡ ልጅዋም የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ነገራት፡፡ በብሩህ ደመና ላይ ተቀምጠው ክፍላተ አህጉር እየተዘዋወሩ ተራራዎችን ወንዞቸን አስጐበኛት የኢትዮጵያን ምድር ከጐበኙ በኋላ በደመና ተጭነው ጥር 29 ቀን ምድረ ግብፅ ደረሱ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ታሪክ በድርሳነ ዑራኤል ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 20

ጥቅምት 20
በዚህች ቀን አባ ዮሐንስ ሐጺር አረፈ፤ ቁመቱ አጭር ስለሆነ ነው ዮሐንስ ሐጺር የተባለው፤በ18 ዓመቱ በገዳመ አስቄጥስ መንኩሶ በተጋድሎ ኖረ፤ ይህ አባት ነጽሮተ ስሉስ ቅዱስ የደረሰ አባት ነው፤እዚህ ደረጃ የደረሱ አባቶች ቀና ቢሉ ሥላሴን ይመለከታሉ ዝቅ ቢሉ እንጦሮጦስን ያያሉ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የገዳሙ አብምኔት ሊፈትነው ብሎ ደረቅ እንጨት ሰጠው ይህንን ተክለህ አለምልመህ ፍሬውን አምጣሊኝ አለው፤እርሱም እንጨቱን ተከለው 3 ዓመት ሙሉ ከሩቅ ቦታ ውሃ እየቀዳ አጠጣው በ3ኛው ዓመት ጸደቀ ለመለመ ትልቅ ዛፍም ሆነ፤ ፍሬም አፈራ፤ መነኮሳቱ ይህ የትእግስት ውጤት ነው ብለው ፍሬውን ቀምሰውለታል፡፡ አንዲት አትናስያ የምትባል ሴት ነበረች፤ መጀመሪያ ጻድቅ ነበረች በኃላ ላይ በዝሙት ወደቀች ዘማዊም ሆነች፤ የቀድሞ ቅድስናዋን የሚያውቁ መነኮሳት ሊመክሯት ቢመጡ ሳቀችባቸው አሁን ማንን እንላክ ብለው አሰቡ ዮሐንስ ሐጺርን ላኩት፤ ተራ ሰው መስሎ ገባ፤ ለዝሙት የመጣ መስሏት ተቀበለችው፤ተጫወት አለችው ዮሐንስ ሐጺር ማልቀስ ጀመረ ምን ያስለቅስሃል ትለዋለች መልክሽ ደስ ብሎኝ ይላታል፤ደስ የሚል መልክ ያስቃል እንጂ መች ያስለቅሳል ትለዋለች የለም ነገ ገሃነም እንደምትወርጂ ታይቶኝ ነው አንድም ብዙ አጋንንት በሰውነትሽ ሲወጡ ሲወርዱ አያለሁ አላት፤ ደነገጠች ምን ይሻለኛል ትለዋለች፤ ንስሃ ገቢ ማን ያስታርቀኛል ኃጢያቴ ብዙ ነው ትለዋለች፤እኔ አስታርቀሻለሁ ተከተይኝ ብሎ ወጣ ልዋል ልደር ሳትል በሯን እንደተከፈተ ተከተለችው በልስላሴ የኖረ እግር ተበጣጥሶ በበዙ ደካም ሲመሽ ከገዳሙ ደረሱ፤የምታርፍበትን ቦታ ለይቶ ሰጣት፤ ሌሊት ለጸሎት ሲነሳ መላአክት ሲወጡ ሲወርዱ ያያል፤ ምንድን ነው ብሎ አንዱን መልአክ ይጠይቀዋል፤ትላንትና አንተን ተከትላ የመጣችው ሴት ሞታ ነፍሷን እያሳረግን ነው ይለዋል፤ እግዚኦ ንስሃ ሳትገባ ብሎ ይደነግጣል፤ አንተን ልትከተል ገና አንድ እግሯን ከቤት ስታወጣ ኃጢያቷ በሙሉ ተፈቆላታል፤ አሁን ወደ ገነት እየወሰድናት ነው ይለዋል፤ዮሐንስ ተገረመ፤የመቃብሯስ ነገር አለው፤ አንበሶች ይመጣሉ ቦታውን ለካላቸው ይለዋል፤አንበሶች ቆፍረውለት ቀብሯታል፤ ዮሐንስ ሐጺር በተጋድሎ ኖሮ በዛሬዋ ዕለት አርፏል፤ በረከቱ ይደርብን፡

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 19

ጥቅምት 19
በዚህች ቀን ጻድቁ ንጉስ ይምርሃነ ክርስቶስ አረፈ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው በላስታ ነግሶ የነበረው ንጉስ ጠቢባንን ይሰበስብና ከኔ በኃላ የሚነግሰው ማን ነው ? ብሎ ይጠየቃቸዋል እነርሱም የወንድምህ ልጀ ይምርሃነ ክርስቶስ ነው ይሉታል፤ልጂቼ እያሉ እንዴት እርሱ ይነግሳል ብሎ ይናደዳል፤ ሊገድለውም ይፈልገዋል፤ ይምርሃነ ክርስቶስም ፈርቶ ወደ እየሩሳሌም ይሰደዳል፤ በዚያም የሌዊ ነገድ የሆነችውን ቅድስት ህዝባ የምትባል ሴት ያገባል ቅስናም ተቀብሎ ማገልገል ይጀምራል፤ከረጀም ጊዜ በኃላ የሚያሳድደው ንጕሰ ሲሞት ወደ አገሩ ኢትዮጵያ ይመለሳል፤ ህዝቡንም ወንጌል ሲያስተምር ድውያንን ሲፈውስ አይተው የአገር ሸማግሌዎች ተሰብስበው ስምህ ማን ነው ይሉታል ይምርሃነ ክርስቶስ እባላላሁ ከነገስታቱ ወገን ነኝ ይላቸዋል፤ እነርሱም በጣም ተገረሙ፤ ምን አስገረማቸው ቢሉ ይምርሃነ ክርስቶስ የሚባል ደገኛ ንጉስ ሲነግስ ሃይማኖት ይቀናል ፍርድ ይስተካከላ፤በዘመኑ ብዙ የውጭ አገር ህዝቦች ወደ ኢትዮጰያ ይጎርፋሉ የሚል ትንቢት ነበርና፤ በእግዚያብሔር ፈቃድ ቀብተው አነገሱት፤እርሱም ንግስናን ከክህነት ጋር አጣምሮ ህዝቡን በፍቅር አያገለገለ ኖረ። የሚገርመው ቤተመቅደስ ገብቶ ሲቀድስ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ሰማያዊ ህብስትን ሰማያዊ ጽዋን ይዞለት ይመጣል ያንን የቅዳሴ ጸሎት አድርሶበት ለህዝቡ ያቆርብ ነበር፤ መልአኩ ለ 22 ዓመት ሳቋርጥ አምጥቶለታል፤ ይህ ቅድስናው በዓለም ተሰማ ከሮም ከግብጽ ከግሪክ 5470 ክርስቲያኖች ወደርሱ መጥተው በእጁ ይህንን ሰማያዊ ህብስት ተቀብለዋል፤ እንዴት መጣችሁ ብሎ ይጠይቃቸዋል፤ መልከጼዴቅ የሚባል በበርሃ የሚኖር አንድ ባህታዊ የእግዚያብሔር መልአክ ሰማያዊ ህብስት ይዞ ሲወርደ ያያል ለየትኛው መነኩሴ ልትሰጥ ነው ብሎ ይጠይቀዋል እርሱም ለመነኩሴ አይደለም ለንጉስ ነው ይለዋል፤ ምን አይነት ቅዱስ ንጉስ ቢሆን ነው ሰማያዊ ህብስት የሚወርድለት ይህን ንጉስ ማየት እፈልጋለሁ ይለዋል መልአኩም አንተ የእረፍትህ ቀን ደርሷል አታየውም ብሎት ይሄዳል፤ እርሱም እኛን ጠርቶ ይህንን ነገረን ወደ አንተም መጣን ብለው የአመጣጣቸውን ነገር ነግረውታል፤እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን ያየ አይናችን ሌላ አያይም ብለው ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እዚያው ላስታ ቡግና ኑረው እዚያው አርፈዋል አጽማቸው ዛሬም ድረስ ሳይፈርስ ሳይበሰብስ ይምርሃነ ክርስቶስ ባነጸው ቤተክርስቲያን በስተምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል፤ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ለ 41 ዓመት በቅድስና በተጋድሎ ህዝቡን ሲመራ ኖሮ በ 97 ዓመት ከ 5 ወሩ በዛሬዋ ቀን አረፈ፤ ይህ ቅዱስ አባት በባህር ላይ ያነጸው ቤተክርስቲያ እጅግ የሚያስገርም ነው የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ 80 ዓመት ይቀድማል፤ ይህን የመሰለ ህንጻ በዚያን ዘመን አይደለም ለመስራት ለማሰብም ይከብዳል፤ ይህ ህንጻ ከከበሩ ድንጋዮች ነው የተሰራው በሩ አርዘ ሊባኖስ ከሚባል እጽ የተሰራ ሲሀን የግብጽ ንጉስ ነው የላከለት ግድግዳው በእንቁ የተንቆጠቆጠ ነው፤ በውስጡ የእመቤታችን፤ የቅዱስ ቂርቆስ፤ የጊዮርጊስ፤ የሩፋኤልና የራሱ የይምርሃነ ክርስቶስ ታቦታት አሉ፤ እናቶቻችን ወደዚህ ቦታ ሲሄዱ “”እላዩ አረንÙዴ ውስጡ ባህር ይምርሃነ ክርስቶስ የዋሻው ደብር’’ እያሉ የሚዘምሩት ለዚህም አይደል፡፡ ይህን ቦታ ለማየት ያብቃን ከበዓሉም በረከት ያሳትፈን፡፡
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 18


በጥቅምት 18 ቀን መታሠቢያቸው የሆኑ ቅዱሳኖች እናስተዋውቆት::ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቀ ዻዻስ:ቅዱስ ሮማኖስ ሰማዕት አርቴማዎስ:ጻድቅ ኤርሰጦስ ሰማዕት በዓለ እረፍታቸውና:3ቱ ደቂቅ የተወለዱበት ዕለት:ቅዱስ ወለዲኖስ ሹመቱ:ዓመታዊ በዓላቸው ነው::ቅዱስ ዮሐንስ:ቅዱስ አዲራ:አቡነ ኤውስጣቴዎስ ወርሀዊ መታሠቢያ በዓላቸው ነው::ምንጭ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ 36ቱ ቅድሳት

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 17


ጥቅምት 17
የቀዳሚ ሰማዕት የሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሾመበትን ቀን ቤተክርስቲያን ታከብራለች፤መስከረም 15 ፍልሰተ አጽሙ ነው ጥር 1 እረፍቱ ነው፤ እነዚህ 3 ቀናት ሰማዕቱ በሰፊው ይዘከርባቸዋል። ቅዱስ እስጢፋኖስ አባቱ ስምኦን እናቱ ማርያም ስና ይባላሉ፤የአብርሃም ዘር አይሁዳዊ ናቸው ልጃቸውን በጥበብ አሳደጉት፤ እስጢፋኖስ ማለት ወደብ ጸጥታ ማለት ነው። ምነዋ ቀዳሚ ሰማዕት ተባለ ቀደምት ነብያት በመጋዝ ተሰንጥቀው እንደ ሽንኩርትም ተቀርድደው የለም ወይ ቢሉ ከጌታችን እርገት በኃላ የመጀመሪያው ሰማዕት እርሱ ስለሆነ ነው፤ ሊቀ ዲያቆናት ያሰኘው ቅሉ በሐዋርያት ስራ 6፤5 ከተመረጡት 7 ዲያቆናት አለቃቸው ስለሆነ ነው። አይሁድ አማጽያን ሊሞግቱት በሸንጎ ተሰበሰቡ መጽሐፍ እንደመሰከረው እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም ይላል፤ “አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሮአችሁም ያልተገረዘ” ብሎ በግልጽ ዘለፋቸው ስለ ጌታችን መሰከረ በዚህም ተቆጡ ድንጋይ ጨበጡ በግፍ ገደሉት ይቅር በላቸው እያለ ነፍሱን ሰጠ፤ ጥቅምት 17 ይህን ቀን የሰማዕቱ ታቦት በሚገኝበት ሁሉ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 15


በጥቅምት 15 ቀን መታሠቢያቸው የሆኑ ቅዱሳኖች እናስተዋውቆት::ቅዱስ ዺላሞን ሰማዕት:ቅዱስ አርሞቅስ እረፍት:ዻውሎስን ይረዳው የነበረው ሲላስ በዓለ እረፍታቸው:ቅዱስ ሰላትዮን:ቅዱስ ኢጥራኩስ:ቅዱስ ኢናፍር:ቅዱስ ኢዲራኒቆስ:ቅዱስ አርሞሊስ:ቅዱስ አድማንያ:ቅዱስ አርሚስ እነዚህ ታሪካቸው የሌለ መታሠቢያቸው: አዝቂርና:ኪርያቅ:ታላቁ አባት የተባለው ኢሳያስ:ቅዱስ ሚናስ:ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስና:ቅድስት ለባሲተ ክርስቶስ ወርሀዊ መታሠቢያ በዓላቸው ነው::ምንጭ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ 36ቱ ቅድሳት አንስት ከሚለው መጽሀፍትና:ነገረ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ ይቆየን::
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 14



ጥቅምት 14
ቤተክርስቲያን የ 3 ታላላቅ አባቶችን መታሰቢያ ታከብራለች፤አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው ደብረ ዳሞ ላይ በፍጹም ተጋድሎ ኖረው ለኢትዮጵያ ብርሃን ሆነው በ 99 ዓመት ከ 3 ቀናቸው ተሰወሩ፤የአቡነ አረጋዊ እናት ንግስት እድና ንግስናዋን ትታ ልጇን ተከትላ መጥታ ደብረ ዳሞ ተራራው ስር በ89 ዓመቷ አርፋለች፤ ሁለተኛው ጻድቅ መናኙ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ነው እርሱም የንጉስ ልጅ ነው፤ከጫጉላ ቤት ጠፍቶ መነነ፤ አባቱ ወታደሮችን ላከበት፤ ገብረ ክርስቶስ ሌት ተቀን ተጉዞ የእመቤታችንን ደብር አገኘ ተንበርክኮም እመቤቴ ወታደሮች እንዳይዙኝ መልኬን ቀይሪሊኝ አላት የውስጥ ሰውነቱ ተገለበጠ በቁስልም የተመታ ሆነ ደጀ ሰላሙ ላይ ምጽዋት ከሚለምኑ ድሆች ጋር ተቀመጠ ወታደሮቹ ደረሱበት አላወቁትም ምጽዋት ሰጥተውት ያልፋሉ፤ በዚያች በቤተክርስቲያን 15 ዓመት በተጋድሎ ኖረ ከዚያም ወደ አገሩ ተመልሶ በአባቱ ደጅ 15 ዓመት ወድቆ ለመነ፤ አባቱ ለአሸከሮቹ እንዲህ አለ ይህንን ደሃ ምጽዋት ስጡት ልጄ ምናልባት ልክ እንደዚህ ደሃ በሰው አገር እየተንከራተተ ይሆናልና አላቸው፤ የአባቱ አሸከሮች ግን የእጅ እጣቢ፤ሽንት ይደፉበት ነበር በላዩ ላይ አጥንት እየወረወሩ ውሾች እንዲጣሉበት ያደርጉ ነበር፤ በእንዲህ ያለ ተጋድሎ 15 ዓመት ኖረ፤የእረፍቱ ቀን ሲደርስ የንጉሱ የቴዎድዮስ ልጅ መሆኑን የደረሰበትን ሁሉ መከራ ጽፎ ይሞታል፤ሊቀብሩት ሲሰበሰቡ ይህችን ጽሁፍ ያገኛሉ፤ አባትና እናቱ መሪር ለቀሶ አለቀሱ አገሩ በሙሉ አለቀሰለት ከበድኑ ገራሚ ገራሚ ተአምራት ተገለጹ ድውያን ሁሉ ተፈወሱ፤በታላቅ ክብርም ቀበሩት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን፤ ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን የኢትዮጰያዊቷ ንግስት ህንደኬ በጀሮንዷ የሆነውን ጀንደረባውን ያጠመቀው ታሪኩ በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 8፤27 ላይ ተገልጾ የሚገኘው ሐዋርያው ፊሊጰስ ያረፈበት ቀን ነው፤ይህ ሐዋርያ ከ 72ቱ አርድእት አንዱ ነው። የአባቶቻችን በረከታቸው ይደርብን።
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 12

ወበዛቲ ዕለት...
ጥቅምት 12 በዚህች ቀን አባ ዲሜጥሮስ አረፈ፤ይህ አባት ያልተማረ ገበሬ ነበረ ይላል ስንክሳሩ፤ እንዲህም ሆነ በዚያን ወቅት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ዩልያኖስ የእረፍቱ ቀን ሲደርስ የታዘዘ መልአክ ተገልጾ ዛሬ የወይን ዘለላ ይዞ የሚመጣ ምዕመን አለ፤ ካንተ በኃላ ሊቀ ጳጳስ የሚሆነው እርሱ ነውና ተቀበለው ይለዋል፤ ዲሜጥሮስ ወደ ተክል ቦታው ሲገባ ያ
ለወቅቱ ያፈራ ወይን ያገኛል በጣም ተገርሞ ይህንንማ ለሊቀ ጳጳሱ ነው የምሰጠው ብሎ ይዞ ይሄዳል፤ አባ ዩልያኖስ መልአኩ የነገረውን ተረዳ እንደተባለውም አደረገ፤ አባ ዲሜጥሮስ ከሹመቱ በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በርካታ መጽሀፍትን ደረሰ ከነዚህም ዋንኛው የአጽዋማትንና የበዓላትን ቀን የሚደነግገው ባህረ ሐሳብ የተሰኘው ግሩም መጽሀፍ አንዱ ነው። የሚገርመው ይህ አባት ከብቃቱ የተነሳ የሰዎችን ኃጢያት ያይ ነበር ሊቆርቡ ሲመጡ አንተ አልበቃህም ንስሀ ግባ አንተ በቅተሃል እያለ ያቆርብ ነበር፤ በዚህም ገሚሶቹ ጠሉት ፤ እርሱ ደግሞ ማነውና ጳጳስ ድንግል መሆን ሲገባው ሚስት አግብቶ እየኖረ የአባቶቻችንን ወንበር አረከሰ ብለውም አሙት፤ በዚህም የታዘዘ መልአክ ተገልጾ እራስህን ግለጽላቸው ይለዋል፤ እንደተባለውም ህዝቡ የደመራ እንጨት ይዞ እንዲመጣና ያመጣውን እንጨት እንዲነድ ያደርጋል፤ በሚነድ እሳት ውስጥም ገብቶ ለረጅም ጊዜ ይቆማል ሚስቱንም ይጠራታል እርሷም እሳት ውስጥ ትገባለች ፍሙን እያነሳ ይሰጣታል በቀሚሷ ትቀበለዋለች፤ የአገሬው ህዝብ ይህንን አይቶ እጹብ እጹብ አለ ምስጉን እግዚያብሔርንም አመሰገነ። ከእሳቱ ወጥቶ እንዲህ ይላቸዋል እኔ ይህን ያደረኩት ውዳሴ ከንቱ ሽቼ አይደለም በሐሜት እንዳትጎዱ ብዬ እንጂ ይህቺ የአጎቴ ልጅ ነች ከተጋባን 48 ዓመታችን ነው አንድ አልጋ ላይ እንተኛለን በግብረ ስጋ አንተዋወቅም ሁለታችንም ድንግል ነን አላቸው፤ ህዝቡ ተንበርክኮ ይቅርታ ጠይቆታል፡፡ አባ ዲሜጥሮስ ሸምግሎ ሳለ ህዝቡ በአልጋ ተሸክሞት ቤተክርስቲያን እየወሰደው እስኪመሽ አልጋ ላይ ተኝቶ ያስተምር ነበር፤ በንጽህና በቅድስና ኖሮ በ 107 ዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን አርፏል። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ወንጌልን የጻፈልን ሐዋርያው ማቴዎስ የእረፍት ቀኑ ነው፤ይህ ሐዋርያ ኢትዮጰያ መጥቶ ወንጌልን እንደሰበከ በርካታ መጽሐፍት ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፤ የመልአክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ዳዊትን ቀብቶ እንዲያነግሰው ወደ ሳሙኤል የተላከበት ቀን ነው፡፡ የመልአኩንም የቅዱሳኑን በረከት ያድለን፡፡

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ስለምን ቤተክርስቲያን እንሳለማለን ? ስለምን እንሰግዳለን?



ስለምን ቤተክርስቲያን እንሳለማለን ? ስለምን እንሰግዳለን?

ሰላም ለኪ ቅድስት ቤተክርስቲያን አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት፡፡

ሁልጊዜም እንደምንለው ቤተክርስቲያናችን ሁሉን በማስረጃ ታደርጋለች እንጂ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት በተረት አይደለም አሁንም በዚህ ርዕስ ዙሪያ ጥያቄ ለሚያነሱ ይህንን ምላሽ እንሰጣለን ነገር ግን ስለመማማር ነው እንጂ ስለክርክር አይደለም፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን በሕንጻ ቤተ እግዚአብሔር ተገኝተን እንሳለማለን፣እንሰግዳለን ይኸውም ለባለቤቱ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ለመግለጽ እንጂ የምናመልከው ማንን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

የመሳለማችን ወይም የመስገዳችን ምስጢር በቤተ እግዚአብሔር ፊት ስለሆነ የምንሰግደው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሕንጻው ወይም ለድንጋዩ አይደለም ይህንንም በማስረጃ እናስረዳለን፡-

"ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳን ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር ሕዝቡም ሁሉ ተነስቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር፡፡"(ዘፀ. 33፡10)
እንግዲህ ለድንኳን አንሰግድም አላሉም በዛ ቤት፣ በዛ ድንኳን ለከበረው ለእግዚአብሔር ሰገዱ እንጂ

"ሰሎሞንም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወረደ የሚቃጠለውን መስዋዕትና ሌላ መስዋዕቱን በላ የእግዚአብሔርም ክብር ቤቱን ሞላ፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ወደ እግዚአብሔር ቤት መግባት አልቻሉም፡፡ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እሳቱ ሲወርድ የእግዚአብሔርም ክብር በቤቱ ላይ ሲሆን ያዩ ነበር በወለሉም ላይ በግምባራቸው ወደ ምድር ተደፍተው ሰገዱ፡፡ እርሱ መልካም ነውና ምህረቱም ለዘላለም ነውና ብለው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡"(2ኛ ዜና.7፡1-3)
በግልጽ እንደተረዳን ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ናትና በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን እንሰግዳለን፡፡

"ዳዊትም ከምድር ተነስቶ ታጠበ ተቀባም ልብሱንም ለወጠ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ፡፡"(2ኛ ሳሙ.12፡20)
ከቅዱስ ዳዊትም እንደተማርነው እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ እንደፈቃዱ ሆነ ብለን በተቀበልን ጊዜ ተነስተን፣ ለቤተክርስቲያን የሚገባ ልብስ ለብሰን ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ ልንሳለምና ልንሰግድ ይገባል፡፡

" እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤት እገባለሁ አንተንም በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ፡፡"(መዝ. 5፡7)
"የስሙን ክብር ለእግዚአብሔር አምጡ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፡፡"(መዝ. 28(29)፡2)

ታዲያ ይህ የቅድስና ስፍራ ቅድስት ቤተክርስቲያን አይደለምን ዳግመኛም እንዲህ ተናገረን፡-

"በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ፡፡"(መዝ. 95(96)፡9 )
" በመላዕክት ፊት እዘምርልሃለሁ ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፡፡"(መዝ. 137(138)፡2)

እነግዲህ በዚህ ቃል ውስጥ ቅዱስ መቅደሱ ቤተክርስቲያን መሆኗን እንዴት መረዳት ያቅተናል?

" አለቃውም በስተውጭ ባለው በር በደጀ ሰላሙ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደህንነቱን መስዋዕት ያቅርቡ እርሱም በበሩ መድረክ ይስገድ፡፡"(ሕዝ.46፡1-2)

ከደጅ መባችንን ስናቀርብ በበሩ ላይ ተደፍተን የምንሰግደው ይህን መመሪያ አድርገን ነው ለቤተክርስቲያንም መስገዳችን በውስጡ ላደረ ለእግዚአብሔር መንፈስ መስገዳችን ነው፡፡

መናፍቃኑ ቤተክርስቲያን አያስፈልግም የእኛ ሰውነት ራሱ ቤተክርስቲያን ነው ይላሉ።??

እኛም እግዚአብሔር በሕንፅው ብቻ ይወሰናል አላልንም የአምልኮቱ ቤት ነዉ አልን እንጂ።እኛም ማድሪያዎቹ ነን!
ነገር ግን እንርሱ ስለሚቃወሙት ቤተመቅደስ ጌታ በወንጌል ላይ እንዲህ አለ፤-

"ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል "(ማቴ. 21:13 , ማር.11:17)

እንዲሁም እግዚአብሔር ኣምላክ አስቀድሞ ለሙሴ በመካክላችሁ አድር ዘንድ ቤተ ምቅደስ ስሩልኝ ስላለ በቤተ መቅደስ ተሰብስበን አምልኮ መፈፅም ስህተት አይድለም::

”በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ”(ዘጸ.25:8 )

” ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው”(ዘፍ.28:16)


አንዳንድ ሰዎች ቤተክርስቲያንን በእጃችን እያበስን ስንሳለም ሊገርማቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ እንደሆነ አድርገው ሊቆጥሩ ይችላሉ?

እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦
"ከድንኳኑ ጀምረህ በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳትን በሙሉ ቅብዓ ቅዱስ ወይም ሜሮን ቀባና ቀድሳቸው እነሱን የነካም ቅዱስ ይሆናል።" (ዘጸ.30:22)

እኛም የቤተክርስቲያንን ዘርፍ በእምነት የምንዳስሰው በዚህ ምክንያት ነው። 12 አመት ሙሉ ትደክም የነበረችው ሴት እምከመ ገሰስኩ ጽንፈ ልብሱ አሀዩ /በእምነት ሆኜ የልብሱን ዘርፍ ብዳስስ እፈወሳለሁ/ ብላ እንደዳነችው እኛም በእምነት የቤተክርስቲያንን ዘርፍ ብንዳስስ እንፈወሳለን። ጌታ የቤተክርስቲያን ራስ ነውና የልብሱ ዘርፍም ቤተክርስቲያን ናትና!!! ኤፌ.1:22
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ” እንደሚል የሐዋ. 20:28

ከሁሉ በላይ ደግሞ የቤተክርስቲያንን መኖር የምትቃወሙ ሆይ እግዚአብሔር ለእርሷ የገባውን ይህንን ታላቅ ቃል ስለምን አታስተውሉም የሰጣትን ክብር ስለምን ዘነጋችሁት?

"በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤ በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ፡፡"(1ኛነገ.9፡3 )

* እነሆ በመንገድ እየሄድህ ሳለ ቤተክርስቲያንን ብታያት ሰላምታ ትሰጣት ዘንድ ስለምን ታፍራለህ?

ወዳጄ እምነታችን አኮ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው! ሰላምታ ለቤተክርስትያን መስጠት ከሐዋርያት የተማርነው ነው፡፡ማስረጃ የሚጠይቀንም ቢኖር እነሆ:-

"ወደ ቂሳሪያም በደረሰ ጊዜ ወጥቶ ለቤተክርስቲያን ሰላምታ ከሰጠ በኋላ ወደ አንጾኪያ ወረደ፡፡" (የሐዋርያት ሥራ 18፡22)

እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ያደረገውን እናደርግ ዘንድ ስለምን እናፍራለን? እርሱ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ ብሎ ያስተማረን አይደለምን?

ለሁላችን ማስተዋልን ያድለን አሜን!!!

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ፡፡

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 6



ወበዛቲ ዕለት ... ጥቅምት 6

በዚህች ቀን ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ ጰንጠሌዎን አረፉ፤ እኚህ ጻድቅ ልክ እንደነ አቡነ አረጋዊ ከሮም ከነገስታት ወገን ናቸው መንግስታቸውን ክብራቸውን ትተው ወደ ኢትዮጰያ መጡ ለጥቂት ጊዜ ዘጠኙም አብረው ኖሩ ከዚያ በኋላ ለየብቻ መኖር ይሻለናል ብለው ሁሉም ተበታተኑ አቡነ አረጋዊ ወደ ደብረ ዳሞ አቡነ ገሪማ ወደ መደራ ሌሎችም በየአቅጣጫው ሄዱ እኚህ አቡነ ጰንጠሌዎን ደግሞ አክሱም አቅራቢያ ተራራ ላይ ወጥተው የራሳቸውን ገዳም አበጁ ርዝመቱ 5 አግድመቱ 2 ስፋቱ 3 ክንድ ነው በር የለውም ቀዳዳ እንጂ በዚህ ገዳም ውስጥ ሳይቀመጡ ሳይተኙ ያለመብልና መጠጥ ቆዳቸው ከአጥንታቸው እስኪጣበቅ 45 ዓመት በተጋድሎ ኖረዋል፤ ብዙ በሽተኞች ወደ እርሳቸው እየመጡ ይፈወሱ ነበር። አጼ ካሌብ በየመን ናግራን ክርስቲያኖችን ነጻ ለማውጣት ሲዘምቱ እኚህ አባት ጋር መጥተው ተባርከው ዘመቱ ድል አድርገው ሲመለሱም መንግስቴን አልፈልግም ብለው በእኚሁ አባት እጅ ነው የመነኮሱት። አቡነ ጰንጠሌዎን የእረፍት ቀናቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦ በርካታ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል ጥቅምት 6 ቀንም አርፈዋል፤ ዛሬ ገዳማቸው የበረከት ቦታ ብቻ ሳይሆን የቱሪስትም መስህብ ነው። ከጻድቁ በረከት ያሳትፈን
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 5



አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ (ግብጽ ) ነው :: አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌያስ ይባላሉ :: ልጅ አጥተው 30 ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል ::

አንድ ቀን አቅለያስ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከስዕለ ስላሴ ስር ወድቃ ስትማጸን "" ንስኢ ወልደ ዘይትሌአል ቅርኑ አምኑኅ ሰማይ ... ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበልጥ ልጅ እንኪ ተቀበዪ "" የሚል ድምጽ ሰማች :: በዚህም መሰረት አባታችን መጋቢት 29 ቀን ተጸንሰው ታህሳስ 29 ቀን ተወለዱ ::

አይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ አፈፍ ብለው ተነስተው "" ስብሐት ለአብ , ስብሐት ለወልድ , ስብሐት ለመንፈስቅዱስ ዘአውጻእከኒ እምጽልመት ውስተ ብርሐን >> ብለው በማመስገናቸውና ሀላም ምድራዊ መብል እና መጠጥ ሳይመገቡ : ሳይጠጡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መልአክትን ይመስላሉ

ሶስት አመት ሲሆናቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእመቤታችንና በገነት ካሉ ቅዱሳን ዘንድ አስባርኮ ገዳማውያን ካሉበት ምኔት ወስዶ ከበሩ አኖራቸው :: አበመኔቱም አባ ዘመድብርሐን ምልክት ተነግሮት ቢሄድ ፍሱሐ ገጽ ሆነ አግኝተዋቸዋል :: አበመኔቱም አሳድጎ አስተምሮ ከመአረገ ምንኩስና አድርሰዋቸዋል ::

ከዚህ ቡሐላ ሐብተ ፈውስ ተሰጥቷቸውል :: በአንድ ቀን እልፍ እውራንን እና እልፍ አንካሳ ፈውሰዋል :: በዋላ ግን ኤጲስ ቆጶሳትና ካህናቱ ዝናቸውን ሰምተው እየመጡ ግብር የሚያስፈቱአቸው ቢሆን ቅዱስ ገብርኤል ነጥቆ ከጌታ ፊት አቀረባቸው ::

በገድለህ : በትሩፋትህ : ከሞት ነፍስ ክርደት ገሀነም የሚድኑ ብዙ አሉና ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ግባ :: ኑሮህም ከስልሳ አናብስትና ከስልሳ አናብርት ጋር ይሁን አለው :: ጌታዬ ምን ተመግበው ይኖራሉ አሉት ? "ዘኬድከ ጸበለ - እግረከ ይልህሱ ወበ ውእቱ ይጽግቡ ... የረገጥከውን ትቢያ ልሰው ያ ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ :: ብሏቸው ውሳጤ ገዳም ገብተው : ከአናብስትና ከአናብርት ጋር ይኖሩ ጀመሩ :: ዳንኤል ከአናብስት ጉድጉዋድ በተጣለ ጊዜ አናብስቱ እንደ ድመት ከእግሩ በታች ሆነው እንደተገኙ : አባታችን የረገጡትን ትቢያ እየላሱ እየታዘዙዋቸው ይኖሩ ነበር :

በዚህ መልኩ 30 አመት ከቆዩ ቡሐላ ጌታ በአንድነት በሶስትነት ተገልጾ ምን ላደርግልህ ትሻለህ ? አላቸው :: መጀመሪያ ላሉበት መጸለይ ይገባልና የምድር ገቦታን ሰዎች ማርልኝ አሉት :: 3000 ሐጥአንን ከሲኦል አውጥቶ ገነት አግብቶላቸዋል :: ከዚህ ቡሐላ ሁር ምድረ ኢትዮጵያ ወበህኒ አልውከ ነፍሳት ወታወጽኦሙ .... ወደ ኢትዮጵያ ሂድ አላቸው :: ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ ነፍስ ጭኖ ምድረ ከብድ አድርሷቸዋል :: ዳግመኛም ወደ ዝቁዋላ (ደብረቅዱስ ) ወስዷቸው ከዚያ ሆነው በንጹሀ ልቦና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሐጢያት ከባህሩ ውስጥ ራሳቸውን ዘቅዝቀው ለ 100 አመት ይጽልዩ ነበር :: 40 ቀን ሲሆናቸው መልአኩ መጥቶ ዘገብረ ተዝካርከ ወዘጽውአ ስምከ እምህር ለከ ብሎሀል አላቸው :: እሳቸው ግን መላ ኢትዮጵያን ካልማረልኝ ከባህሩ አልወጣም ብለው 100 አመት በባህሩ ውስጥ በጭንቅላታቸው ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖረዋል :: ከ 100 አመት ቡሐላ ጌታ ተንስእ ወጽእ መሀርኩ ለከ ኩሎ ኢትዮጵያ ... ምሬልሀለው ውጣ ብሏቸው ወጥተዋል ::

ከዚህ ቡሐላ ምድረ ከብድ ወርደው ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ሆነው 7አመት እንደ ትኩል አምድ ሆነው አይናቸውን ሳይከድኑ 7 አመት ሙሉ አይናቸውን ሳይከድኑ ቆመው ጸልየዋል :: ሰይጣን ግን ለምቀኝነት አያርፍምና ቁራ መስሎ መጥቶ አይናቸውን አንቁሮ አሳወራቸው :: 2 ሱባኤ ሲፈጽሙ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው እፍፍ ብለው አድነዋቸዋል :: ከዚያ ተነስተው ወደ ዝቁዋላ ሲሄዱ ስላሴን በአምሳሌ አረጋውያን ከጥላው ስር አርፈው አገኙዋቸው :: በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነንሀል አዝለክ አንድ አንድ ምህራፍ ሸኘን አሉዋቸው :: አዝለው ከሸኙዋቸው ቡሐላ በአንድነት በሶስትነት ሆኖ ታያቸው :: ድንግጠው ወደቁ : እግዚአብሔር ግን አንስቷቸው ሂድ ዝቁዋላ ሄደህ ጠላቶችህን ተበቀላቸው አላቸው :: በዛበነ መብረቅ ደርሰው 7 ቱን ሊቃነ መላእክት አጋዥ አድርገው እልፍ አእላፍ አጋንንትን አጭደዋል ::

ጻድቁ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍታቸው መጋቢት 5 ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 15 ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ ስለዚህም ወደ ጥቅምት 5 ቀን ተዛውሮ እንዲከበር የመጋቢት 27 ስቅለት ደግሞ ጥቅምት 27 ቀን እንዲከበር ተደረገ፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይህ ስርዓት ሆነ፤


ምንጭ ገድለ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ተአምር 14 


ጥቅምት 4

ጥቅምት 4
በዚህች ቀን የኢትዮጵያ ባለውለታዎች፤ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ እንድትሆን ትልቁን ድርሻ ያበረከቱ አብርሃና አፅብሃ የእረፍት ቀናቸው ነው፤እነዚህ ሁለት ጻድቅ ነገስታት ወንድማማች ሲሆኑ የክርስትና እምነትን በኢትዮጽያ ያበሩ አማናዊ ጥምቀትንና ቁርባን ያስጀመሩ ከመሆናቸው ባሻገር ከ 154 በላይ አብያተክርቲያናት አንጸዋል፤ ከነዚህም በተለይ ዋንኞቹ ትግራይ ውስጥ ገልአርታ ቀመር አርብአቱ እንስሳ፤ጋሞ ጎፋ ብርብር ማርያም፤ጎጃም መርጡለማርያምና ዲማ ጊዮርጊስ፤ የብሐ ጊዮርጊስ ከፋ፤የዋሻ ሚካኤል ሰላሌ፤ የጀንባ ሚካኤል ሰማዳ፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ የካ ሚካኤልንና የረር በዓታ ተጠቃሽ ናቸው። ከሁሉም በላይ ዓለም ዛሬም ድረስ የሚገረምባቸውን የአክሱም ሀውልቶች ያቆሙ ናቸው፤ 33 ሜትር ተኩል ድንጋይን ከየት አመጡት እንዴትስ ቀረጹት እንዴትስ ብለው አቆሙት ይህ የእግዚያብሔር ተአምር ነው እንጂ፤ እኛስ እጹብ ግሩም ብቻ ብለን እናልፋለን። በኢትዮ ከነገሱ ከጥንት ነገስታት እንደ አብርሃና አጽብሃ በርካታ ታሪክን አኑሮልን ያለፈ ንጉስ የለም ብንል አልተሳሳትንም፤ እነዚህ ቅዱሳን የኢትዮጵያን ድንበር አስፍተው ክርስትናን አጽንተው ያስረከቡን ዋኖቻችን ናቸው፤ሁለቱም በተለያየ ዓመተ ምህረት ጥር 4 ቀን አርፈዋል፤ኢትዮጰያ ውስጥ በስማቸው ሰባት ቤተክርስቲያን እንዳላቸው ሊቀ ብርሃናት መርቆሪዎስ አረጋ የቅዱሳን ታሪክ በሚለው መጽሀፋቸው ጠቅሰውታል፤ ጥር 4 ቀን በተለይ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በደማቁ ተከብረው ይውላሉ። በረከታቸው ይደርብን። 

ጥቅምት 3

ጥቅምት 3ቀን መታሠቢያቸው የሆኑ ቅዱሳኖች እናስተዋውቆት:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የቅዱሱና የንጉስ ላሊበላ ወንድም ልጅ ነው:አቡነ ዜና ማርቆስ ዘጽልላሽ ዞረሬ:አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘትግራይ አዲግራት:አቡነ ፍሬ ካህን ዘትግራይ ተንቤን:እነዚ ከላይ የተጠቀሱ ሁሉ ኢትዮዽያውያን ናቸው:መጋቢ ብሉይ ቅዱስ ፋኑኤልና:እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት:አባ ሊባኖስ ዘሮም ዘመጣዕ:አባ ስምኦን ሊቀ ዻዻስ:ቅድስት ማርያም የአላዘር እህት:ቅድስት ታኦድራ : ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ ልደቱ: ወርሀዊ መታሠቢያ በዓላቸው ሲሆን: ሀዲስ ጊዮርጊስ የተባለው ሰማዕት እረፍቱ
LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 2

በዚህች ቀን ደገኛው አባት አባ ህርያቆስ አረፈ። ይህ አባት ትውልዱ ብህንሳ ነው፤አልተማረም ግን በትሩፋት የጸና ደገኛ አባት ነው፤ የገዳሙ አበ ምኔትም ነበር፤ ልክ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የእመቤቴ ምስጋናዋ እንደ ባህር አሸዋ እንደ ሰማይ ኮከብ በዝቶልኝ እንደ ምግብ ተመግቤው እንደ መጠጥ ጠጥቼው እንደ ልብስ ለብሼው በኖርኩኝ እያለ ይመኝ ነበር። በብህንሳ ያሉ አብዛኞቹ መኖኮሳት ይጠሉት ይንቁት ነበር ምነዋ ቢሉ ስርዓት ያጸናባቸው ነበር፤ከዕለታት በአንዱ ቀን በምን እንሻረው ብለው አሰቡ አስበውም አልቀሩም ቀድሰህ አቁርበን አሉት፤እመቤታችንን አደራ እንዳታሳፍሪኝ ብሎ ሊቀድስ ገባ፤ የለመኗትን የማትነሰ እመቤታችን አዲስ እንግዳ ድርሰት ገለጸችለት ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ ልቦናዬ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ ወይእዜኒ ንሰብሖ እስከሚለው ድረሰ ሰተት አድርጎ ተናገረ፤ በዙሪያው ያሉት የሚወዱት መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እንዲህ ያለ ሚስጢር ከሩቅ ብእሲ አይገኝም አሉ፤ ገሚሶቹ የሚጠሉት ደግሞ አናናቁበት በዚህም ተከራከሩ ጽፈው ደጉሰው ከህሙም ላይ ጣሉት ድውይ ፈወሰ ይልቁንም ሙት አስነስቷል። 14ኛ ቅዳሴ አድርገው ይዘውታል። አባ ህርያቆስ ከአቡነ አረጋዊ ጋር ሆነው በርካታ መጽሐፍትን ይዘው ወደ ኢትዮጰያ እንደመጡ ህዝቡንም እንዳስተማሩ የጥር ድርሳነ ኡራኤል ላይ ተጽፎ ይገኛል፤ በድጋሚ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እመቤታች አዛቸው አክሱም መጥተው ከቅዱስ ያሬድ ጋር ተገናኝተዋል አንተ ቅዳሴየን አንተ ደግሞ ውዳሴየን ነግራቹት በዜማ ያድርስ ብላቸው እነሱም ነግረውት አድርሶታል፤ አባ ህርያቆስ በንጽህና በቅድስና ኖሮ ጥቅምት በባተ በሁለተኛው ቀን በክብር አረፈ፤ የዚህ ደገኛ አባት በረከት ይደርብን።
LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

ጥቅምት 1


በጥቅምት 1 ቀን መታሠቢያቸው የሆኑ ቅዱሳኖች እናስተዋውቆት:: የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት መታሠቢያ:አቡነ ቆውስጦስ ልደት መታሠቢያ :ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ቀናኢ ለአምላክ ልደት መታሠቢያ : አባታችን እዮብ:ቅድስት አንስጣስያ:የቅድስት ሶስና:የቅድስት ሕርጣን መታሠቢያ በዓልና:የቅዱስ ራጉኤል ሹመት መታሠቢያ በዓል ነው::ምንጭ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ 36ቱ ቅድሳት አንስት ከሚለው መጽሐፍ
LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

መስከረም 29



የቅድስት አርሴማ እናት አትኖስያ ትባላለች ልጅ በማጣት ለረጅም ዘመን ታዝን ታለቅስ ነበር በኃላም እግዚያብሔር ልመናዋን ሰማት ይህችን ክብርት ቅድስት ልጅንም ሰጣት፤ቅድስት አርሴማ ጥር 6 ነው የተወለደችው፤15 ዓመት ሲሆናት ሊያጋቡአት አሰቡ እርሷ ግን ይህን አልወደደችም፤ በደናግል ገዳም ገብታ በተጋድሎ መኖር ጀመረች። ከዚህ በኃላ እንዲህ ሆነ ከሃዲው ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ሊያገባት ወደደ ቅድስት አርሴማ ግን ከደናግሉ ጋር ሸሽታ ወደ አርማንያ ሄደች በዚያም በበርሃ ለጥቂት ቀናት ተቀመጠች በኃላ ላይ ድርጣድስ የሚባል አገር ገዢ በበርሃ እንደሚኖሩ ሰማ ወታደሮችንም ልኮ አስመጣቸው፤ የቅድስት አርሴማን መልክ በተመለከተ ጊዜ ፈዞ ደንዝዞ ቀረ የፊቷ ውበት እጹብ ድንቅ፤ ግርማዋ የሚያስደነግጥ ልብ የሚያርድ ነበርና፤ስለዚህም ሊያሰቃያት አልደፈረም በእንክብካቤ በሰገነት ላይ አኖራት፤ ሌሎቹን ግን ለጣአት እንዲሰግዱ ገረፋቸው፤ ቅድስት አርሴማ እኔንም አሰቃዩኝ እያለች አምርራ ታለቀስ ነበር። ድርጣድስ ብዙ ጊዜ ሊሸነግላት ሞከረ እርሷ ግን ትዘልፈው ጣኦታቱንም ትረግም ነበር፤ እርሷ ጸንታ ደናግሉን ታጸና ነበር ትመክራቸው ታረጋጋቸው ነበር፤ ድርጣድስ ሽንገላው እንደማያዋጠው በአወቀ ጊዜ ማሰቃየት ጀመረ፤ በመጨረሻም ከብዙ ስቃይ በኃላ መስከረም 29 ቀን አንገቷን ቆረጣት ከእረሷ ጋር 27 ሰማዕታት አብረው ተሰይፈዋል። በአገራችን በስሟ ሰሜን ወሎ ውስጥ ሲሪንቃ ቅድስት አርሴማ የሚያስገርም ገዳም አላት፤በዚህ ገዳም ሰባት ቀን ብቻ ሱባዬ የሚገባ የልቡን መሻት ትፈጽምለታለች፤በመዲናችን አዲስ አበባም የቅድስት አርሰሴማ ቤተክርስቲያኖች አሉ አንዱም አስኮ ቃሎ ተራራ ላይ የሚያስገርም ቤተክርስቲያን አላት ይህንን የቃሎ ተራራ ሲወጡ ዝቋላ አቦ ትዝ ይላል፤ መስከረም 29 በደማቁ ታቦተ ህጉ ወጥቶ ተከብሮ ይውላል። ከሰማዕቷ በረከት ያድለን። ታህሳስ 6 ፍልሰተ አጽሟ ነው።

LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

መስከረም 23



በመስከረም 23 ቀን መታሠቢያቸው የሆኑ ቅዱሳን ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዳዊ:አባ ተጠምቀ መድህን ዘጎጃም ኢንብሳ የጏሕንቻ ማርያም ወንዶችና:የጋሾላ ቅ/ጊዮርጊስ ሴቶች ገዳም የመሠረቱና:ጻድቁ ዮስጣቲዎስ ወርሐዊ መታሠቢያ በዓላቸው:የሐዋርያው እንድርያስ ልደቱና:ቅዱስ ዮልያኖስ ሰማእት:ቅዱስ አናብዮስ ሰማእት አመታዊ መታሠቢያ በዓላቸው ነው:ምንጭ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ 36ቱ ቅድሳት አንስት ከሚለው መጽሐፍት

Tuesday, October 1, 2013

እንኳን አደረሳችሁ መስከረም 21

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ - የግማደ መስቀሉ መገኛ

ግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፤ በደላንታ፤ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ በበጌምድር እንደዙር አምባ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት ፡፡

ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሐ አቋርጦ በሸሎን በመሻገር ፫ ሰዓት መንገድ አቀበት በመውጣት አንድ ቀን ሙሉ ተጉዞ ማታ ፲፪ ሰዓት ይገባል ፡፡ግሸን ማርያም በፊት ደብረ እግዚአብሔር ትባል ነበር ፡፡ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች ፡፡

ከዚያም በ ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡

የግማደ መስቀሉ መምጣት ታሪክ

ዓለምንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ፍጡር ፈጥሮ የሚገዛውን አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤተ እሥራኤል በቀራንዮ ላይ በመስቀል ሰቀሉት ፡፡ መድኃኔዓለም በዕለተ ዓርብ ከቀኔ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየ በኋላ በኋላ ከመስቀሉ አውርደው ቀበሩት ፡፡በ፫ኛው ቀን ሲነሣ ተሰቅሎ የነበረው የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደፀሐይ ሲያበራ በተጨማሪም አጋንንት ሲያባርር ድውይ ሲፈውስ ሙት ሲያነሣ ቤተ እሥራኤል አይሁድ ቀንተው በዓዋጅ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ ጠቅላላ የቆሻሻ መከማቻ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ ከዚያ ዘመን ጀመሮ እስከ ሦስት መቶ ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደተራራ ሆነ፡፡
ከዚያ በኋላ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ ንግሥት የተባለች ደግ ሴት የክርስቶስን መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳ ዓ.ም. ላይ በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህ መስቀልም ከዚያ ዘመን ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራትን እየሠራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምዕመናን የሮማውን ንጉሥ ሕርቃልን ዕርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርገው በኢየሩሳሌም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ እወስድ እኔ እወስድ እያሉ ጠብ ፈጠሩ፡፡

በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ፤ የቁስጥንጥንያ ፤ የአንጾኪያ ፤ የኤፌሶን ፤ የአርማንያ ፤ የግሪክ ፤ የእስክንድርያ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚህም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስ መስቀል ከ፬ ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡
ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁት” ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ፳ ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞች ላኩ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ላኩ ፡፡የንጉሡ መልዕክት ለእስላሞች እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ፀንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡
መታረቃቸውን ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ በጣም ደስ አላቸው እገዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብፅ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልከተው ደስ ኣላቸው ፤ ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡

በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት ወርቅ የብርና የንሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቡአቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት ይህም የሆነው መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ታለቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርአ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ሥናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማቸው አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል ወዳጄ ዘርአ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ ፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ ከብዙ ቦታ ላይ አስቀምጠውት ነበር ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም ፤ በመናገሻ ማርያም ፤ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ያላገኙ በመሆኑ በራዕይ እየደጋገገመ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡

ዓፄ ዘርአያዕቆብም ለ፯ ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ በዚያም የተገለፀላቸው መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል አላቸው እርሳቸው ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል መርቶ አደረሳቸው ፡፡በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው ፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡
ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር
ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳው
ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ
ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል
ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ስዕሎች
የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር
የዮርዳኖስ ውሃ
በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ነው፡፡ የነዚህንም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሼን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩ ሺ ፬፻፵ ዓ.ም. ላይ ተናገሩ ፡፡በመጀመሪያም ይህ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ነው ወደ ኢትዮጵያም የገባው በመስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ አሁንም በመጨረሻ ግሸን አምባ የገባው መስከረም ፳፩ ቀን ሲሆን ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና አፄ ዘርዓያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በፅሑፍ በመዘርዘር የገለፁበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡
ስለዚህ ከዚህች በግሸን ደብር የክርስትና እምነት ያላቸው የኢትዮጵያ ምእመናን ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማገኘት በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን እየመጡ ያከብራሉ፡፡ በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የነበሩት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምህረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ በሱባዔአቸውም በመጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን በዚች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች ጠለ ምህረቴንም አይለይባትም ፤ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ መጥቶ የተቀበረ ኢየሩሳሌም እንደተቀበረ ይሁን የሚል የምህረት ቃል ኪዳን ተገልጾላቸው በዚህ ለተገኙት ምዕመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋያተ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ጤፉት ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለግሸን እግዚአብሔር አብ ሰጡ፡፡
አፄ አርዓ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እሌኒ እኅታቸው የተሰኘችው በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብም ይህችን ደብር ደብረ ከርቤ ብለው በመሰየም እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ ፤ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሀሏ ገነት ትሁን ብለው ደንብና ሥርዓት በጤፉት መጽሐፍ ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የተሾሙ ጳጳሳት መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትንና መጻሕፍትን የወርቅንና የብርን ሰን ፤ ብርና ጻሕል ጽዋን መስቀልን የመሳሰሉትን የሰጧት ምዕመናንም በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዓመት ወደ ዓመት እየበረከቱ ሔደዋል፡፡

በመስከረም 10 ፤ መስከረም 17 በዓለ መስቀል እና መስከረም 21 የግሸን በዓል ታሪክ ከረጅም በአጭሩ ይህንን ይመስላል ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ምዕመናን የሆናችሁ ሁሉ ከበረከተ መስቀሉ ለመሳተፍ ወደ ግሸን ገሥግሱ፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን
አሜን
መልካም በዓል


ትንሣኤ መጽሔት
መለከት መጽሔት

LIKE >>> https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን
/117298008428339?ref=hl