Monday, March 31, 2014

ገብርሔር (ስድስተኛ ሳምንት)


ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡

በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡

ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡

ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡

በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡- 

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:-

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡

3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:-

ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡
ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡

የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡

ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን?

ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡ 

ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት ... የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡ 

በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡

እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡

እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡

ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡

ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡ 

2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ 

መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በዲ/ን አባተ አስፋ


LIKE OUR PAGE >>>

Thursday, March 27, 2014

መጋቢት 19

በዚህች ቀን የብርሃናተ ዓለም የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር የሆነው ሐዋርያው አርስጣባሉ በሰማዕትነት አረፈ። ይህ ሐዋርያ ቁጥሩ ከ 72ቱ አርድእት ነው፤ በአምሳኛው ቀን ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ አብሮ ነበር፤ በኃላም ቅዱስ ጳውሎስን ተከትሎ አገር ለአገር እየዞረ ወንጌልን አስተማረ፤ ቅድስናውን በተመለከቱ ጊዜ አባቶቻችን ሐዋርያት አብራጣብያስ በሚባል አገር ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾሙት እርሱም ወረደ ተወለደ ሞተ ተቀበረ ተነሳ ዳግም ለምጽአት ይመጣል፤ በእርሱ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ይፈረድበታል እያለ ክርስቶስን ሰበከላቸው ብዙዎች አመኑ ተጠመቁም ቤተክርስቲያን አንጾላቸው ዲያቆን ካህን ሾሞላቸው ሲያበቃ ወንጌልን ለማስፋት ወደ ሌላ አገር ሄደ፤ በዚያም ሲሰብክ ሲያስተምር ዓላውያን ጣኦት አምላኪዎች ያዙት በብዙም አሰቃዩት በዛሬዋ ቀንም ገደሉት፤ እርሱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች መልእክትን ሲጽፍ የዚህን አባት ስም አንስቶ ሰላምታ አቅርቦለታል ሮሜ 16፤10። ከቅዱስ ገብርኤልና ከሐዋርያው አርሰጣባሉ በረከት ያሳትፈን። 

LIKE OUR PAGE >>>

መጋቢት 17

በዚህች ቀን የአገረ ሮሜው ቅዱስ አባ ቴዎቅሪጦስ በሰማዕትነት አረፈ። ገና የ15 ዓመት ብላቴና ሳለ ዓላውያን ለጣኦት እንዲሰዋ ግድ አሉት፤ ከጌታዬ ከእየሱስ ክርስቶስ በቀር አምላክ የለም አላቸው፤ እየደበደቡ ንጉሱ ጋር አቀረቡት፤ ንጉሱም ለጣኦት ስገድ አለው፤ ንጉሱንም ጣኦታቱንም ዘለፋቸው፤ ንጉሱ ተቆጣ አፍንጫውን ቆረጠው፤ ወደ ገደል ወረወረው፤ ስጋው እስኪበጣጠስ አጥንቶቹ እስኪሰባበሩ አስደበደበው፤ እንዲያውም የሰደባቸው የዘለፋቸው አማልክቶቻችንን ተበቅለው ያጥፉት ብሎ ጣኦት ቤት አስገብተው ዘጉበት፤ ይህ ቅዱስ ግን ጣኦቶቹ ላይ ያለውን ወርቅ እያወለቀ በስውር ወጥቶ ለጦም አዳሪዎችና ለምስኪኖች... አከፋፍሎ ይመለሳል፤ በሩ እንደቀድሞ ይዘጋል ሐዋ 16፤26 ጳወሎስና ሲላስ የወህኒ ቤቱ በር በመዝሙር እንደከፈቱት ልብ ይሏል። ከአንድ ሳምንት በኃላ ሊያየው ቢመጣ ጣኦታቱ ተሰባብረው ወድቀው ቅዱሱ ሲዘብትባቸው አገኘው 1ኛ ሳሙ 5፤4 በዚህም ተቆጣ የሆድ እቃው እስኪታይ አስደበደበው፤ ወደ መጫወቻ ቦታ አስገቡት አንበሶች ለቀቁበት፤ አንበሶቹ ግን ቁስሉን ላሱለት ዳን 6፤22። ዳግመኛ ልዩ ልዩ መከራ አደረሰበት በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን አንገቱን ቆርጠው ገደሉት እርሱም የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጀ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሰማዕቱ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

መጋቢት 14

በዚህች ቀን ከፍጹማን መነኮሳት አንዱ የሆነው አባ ባጥል አረፈ። ይህ አባት ከሌሎች አባቶች ለየት የሚያደርግው ቅድስና አለው፤ ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በእስክንድርያ ያሉትን ሴተኛ አዳሪዎችን ስማቸውን መዘገበ ከዚያም ሰርቶ ለፍቶ የሚያገኛትን ጥሪት ለዕለት ጉርሱ የምትሆን የሽንብራ ቂጣ ይገዛበታል፤ የተረፈውን ገንዘብ ግን ሴተኛ አዳሪዎቹ ጋር ሄዶ ዛሬ ካንቺ ጋር ነው የማድረው ይልና ገንዘብ ሰጥቶ ይገባል ሌሊቱን ሙሉ ሲሰግድ ሲጸልይ ያድርና ጠዋት ይህንን ስራዬን ለማንም እንዳትናገሪ ብሏት አምሏት ይወጣል፤ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ሌላዋ ጋር ይገባል እንዲሁ ያደርጋል፤ ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን አንዲ...ቷ ሴተኛ አዳሪ ማሃላዋን አፍርሳ ለሰዎች ተናገረች፤ " እርሱ ንጹህ መነኩሴ ነው ምንም ኃጢያት የለበትም እኛ እንዳናመነዝር ከኃጢያት ይጠብቀናል ሌሊቱን ሁሉ ሲሰግድ አድሮ ገንዘባችንን ከፍሎን ይሄዳል" ብላ ለሰዎች ተናገረች። ማሃላዋን ስላፈረሰች ጋኔን ይዞ አሳበዳት፤ ሌሎቹ እውነቷን ነው ብለው ለመመስከር ፈሩ ይላል። የዚህን አባት ስራውን ትህትናውን ፍቅሩን የተመለከቱ ሴተኛ አዳሪዎች ገሚሱ መንኩሰው ገዳም የገቡ አሉ፤ ገሚሶቹ ባል አግብተው የኖሩ አሉ፤ ጨርሰው ይህን ክፉ ስራ የተውም አሉ። የዛኑ ያህል ደግሞ ብዙ ሰዎች ባለማወቅ ይነቅፉት፤ ይሰድቡት፤ ይጸየፉትም ነበር፤ እርሱ ግን በትህትና ተጋድሎውን አበዛ መጋቢት 14 በዛሬዋ ቀን እንደተለመደው ሌሊቱን ሁሉ ሲሰግድ አድሮ ሊነጋጋ ሲል አረፈ የቤቱ ወለል ላይ " እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ" ማቴ 7፤1 የሚል ፅሑፍ ተጽፎ ተገኘ፤ ታሪኩም ለሁሉ ተገለጸ ብዙዎች ተገረሙ ዳን 5፤5። በጸሎቱ የሚገኝ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን። 

LIKE OUR PAGE >>>

መጋቢት 13

በዚህች ቀን ፵ ሐራ ሰማይ በሰማዕትነት አረፉ። 
ዘመኑ ዘመነ ሰማዕታት ነው በወቅቱ በሮም ነግሶ የነበረው ደግሞ አረመኔው ንጉስ ሉክ
ያኖስ ነው፤ መኮንኑ ግሪኮልዮስ ይባላል። ክርስቶስን ክዶ ለጣኦት እንዲሰግድ ህዝቡ ላይ የመከራ ቀንበር ጫኑበት፤ ብዙዎች ሞቱ ብዙዎችም ካዱ። የንጉሱ ወታደሮች የነበሩት በጀግንነታቸው የሚታወቁት አገራቸውን በውትድርና ያገለገሉት ፵ ሐራ ሰማይ ግን እኛ የሰማያዊው ንጉስ የእየሱስ ክርስቶስ ወታደሮች ነን ለጣኦት አንሰግድም አሉ። ለዚህም ነው ፵ ሐራ ሰማይ የተባሉት “የሰማያዊ ንጉስ ወታደር ተከታይ” ማለት ነው፤ ብዛታቸው 40 ነው። ከዚህ በኃላ ልዩ ልዩ ጸዋትኦ መከራ... አጸኑባቸው ይህን ሁሉ ታገሱ፤የመጨረሻ መከራቸው ግን ለየት ያለ ነበር፤ ሰውነትን የሚቆራርጥ እጅግ ቀዝቃዛ ወደሆነ የበረዶ ባህር ውስጥ መጣል መወርወር፤ ተጣሉ ተወረወሩም ስቃዩ ቅዝቃዜው እጅግ ጸናባቸው፤ ቀናት፤ ሳምንታት፤ ወራት ተቆጠሩ ወታደሮች ዙሪያውን ከበው እየተመለከቷቸው ነው፤ የሚገርመው የመጨረሻው ቀን ላይ አንዱ ስቃዩ ሲጸናበት ከባህሩ ወጣ 39 ቀሩ ነገር ግን 40 የብርሃን አክሊላት ወርዶ በራሳቸው ላይ አረፈ አንዷ ብቻ አየር ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፤ ይህንን የተመለከተ ወታደር ሮጦ ወደ ባህሩ ገባ ከሰማዕታቱ ጋርም ተቀላቀለ፤በበነጋው ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው ይህም መጋቢት 13 ቀን ነው። ከሰማዕታቱ በረከት ያሳትፈን። 
ስንክሳር፤ ገድለ ሰማዕታት

LIKE OUR PAGE >>>

መጋቢት 10

ተቀብሮ አልቀረም ተገኝቷል መስቀሉ

በዚህች ቀን ክብር ይግባውና የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለዘመናት ተቀብሮ ከኖረበት ቦታ የወጣበት ቀን ነው። መስከረም 16 ቀን ደገኛዋ እናት እሌኒ ቅድስት ደመራ ደምራ በደመራው ጢስ አማካኝነት የተቀበረበትን ቦታ አገኘች መስከረም 17 ቁፋሮ ጀመረች፤ከ 300 ዘመናት በላይ ቆሻሻ እየተጣለበት ታላቅ ተራራ አህሎ ነበርና እነሆ ቁፋሮ ስድስት ወራት ፈጀባቸው መጋቢት 10 በዛሬዋ ቀንም መስቀሉ ወጣ። ሦስት መስቀሎች ናቸው፤ሁለቱ መስቀሎች ሽፍታዎቹ የተሰቀሉባቸው ሲሆኑ አንዱ የጌታችን ነው፤ ታዲያ እንዴት ለየችው ቢሉ የጌታችን መስቀል ታላላቅ ታአምራትን አድርጓል ድውይ ፈውሷል ዓይነስውር አብርቷል። ይህንን ቀን ቅድስት ቤተክርስቲያን "መስቀለ እየሱስ" ስትል ታከብረዋለች፤ በዛሬዋ ቀን ዝማሬው፤ ምስጋናው፤ ትምህርቱ፤ ቅዳሴው ፤ ንባቡ ሁሉም መስቀልን የሚመለከቱ ናቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መስቀል የሚጣፍጥ ነገር ተናገረ እንዲህ ሲል “ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” ገላትያ 6፤14። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

— with Ayalew Amogne.

Monday, March 17, 2014

መጻጉዕ (የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ)



በዐቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት መካከል አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ድውያንን መፈወሱን ዕራንን ማብራቱን የሚያነሣ በመሆኑ ነው፡፡ «38 ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው «ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም» አለው:: «ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ» ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ «የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ» እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡

«በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና

«በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ እያለ 38 ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ወዘተ እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ዕለቱና ሳምንቱ መጻጉዕ ተብሏል፡፡

ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በነዚህ ሁሉ ታሪኮች የመጻጉዕንና የሌሎቹን ሕሙማን ሁሉ ደኅንነት ታሪክ እንረዳለን፡፡ የሰንበቱም ስያሜ ልብ ወለድ አጠራር ሳይሆን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡


በዕለቱ በቅዳሴ ላይ የሚነበቡትም ምንባቦች የሚከተሉት ናቸው፡

1ኛ. የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች 5Ý1(26

2ኛ. የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት 5፡14-20 

3ኛ. የሐዋርያት ሥራ 3፡1-12 


እንዲሁም የዕለቱ ምስባክ ደግሞ

በመዝሙር 4ዐቁጥር 3 ላይ የሚገኘው

እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፡፡ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል እኔስ አቤቱ ማረኝ፡፡


የሚለው ይሆናል፡፡የዕለቱ የወንጌል ንባብም

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 25 ድረስ ያለው ነው፡፡

ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርስ የጌታች ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምኩራብ (የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት)



ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ»

«ምኩራብ» ማለትም ቀጥተኛ ፍችው ኮረብታ፣ ተራራ የሚያኸል ታላቅ ሕንጻ ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የአይሁድ ቤተ ጸሎት ወይም ቤተመቅደስ ማለት ይሆናል፡፡ ዐቢይ ፍሬ ቃሉ ግን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በትምህርቱ፣ ድውያነ ነፍስን በታምራቱ ሲፈውስ በምኩራብ እየተገኘ የፈጸመውን የማዳን ሥራ በኀሊና እያሳሰበ የሚያስተምር ሦስተኛ ሳምንት ነው፡፡ ዮሐ. 2:12

«ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ» እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ነው፡፡ የዚህም በዓል ታሪክ ዝርዝር ሁኔታው በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 21፡12-13 ተጠቅሷል፡፡

ቆላስ 2፡16-23 «እንግዲህ በመብል ወይ በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፣ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለፈቃድ እየገባ፣ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ እንደዚህ ያለ ሰው ራስ ወደሚሆነው አይጠጋም፣ ከእርሱም አካል ሁሉ በጅማትና በማሰሪያ ምግብን እየተቀበለ እየተጋጠመም፣ እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ ያድጋል፡፡ ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ት ምህር ት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እንደሰው ሥርዓትና ት ምህር ት፡- አትያዝ አትቅመስ፣ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም ሁሉ እንደምትኖሩ ስለምን ትገዛላችሁ) እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና፡፡ ይህ እንደገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቈን ጥበብ ያለው ይመስላል፣ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም፡፡»

ያዕ 2፡14-26 « ወንድሞቼ ሆይ፣ እምነት አለኝ የሚል፣ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል) እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን) ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፣ ከእናንተ አንዱም በደህና ሂዱ፣ እሳት ሙቁ፣ ጥገቡም ቢላቸው ለሰውነት ግን የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው ምን ይጠቅማቸዋል) እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡

ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ በእግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡ አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን) አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን) እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን) መጽሐፍም አብርሃምም እግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን) ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡»

የሐዋ.ሥራ 1ዐ፡1-9 « በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ፡፡ ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል፡- ቆርኔሌዎስ ሆይ የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው እርሱም ትኩር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ ጌታ ሆይ ምንድር ነው) አለ፡፡ መልአኩም አለው፡- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን ዐረገ፡፡ አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ፡፡ እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቁርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ የተናገረውም መልአክ በሄደ ጊዜ ከሎሌዎቹ ሁለቱን፣ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ፣ ነገሩን ሁሉ ተረከላቸው ወደ ኢዮጴም ላካቸው፡፡ እነርሱም በነገው ሲሄዱ ወደ ከተማም ሲቀርቡ፣ ጴጥሮስ በስድስት ሰዓት ያህል ይጸልይ ዘንድ ወደ ጣራው ወጣ፡፡

መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡

ዮሐ 2፡12-25 «ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡ ስለዚህ አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ) አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን) አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡ ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡

በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡»

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


LIKE OUR PAGE >>>

ቅድስት ( የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት )


«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች » ማለት ነው፡፡ ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ. 4-2

ቅድሰት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ስያሜውም ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ና ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ክቡር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ መጻሕፍትም የባሕርይ ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡( ኢሳ 6፡1-3፤40፡25 ራዕ 15፡4 ፤ 1ሳሙ2፡2-3፡፡) እኛም ቅዱስ ልጁ በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡ የቅድስና ምንጭ ፡ ቅድስናን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡ለመላእክት ፡ ለቦታ ፡ለዕቃ፡ ለዕለታት … ቢቀጸልም ቅድስናቸው በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ይህም የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው፡፡ ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ እግዚአብሔር ለቅድስና እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና ›› ያለንም ለዚህ ነው፡፡/1ተሰ 4*7/ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን አላማ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች እንዲህ ገልጾላቸዋል ‹‹ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ብሎ ካመሰገነ በኋላ ‹‹ ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን ፡ንጹሐንና ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን›› ኤፌ 1፡3-4 አስቀድሞ ስለወደደንና ስላከበረንም ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጅቶ በእጆቹ ካበጀን በኋላ የሥነ ፍጥረት ዘውድ አድርጎ በገነት አኖረን ፡፡( ዘፍ 1፡26 ፤መዝ 8፡1)

የቀደመው አዳም አታድርግ የተባለውን በማድረጉ በንዝህላልነትና በስንፍና በከይሲ ዲያብሎስም ምክር ተዋረደ፡፡ በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ፤በርዕደተ መቃብር ላይ ርዕደተ ሲኦል ተፈረደበት፡ በባሕርዩ ሞት ገባበት፡ተዳደፈ፡፡ ክፉ ፍትወታት የሚያጠቁትና የሚያሸንፉት የዲያብሎስና የኃጢአት ባርያ ሆነ፡፡ በማይለወጥ ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ግን ጠፍተን እንድንቀር አልተወንም፡፡ በሰጠን ተስፋ፡በተቆጠረው ሱባኤና በተነገረው ትንቢት መሰረት ዘመኑ ሲደርስ በተዋህዶ ሰው ሆነ፤ የተዋረደ ሥጋችንን አከበረ፡፡ በከበረ ደሙ ዋጀን፤ከኃጢአታችን አጠበን፡፡ በእርሱ ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን ፡፡ጌታችንና መድኃኒታችን ሰው የሆነውና ለመዳናችን የሆነውን ዋጋ ሁሉ የከፈለው ለእኛ ያለውን ፍቅርና ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ለእኛ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ ነገር ግን የኃጢአትን ሥራ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለውን አሮጌውን ሰውነታችን እንደሆነ ይህን እናውቃለን ›› የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ (ሮሜ 6፡6) እኛን ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ የተከፈለውም ዋጋ ታላቅ ከሆነው የጋብቻ ምስጢር ጋር በማያያዝ እንዲህ ገልፆታል ‹‹ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርሰቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና … ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት ራሱንም ስለእርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ፡፡ በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኩሰት እንዳይገኝባት ቤተ ክስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ…›› ኤፌ 5፡23-28
ስለዚህ ጌታችን በደሙ ኃጢአታችንን እንደ ቸርነቱ ይቅር ብሎናል፡፡ኤፌ 1፡7 ከእንግዲህ የራሳችን አይደለንም ፡፡ በሰውነታችንም ኃጢአትና ዐመፃን ልናደርግበት አይገባም ፡፡‹‹በዚህ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አታንግሷት፤ለምኞቱ እሺ አትበሉት፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ››ተብለናል፡፡ (ሮሜ6፡12-13)

የተወደዳችሁ ምዕመናን እግዚአብሔር ደስ ብሎት የሚቀበለውን ህይወት ለመኖር አንፈልጋለን ፡፡ ለመሆኑ ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ብንመላለስ ነው? መልሱን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮቱ ከንቱ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ወላጆች የሌሉአቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በችግራቸው መጠየቅ በዓለምም ከሚገኝ ርኩሰት ሰውነትን መጠበቅ ነው፡፡››በማለት ይመልስልናል( ያዕ 1፡26-27)፡፡ በክርስቶስ ደም የተቀደሰና የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በዓለም ከሚገኝ ርኩሰት መጠበቅ የሰማያዊ ርስት ወራሾች ያደርገናል፡፡ በዓለም የሚገኘውን ርኩሰትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሥጋ ሥራ ›› በማለት ገልጾታል፡፡‹‹እርሱም ዝሙት ፣ርኩሰት፣መዳራት፣ጣዖት ማምለክ፣ሥራይ ማድረግ፣መጣላት፣ ኩራት፣የምንዝር ጌጥ ፣ቅናት፣ቁጣ ፣ጥርጥር፣ፉክክር፣ ምቀኝነት፣ መጋደል፣ ስካር ፣ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡››እነዚህን የሚያደርጉ ሰዎችም ከመንግስተ እግዚአብሔር በአፍአ ወይም በውጭ እንደሚቀሩ ሲያስረዳ‹‹አስቀድሜ እንደነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይም›› ብሏል ( ገላ5፡19)።

በሕይወታችን ሁሉ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን መገኘት ለቅድስና የጠራንን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡እነዚህንም ነገሮች ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመንፈስ ፍሬዎች ›› ብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ፍቅር፣ደስታ ፣ሰላም፣ትዕግስት፣ምጽዋት፣ቸርነት ፣እምነት ፣ገርነት ንጽሕና ››ናቸው፡፡ገላ 5፡22 እግዚአብሔር ማደርያው ይሆን ዘንድ የመረጠውን ሰውነታችንን እርሱ የሚከብርበትን ሥራ ልናደርግበት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በሕይወት የሚኖሩትም ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ›› እንደተባለ በሕይወታችን ሁሉ ፋቃዱን በመመርመርና በመፈጸም በቅድስና ልንኖር ይገባናል፡፡2ቆሮ 5፡15

ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ1፡15)፡፡ ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣በማኅበራዊ ኑራአችን ፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣በንግግራችንና በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን በማድረግ እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር ይገባናል(ዕብ 12፡1)። ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር


LIKE OUR PAGE >>>

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ)

ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ /መዝ 2፡11-12/

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት (ዘወረደ) ለአጠቃላይ ጾሙ መግቢያ የሚሆኑ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች(መልዕክቶች) ይተላለፉበታል። እነዚህን ቀጥለን እንመለከታለን።

1. ስለ ጾም

ዘወረደ የታላቁ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን የጾም አዋጅ ታውጅበታለች፤ ስለ ጾም ጥቅምና እንዴት መጾም እንዳለብን ታስተምረናለች፡፡ጾመ ድጓው “አከለክሙ መዋእል ዘኃለፈ ዘተቀነይክሙ ለግእዘ ሥጋክሙ፤ ለሥጋቸሁ ፈቃድ የተገዛችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋል፤ ከአሁን በኋላ ግን ጹሙ፣ ጸልዩ ለእግዚአብሔር ተገዙ” እያለ የጾም አዋጅ ያውጃል።
ጾም ፈቃደ ስጋን ለፈቃደ ነፍስ፣ ፈቃደ ነፍስን ለፈቃደ እግዚአብሔር/ለመንፈስ ቅዱስ/ የምናስገዛበት መንፈሳዊ መሳሪያ ነው፡፡ጾሙ ይህ የሚደረግበት መሆኑን ቤተክርስቲያን ሳምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት በሚሰበከው ምስባክ እንዲህ ብላ ታሳስባለች፤ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣በረዓድም ደስ ይበላችሁ” /መዝ 2፡11-12/ ጾም ከምግብና ከመጠጥ እንዲሁም ከሌሎች ምቾቶችና ደስታዎች ከመከልከል ያለፈ ጥልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው። ጾም ውጤታማ እንዲሆን እነዚህ መከልከሎች ከጸሎት ፣ ከፍቅርና ራስን ከማዋረድ ጋር መተባበር አለባቸውና በዚህ ሳምንት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ እያለች ታስተምራለች፦“ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ከመ ያብርህ ብርሃነ ስብሃቲሁ በላዕሌነ፤ (የእግዚአብሔር) የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም ፤ወንድማችንንም እንውደድ”
(ጾመ ድጓ)።በዘወረደ እሁድ የሚነበቡት ምንባባትም ይህንን መልዕክት የያዙ ናቸው።“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡” /ያዕ 4÷6-10/
“ በውኑ እንግዲህ በስሙ እናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” /ዕብ 13÷15-16/
“ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና ። ” /ዕብ. 13፥9/በጾም የተጠቀሙ ቅዱሳንን እያሰብን ለጾም እንድንተጋም ወደ እነርሱ እንድንመለከት ቤተክርስቲያን ትጠቁማለች፡፡ ሳምንቱ በሚጀምርበት ሳምንት የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትእንዲህ ይላል፡፡
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው።” /ዕብ. 13፥7/ጾመ ድጓው ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንዲህ እያለ ያስታውሰናል፤“የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን በላያችን ላይ ያበራ ዘንድ ጾምን እንጹም፤ ወንድሞቻችንም እንውደድ፤ ኤልያስ በጾም ወደ ሰማይ አርጓልና፤ዳንኤልም ከአናብስት አፍ ድኗልና፡፡”

2. ስለ እግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሥጋዌ)

ከዐቢይ ጾም ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያሉት ዕለታት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን ያደረጋቸው ነገሮች (ማስተማሩ፣ ተአምራት ማድረጉ፣ በፈቃዱ ተላልፎ መሰጠቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱ፣ መንፈስ ቅዱስን መላኩ…) በስፋት የሚነገርባቸው ናቸው።
የእነዚህ ሁሉ ነገሮች መሠረትና ያገኘናቸው ጸጋዎች ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር ወልድ መውረድ (ሰው መሆን) ነው።ይህ ሣምንት የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሣምንት እንደመሆኑ ቀጥለው ለሚነገሩት ነገሮች መሠረት የሆነው ይህ የእግዚአብሔር መውረድ ይነገርበታል። ዘወረደ (የወረደው) የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከዚህ በመነሳት ነው።
ሣምንቱ በሚጀመርበት ሰንበት የሚነበበው ወንጌል ይህን መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።“እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ነገር ግን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም። በምድር ያለውን ስነግራችሁ ካላመናችሁኝ፥ በሰማይ ያለውን ብነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው። ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና።” /ዮሐ. 3፥11-16/ጾመ ድጓው የሚጀምረውም እንዲህ በማለት ነው፣ “ዘወረደ እምላዕሉ፣ አይሁድ ሰቀሉ…. እግዚአ ኩሉ ዘየሀዩ በቃሉ፤ ….በቃሉ የሚያድነውን ከላይ የወረደውን የሁሉን ጌታ አይሁድ ሰቀሉት… ”

3. ስለ ትምህርት

ዐቢይ ጾም የትምህርት ዘመን ነው። በጥንት ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ አማንያን /ንዑሰ ክርስቲያን/ የሚጠመቁት በትንሣኤ በዓል ስለነበር በዐቢይ ጾም ሰፊ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር።ዛሬም ዐቢይ ጾም ጌታችን በዚህ ምድር በእግረ ሥጋ በተመላለሰባቸው ዘመናት ያደረጋቸው ነገሮች (ትምህርቱ፣ ተአምራቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው … ) በሣምንታት ተከፋፍለውና ተደራጅተው የምንማርበት የትምህርት ዘመን ነው። በአብነት ትምህርት ቤቶቻችንም ዐቢይ ጾም ዋነኛ የትምህርት ዘመን መሆኑ ይታወቃል።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ዘመን በሆነው ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ስለ ትምህርትና ስለ መምህራን እንዲህ እያለች ትሰብካለች፤
“የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም የሚኖር እርሱ ነውና። ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ።” /ዕብ. 13፥7-9/
“ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደመሆናቸው፣ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና፡፡” /ዕብ. 13፥17/
አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ መዋዕለ ጾሙን በሠላም አሳልፈህ የትንሣኤህን ብርሃን ለማየት እንድታበቃን እንለምንሃለን። አሜን።

በዲ/ን አሉላ መብራቱ

LIKE OUR PAGE >>>