Tuesday, February 25, 2014

የካቲት 16


በላዔ ሰብ በአማርኛ ሰው በላ ማለት ነው፤ ትክክለኛ ስሙ ግን ስምዖን ይባላል ቅምር በሚባል አገር የሚኖር እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ ድሆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር፤ ሰይጣን በዚህ ስራው ቀናበት ሊፈትነውም በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ስላሴ ነን ብሎ ተገለጠለት ልክ እንደ አብርሃም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይመጣል እንዳለ፤ እርሱም ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸው ተንከባከባቸውም፤ ምግብ አቀረበላቸው ምግብ አንበላም የምንጠይቅህን ግን ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን አሉት ቃል ገባላቸው እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን አሉት፤ መጀመሪያ ደነገጠ ኃላ አብርሃም ልጁን ሊሰዋ አልነበረምን እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል ብሎ ለማረድ ተዘጋጀ፤ተው የሚለው ድምጽ አልሰማም፤ አረደው አወራረደው ይዞላቸው ቀረበ፤ መጀመሪያ ቅመስልን አሉት ቀመሰው ወዲያው እነዚያ ሰዎች ተሰወሩበት እርሱም አህምሮውን ሳተ ተቅበዘበዘ ከዚያ በኃላ ምግብ አላሰኘውም የሰው ስጋ እንጂ መጀመሪያ ቤተሰቦቹን በላ ከዚያም ጓደኞቹን ጦርና የውኃ መንቀል ይዞ ከቤቱ ወጣ ያገኘውን ሰው እየገደለ ይበላል የበላቸው ሰው ቁጥር 78 ደረሰ፤ በመንገድ ተቀምጦ የሚለምን በደዌ የተመታ አንድ ደሃ አገኘ ሊበላው ወደ እርሱ ተጠጋ ግን ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፤ ደሃውም “ስለ እግዚያብሔር ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ” አለው “ዝም በል ደሃ” ብሎት አለፈ፤ “ኸረ በውኃ ጥም ልሞት ነው ስለ ጻድቃን ስለ ቅዱሳን” አለው አሁንም ዝም ብሎት ሄደ ለሦስተኛ ጊዜ “ስለ አዛኝቷ ስለ እምዬ ማርያም” አለው፤ ሰውነቱን አንዳች ነገር ወረረው “አሁን የጠራከውን ስም እስኪ ድገመው ስለ ማን አልከኝ” አለው፤ ስለ አዛኝቷ ስለ እመቤቴ ማርያም አለው፤ ይህቺስ ደግ እንደሆነች በምልጃዋም ከሲኦል እንደምታወጣ ህጻን እያለው እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበር፤ በል እንካ አለው እጁን ዘረጋለት ጥርኝ ውኃ ጠብ አደረገለት ወደ ጉሮሮው አልወረደም የተሰነጠቀ እጁ ውስጥ ገባ እንጂ፤ በለዔ ሰብ ከዚያች ደቂቃ በኃላ አዕምሮው ተመለሰለት እንዲህም አለ “በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ ስጋዬ ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ ወዮሊኝ ወዮታም አለቢኝ አለ፤ ወደ ዋሻ ገባ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን ኖሮ በርሃብ ሞተ ይላል ተአምረ ማርያም። ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት እያስፈራሩ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት መጡ፤ እመቤታችን ፈጥና በመካከላቸው ተገኘች፤ ልጄ ወዳጄ ይህችን ነፍስ ማርሊኝ አለችው እናቴ ሆይ 78 ነፍሳትን የበላ እንዴት ይማራል አላት፤ የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ ቃል ኪዳን አስብ ስምሽን የጠራ መታሰቢያሽን ያደረገን እምርልሻለው ብለኸኝ የለምን አለችው፤ እርሱም እስኪ ይህቺን ነፍስ በሚዛን አስቀምጧት አለ ቢያስቀምጧት ጥርኝ ውኃው መዝኖ ተገኘ፤ ስላቺ ስል ምሬታለው ሰባት ቀን ሲኦልን አስጎብኝታችሁ ወደ ገነት አግቧት አላቸው። ቦታሽ እዚህ ነበር እያሉ ሲኦልን አስጎብኝተው ወደ ገነት አገቧት። ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን። ተአምረ ማርያም

No comments:

Post a Comment