Tuesday, December 3, 2013

ኀዳር 24



ኀዳር 24 በዚች ዕለት . . .
1. ካህናት ሰማይ ሱራፌል የድርሻችንን እንወጣ፣ ከበረከቱ ተካፈሉ
ሱራፌል ማለት አጥንተ መንበሩ ለልዑል ማለት ነው : : በቁጥር ሃያ አራት ናቸው: : መንበሩን እያጠኑ ቅዱስቅዱስ ቅዱስ እያሉ ያለ እረፍት ያመሰግናሉ
2. አባታችን ተክለሃይማኖት በሐይቅ እስጢፋኖስ የአቡነ ኢየሱስ ሞዓ ረድዕ ሆነው እያገለገሉ እያለ ተመጥቀው ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር ሆነውየሥላሴን መንበር ያጠኑበት ቀን: ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ እንደ አንዱ ሁነው መንበረ ጸባዎትን ያጠኑበት ታላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በፍቅር እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እረድሄት በረከታቸው ምልጃና ጸሎታቸው ከመላው ህዝበ ክርስቲያን ጋር ይሁን አሜን።
3. በዚህች ቀን የጎሬው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤል አረፉ፤ ትውልዳቸው ጎንደር ነው 1887 ዓ/ም ትምህርታቸው ወሎ ቦሩ ሜዳ፤ በ 1921 ዓ/ም እንዲህ ሆነ እንዲህም ተደረገ፤ አራት አባቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብጽ ይላካሉ ጵጵስና ለመቀበል፤ ከነዚህ አራት አባቶች መካከል አንዱ አቡነ ሚካኤል ነበሩ፤ ግብጽ ለረጅም ዓመት ዝናብ ጠፍቶ ምድሪቱ ነዳ ነበረ፤እነዚህ አባቶች የግብጽን መሬት ሲረግጡ ወዲያውኑ ደመና ግጥም አለ በዚያው ቀንም ዝናብ ዘነበ ይላል፤ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ከግብጽ ከተመለሱ በኃላ የጎሬ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመደቡ ለ 8 ዓመትም ህዝቡን በፍቅር አገለገሉ፤ በ 1929 ዓ/ም ጣሊያን ገባ ጎሬንም ያዘ በወቅቱ የነበሩት አገር ገዢ ቢተወድድ ወልደ ጻድቅና ሹማምንቶቻቸው ወደ ከፋ ሲሰደዱ አቡነ ሚካኤል ህዝቡን ለተኩላ ትቼ አልሄድም ብለው እዚያው ቀሩ ለህዝቡ ስለ አገር ፍቅር ስለ ወገን ክብር ስለ ነጻነት መስበክ ጀመሩ፤ የፋሺሽት ጦር መሪ ኮሎኔል ማልታ ወታደሮቹን ልኮ አቡኑን አስያዛቸው፤ እንዲህም አላቸው “ ለጣሊያን ለመገዛት ቃል ይግቡ ህዝቡንም ያሳምኑልንና እንለቆታለን” አላቸው፤ “እኔ ግን እልሃለው” አሉት አቡኑ፤ “እኔ ግን እልሃለው ለናንት የሚገዛ አይደለም ህዝቡ መድሪቱ የተወገዘች ትሁን” አሉት በድፍረት፤ ተቆጣ ጉድጓድ አስቆፈረ፤ ጉድጓዱ አጠገብ አቡኑን አቆመ አልሞ ተኳሾችንም አዘጋጀ፤ “ጥቂት ጸሎት ላድርግ ፍቀዱሊኝ” አሉ አቡነ ሚካኤል፤ፈቀዱላቸው ጸሎት አደረጉ መስቀላቸውን አውጥተው ግንባራቸው ላይ አስጠጉ፤ “አሁን የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ” አሉ፤ “ተኩስ” የሚል ትእዛዝ ተሰማ፤ ነፍሰ ጋዳዮቹ በተኩስ እሩምታ የአቡኑን ደረትና ግንባር በሳሱት፤ ወደቁ ወደ ጉድጓዱም ተወረወሩ አፈርም ለበሱ፤ከዚህ በኃላ ኮሎኔል ማልታ ሽማግሌዎችን ሰብስቦ እኛ አቡኑን ለምነናቸው ነበር እርሳቸው እምቢ ብለው ነው በአመጽ ስራ በመገኘታቸው ነው፤ እናንተስ ምን ትላላችሁ የአቡኑ መገደል ትክክል ነበር ወይንስ አልነበረም ብሎ አፋጠጣቸው፤ ሽማግሌዎቹ ትክክል አልነበረም ለማለት ፈሩ፤ ከመካከላቸው አንድ የንግግር ዘይቤ አዋቂ አለቃ ቢረሳው የተባሉ አዛውንት ሽማግሌዎቹን ወክለው ለመናገር ቆሙ፤ እንዲህም አሉ “እናንተም ደግ ገደላችሁ፤ እርሳቸውም ደግ ሞቱ ብለው ተናገሩ፤” ቅኔ መሆኑም አይደል “ ደግ ” የሚለው ወርቁ ነው አቡነ ሚካኤል ህዝብ የሚወዳቸው በጣም ደግ ነበሩ። 1936 ዓ/ም የሰማእቱ አጽም ተለቅሞ ጎሬ ደብረ ገነት ማርያም ቤተክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፤ የሚያሳዝነው ግን አቡነ ሚካኤልን ጣሊያን ከገደላቸው እኛ የገደልናቸው ይበልጣል፤ በአገራችን ለቁጥር የሚበዙ ሀውልቶች አደባባዮች እውራ ጎዳናዎች የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ደጎል አደባባይ ፑሽኪን አደባባይ ቸርቸል ጎዳና…ወዘተ እነዚህ ሰዎች እኮ ለራሳቸው ኖረው ለራሳቸው የሞቱ ግለሰቦች ናቸው፤ ሰማእቱ ግን ውድ ህይወታቸውን ለአገር ለወገን ለነጻነት የሰው ናቸው፤ የረባ መታሰቢያ እንኳን የላቸውም፤ ዝክራቸው ቀርቷል ስማቸውም ተረስቷል፤ “ አገሬ ኢትዮጰያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ያለው ማን ነበር ? ህዳር 22 ለኤች አይቪ ኤድስ ሻማ በርቶለታል፤ግጥም መወድስ ዝማሬም ቀርቦለታል፤ሐመ ከመ ዮም “እንደዛሬው ለአመቱ ያድርሰን” ብለንም ተመራርቀንበታል፤ ይገርማል ህይወቱን የሰጠ ሕይወትን ከሚነጥቅ ሲያንስ ይገርማል፤ይደንቃል…፤ ከሰማእቱ አቡነ ሚካኤል፤ ከጻድቁ ተክልዬ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በረከታቸውን ያድለን።

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

No comments:

Post a Comment