Thursday, October 31, 2013

ጥቅምት 22



ጥቅምት 22

በዚህች ቀን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አረፈ፤ የሉቃስ ወንጌልንና የሐዋርያት ስራን የጻፈልን አባት ነው፤ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድዕት ነው፤ቀድሞ ዶክተር ነበር መድሐኒት ቀምሞ የስጋ በሽታን የሚፈውስ በኃላ ግን ወንጌልን ሰብኮ የነፍስ ቁስልን የሚፈውስ ሆኗል፤ ወንጌሉን መቼ ጻፈው ቢሉ ጌታ ባረገ በ 22 ዓመቱ የት ጻፈው መቄዶኒያ በምን ቋንቋ በዮናኒ፤ማቴዎስ በዕብራይስጥ፤ ማርቆስ በሮማይስጥ፤ ዮሐንስ በጽርዕ ቋንቋ ነው የጻፉት። ቅዱስ ሉቃስ መጀመሪያ ዮሐንስን ተከትሎ ወንጌል ሰበከ በኃላም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ሮም ሲሰብኩ ቅዱስ ጳውሎስ በኔሮን እጅ በሰማዕትነት ሞተ፤ ብቻውን እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ የክርስቲያኖች ቁጥር በዛ አብያተ ጣኦታትንም አፈራረሰ በዚህም ንጉሱ ተቆጣ ሸንጎ ፊት አቅርቦም፤ ወንጌልን የጻፈች እጅህ ይህች ነችን? ብሎ ቀኝ እጁን ቆረጠው፤ ቅዱስ ሉቃስም እየሱስ ክርስቶስ የተቆረጠ እጅ አይደለም የተቆረጠች ነፍስንም ይቀጥላል ብሎ በግራ እጁ የተቆረጠች እጁን አንስቶ እንደ ቀድሞ አደረጋት፤ በወንጌል ላይ ጌታችን የተቆረጠች የማልኮስን ጆሮ ወደ ቀደመ ቦታዋ እንደ መለሳት ልብ ይሏል፤በኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል ከኔም በላይ ያደርጋል ያለ ጌታ የታመነ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ያደረገውን ተአምር ተመልክተው 267 ወታደሮችና መኮንኑ በክርስቶስ አምነዋል፤ ንጉሱም በሰይፍ አስፈጅቷቸዋል፤ቅዱስ ሉቃስንም በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጦ በአሸዋ ከተሞላ ስልቻ ጋር አድርገው ወደ ባህር ጥለውታል፤ ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን፤

No comments:

Post a Comment