Tuesday, November 19, 2013

ቁስቋም - ህዳር 6

እንኳን እመቤታችን ከስደት ተመልሳ ቁስቋም የገባችበት በዓል ቀን በሰላም አደረሳችሁ

ህዳር 6
በዚህች ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ አንዲሁም ከዮሴፍና ሶሎሜ ጋር 3 ዓመት ከ 6 ወር በስደት ከተንገላታች በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱበት ቀን ነው፤ ከግብጽ ሲመለሱ ጌታችን በእመቤታችን ጀረባ ላይ ሆኖ እነዚያ እውራንን ባበሩ ጣቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ይጠቁም ያመለክት ነበር፤ እመቤታችንም ልጄ ሆይ ለምንድነው ጣትህን የምታመለክተው ብትለው "ያቺ የተባረከች አገር ናት እኔን የሚያመልኩ አንቺን የሚማልዱ በፍቅርሽ የነደዱ ቅዱሳን መነኮሳት የሚፈልቁባት አገር ናት፤ ያንቺ ዘመዶች ሰቅለው ይገድሉኛል በዚህች አገር ያሉ ግን ሳይዩኝ ያመኑኛል፤ አስራት በኩራትሽ ትሁን ብሎ ሰጥቷታል፡፡ በኪደተ እግራቸውም ጣና ሐይቅን፤ ዋልድባንና ሌሎችንም ቦታዎች ዞረው እንደባረኩ ድርሳነ ኡራኤልና ተአምረ ማርያም ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን በኢትዮጵያ ምድር ታላቅ አምድ ወደቀ ይህም የመናገሻው ባህታዊ አባ ኤልያስ ነው፤ በ 400 ዓመት እድሜው ህዳር 6 1874 ዓ/ም አረፈ፤ በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ማለት ነው፤ የቅርብ ጊዜ ነው፤ ይህ አባት በግራኝ መሐመድ ወረራ ጊዜ የነበረ ነው፤ በዚያን ጊዜ በተለይ ኦሮሞዎች "አያና ውቃቢ" እያሉ በጣም ያከብሩት ነበር፤ ከመናገሻ እንጦጦ ኪዳነምሕረት እየተመላለሰ ሱባኤ እየገባ ጸሎት ያደርግ ነበር፤ በዛሬዋ ቀን ይህ አባት ሲሞት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ከዋክብት ሲበታተኑ ሲራወጡ ታየ የተጉለቱ አባ በላይነህም ይህንን ምልክት አይቶ የአባ ኤልያስን መሞት ተረዱ ወደ መናገሻ ቢመጡ ሞቶ ተቀብሮ አገኙት፤ጎንደር ላይም በተመሳሳይ ከዋክብት ሲበታተኑ እነ አለቃ ወልደ ቂርቆስ በአይኔ አየሁ ሲሉ መስክረዋል ይላል መርስሄ ሐዘን ''ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው" በሚለው መጽሐፋቸው የከተቡልን። የሚገርመው ይህ አባት ከቤተመንግስት ወገን ሲሆን ተድላ ደስታን ንቆ 400 ዓመት በቅድስና በተጋድሎ የኖረ መናገሻንና እንጦጦ ኪደነምሕረትን በጸሎቱ የባረከ ይህንን የመሰለ ቅዱስ አለመዘከሩ ታሪኩ አለመጻፉ የታሪክ ጸሐፍት ወዴት አሉ ሊቃውንቱስ ወዴት ተደበቁ ያሰኛል፤ ከእመቤታችንንና ከመናገሻው አባ ኤልያስ በረከት ያሳትፈን። አሜን !!!

LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment