Friday, December 27, 2013

ታህሳስ 19


እንኩዋን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ:: ታህሳስ 19 በዚህች ቀን… ንጉሡ ናቡከደነፆር የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው ። ለወርቁ ምስል ሁሉም እንዲሰግድ እንዲንበረከክ አዘዘ ሁሉም ሰገደ ተንበረከከ ከእነዚህ ሦስት የልዑል እግዚያብሔር ብላቴናዎች በቀር ስማቸው ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎም ይባላል፤ ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሦስቱን ብላቴናዎች ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? እንግዲውስ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት ንጉስ ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ደግሞም ያድነናል! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን እንኳን አማልክትህን እንደናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ አሉት። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት እና እሳቱ ይጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ፤ የዚያን ጊዜም እነዚህ ብላቴናዎች ከነልብሳቸው ከነመጐናጸፊያቸው ታስረው እሳት ውስጥ ተጣሉ። ናቡከደነፆር አሟሟታቸውን ሊመለከት ቆመ ወደ እሳቱም ተመለከተ አራት ሰዎችም በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ አየ ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው መለሱለት።እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። ይህም ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡ ናቡከደነፆር ድምጹን ከፍ አድርጎ ከእሳቱ እንዲወጡ ተጣራ የራሳቸው ጸጉር አልተቃጠለም ልብሳቸውም እንዲሁ ናቡከደነፆር ከዚህ በኃላ እንዲህ ሲል እግዚያብሔርን አመሰገነ “በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ” ትንቢተ ዳንኤል 3፡ 1- 30 ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡ 
 

2 comments:

  1. አሜን አሜን አሜን።

    ReplyDelete
  2. እነርሱን ያዳነ መልአክ እኛንም ያድነን። አሜን

    ReplyDelete