Thursday, November 21, 2013

╬ ╬ ╬ በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ╬ ╬ ╬

ህዳር 12

በዚህች ቀን የሰማይ ሰራዊት ሁሉ አለቃቸው መልአከ ምክሩ የምክሩ አበጋዝ ይለዋል የቅድስት ስላሴ መንጦላእትን የሚከፍትና የሚዘጋ ለፍጥረት ሁሉ የሚማልድ የገናናው ቅዱስ ሚካኤል የተሾመበት ቀን ነው። በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ህዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2 እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)
የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” (ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ቅዱስ ሚካኤል እንዲህ አለ "በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱም ዘንዶውን ተዋጉት፥ ዘንዶውም አልቻላቸውም፥ ከዚያም በኋላ በሰማይ ቦታ አልተገኘለትም። ራእ 12፤7 ነብዩ ዳንኤልም እንዲህ አለ "በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል" ዳን ፲፪፥፩። አዲስ አበባ ውስጥ ከተተከሉት አብያተክርስቲያናት ቀዳሚው ሾላ የሚገኘው የካ ሚካኤል ነው፤ የተተከለው በ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአብርሃና አጽብሃ ሲሆን ታቦቱ የመጣው ከታቦተ ጽዮን ጋር አብሮ ነው፤ ለዚህም ይመስላል አንዳንድ ምዕመናን አጥቢያቸው የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እያለ የካ ሚካኤል ድረስ ሄደው የሚያነግሱት፤ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።
LIKE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment