Monday, June 9, 2014

ግንቦት 21

ግንቦት 21

ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤በዚህ ቀን ግብጽ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በተሰራች ቤተክርስቲያን እመቤታችን ጻድቃንን መልአክትን አስከትላ ትገለጽላቸው ነበር፤እስላምም ክርስቲያንም በግልጽ ይመለከቷት ነበር። ከየአገሩ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ድንኳን ተክለው ሰቀላ ሰርተው አጎበር ጥለው ይከትማሉ ፤ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ ለአምስት ተ...ከታታይ ቀናት ሳታቋርጥ ትገለጽላቸው ነበር፤ህዝቡ የተለያየ ጥያቄ ይጠይቃታል አዳም አባታችንን አሳይን ይሏታል ገሚሱ ነብዩ ዳዊትን ገሚሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳይን ይሏታል አንዳንዱም ከዚህ ቀደም የሞተ ዘመዱን እንድታሳየው ይጠይቃታል፤እርሷም ለሁሉም ፍቃዳቸውን ትፈጽምላቸው ነበር፤አዳምን ስትጠራው ከሔዋን ጋር ዳዊትን ስትጠራው ከበገናው ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስን ስትጠራው ከጸአዳ ፈረሱ ጋር ነው። ወይ ግሩም ታዲያ ይህ በዚያ ደጉ ዘመን ነበር፤አሁን ግን ኃጢያታችን ሲበዛ በረድኤት ካልሆነ በገሃድስ ተገልጻ አትታይም ለበቁ ካልሆነ። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን አባ መርትያኖስ አረፈ፤ ይህም በህጻንነቱ መንኩሶ ለ 67 ዓመት በፍጹም ተጋድሎ የኖረ ነው። ይህ ገድል ትሩፋቱ በሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ እነሆ አንዲት በዝሙት ስራዋ እጅግ የምትታወቅ ሴት ዘንድ ወሬው ደረሰ፤ እርሱ እኮ የሴት ፊት ስላላየ ነው እንጂ በፍትዎት ይወድቃል ከክብሩም ይዋረዳል አለቻቸው ባልንጀሮቿም የለም በፍጹም አያደርገውም አሏት፤ እኔ በዝሙት ከጣልኩት ምን ትሰጡኛላችሁ አለቻቸው ብር እንሰጥሻለን አሏት፤በዚህ ተወራርደው ሄደች፤ ሽቶ ተቀባብታ አምራ ተውባ ሄደች፤ስንክሳሩ እጅግ ውብ መልከመልካም ነበረች ይላታል፤ እስኪመሽ ከገዳሙ አቅራቢያ ቆይታ በሩን አንኳኳች የመሸቢኝ እንግዳ ነኝ አሳድረኝ ትለዋለች፤ ነፍሱ ተጨነቀች ባስገባት የዝሙት ጦር ይነሳብኛል ብተዋት እንግዳ ሆኜ መጥቼ መቼ ተቀበላችሁኝ ብሎ ይፈርድቢኛል ደግሞም አውሬ ይበላታል ብሎ አሰበ፤ባስገባት ይሻለኛል ብሎ አስገባት የተቀበችው ሽቶ ዝሙት የሚቀሰቅስ ነው፤ ቀረበችው፤አባቴ በዚህ ማንም አያየንም አብረን እንተኛ አለችው፤እሳት እያነደደ ነበርና እሺ ምን ችግር አለው እዚህ አሳት ላይ ምንጣፍሽን አንጥፊና እንተኛለን አላት፤ አንድም እግሩን ወደ እሳቱ ማገደው ይላል አይንህ ብታሰናክልህ ካንተ አውጥተህ ጣላት አይደል የሚለው መጽሐፉ፤ ደነገጠች ምንድን ነው አባቴ አለችው፤ ይህ ያስደንቅሻልን የገሃነም እሳትን ታዲያ እንዴት ልትችይው ነው አላት እግሩ ስር ወድቃ ይቅር በለኝ አለችው እርሱም ሌሊቱን ሙሉ ሲያስተምራት አደረ፤ ሲነጋ አልተመለሰችም አመንኩሰኝ ከዚህ በኃላ ወደ ዓለም አልመለስም አለችው አመነኮሳት ከደናግል ገዳም ወስዶ ለእመምኔቷ አደራ ሰጣት፤የሚገርመው ይህች እናት ከብቃቷ የተነሳ የመፈወስ ሀብት ተሰጣት ብዙ በሽተኞች ወደርሷ እየመጡ ይፈወሱ ነበር፤ አባ መርትያኖስ ግን ድጋሚ ሌላ ሴት መጥታ እንዳትፈትነው ሰው የማይደርስበት ከባህር መካከል ባለች ደሴት ብቻውን መኖር ጀመረ፤ ከብዙ ዘመን በኃላ መርከብ ተሰብሮ ብዙዎች ሲሞቱ አንዲት ሴት በመርከቡ ስባሪ ተጣብቃ እርሱ ካለበት ደሴት ደረሰች ባያት ጊዜ ደነገጠ አደነቀም ከእርሷ ጋር በአንድነት ስለመኖሩም አዘነ፤ ይምትበላውን ሰጥቷት የምትለብሰውን አዘጋጅቶላት ሲያበቃ ተወርውሮ ወደ ባህሩ ገባ ዓሳ አንበሪም ተሸክሞ ወደ የብስ አደረሰው ከዚህ በኃላ በአንድ ቦታ ላለመቀመጥ ወስኖ በ108 አገሮች የሚገኙ ታላላቅ ገዳሞችን ዞረ በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በክብር አረፈ፤ እመቤታችንን ከሐና ማህጸን ፈጥሮ ከፍጥረተ ዓለም ለይቶ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ ትሁናችሁ ብሎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፤ እኛንም ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

No comments:

Post a Comment