Tuesday, December 3, 2013

ህዳር 26


ህዳር 26 ገድለኛው አባ እየሱስ ሞአ አረፉ። የተወለዱት ጎንደር ጎርጎራ ልዩ ስሙ ዳህና ሚካኤል በ 1196 ዓ/ም ነው፤ በ 30 ዓመታቸው መንነው ደብረ ዳሞ ሄዱ በአባ ዮሐኒ እጅ መነኮሱ በተጋድሎም ኖሩ፤ ከዚያም ቅዱስ ገብርኤል እየመራቸው ሐይቅ እስጢፋኖስ መጡ፤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ማለት ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሰረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብጻዊ ጻድቅ ናቸው፤ ገዳሙን ከሰሩ በኃላ የማንን ታቦት እናስገባ ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ ሁለት ታቦት አገኙ አንዱ የእስጢፋኖስ አንዱ የጊዮርጊስ " ይህንን ታቦት በእ...የሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚያብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍም አገኙ ይላል። ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኃላ ነው አባ እየሱስ ሞኣ ወደዚህ ቦታ የመጡት ለ 52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ስራቸውን ይሰራሉ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፤ በእንዲህ ያለ ፍጹም ተጋድሎ ኖረው ህዳር 26 በዛሬዋ ቀን አርፈዋል፤ በነገራችን ላይ ተክልዬን ያመነኮሱ አባት ናቸው። እንደዚህ ነው የመነኮሳት አባት እንጦንስ ነው እንጦንስ መቃርስን ወለደ መቃርስ ጳኩሚስን ጳኩሚስ አቡነ አረጋዊን አቡነ አረጋዊ አባ ዮሐኒን አባ ዮሐኒ የሐይቁን አባ እየሱስ ሞአን ወለዱ አባ እየሱስ ሞኣ ደግሞ ተክልዬን ወለዱ። በዚህ ገዳም የሚከበሩ በዓላት መስከረም 15 የእስጢፋኖስ ፍልሰተ አጽሙ፤ ህዳር 26 የአባታችን እረፍት እንዲሁም ጥር 1 የእስጢፋኖስ እረፍቱ ናቸው፤ በእውነቱ የሚገርም ገዳም ነው ገነት እንጂ ምድር አይመስልም። ቦታውን ለማየት ያብቃን የጻድቁ በረከትንም ያሳትፈን።

No comments:

Post a Comment