Monday, June 9, 2014

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

በዓለ መንፈስ ቅዱስ/ጰራቅሊጦስ

ምንም እንኳን የዕለታትና የዘመናት ሁሉ ባለቤት እርሱ እግዚአብሔር ቢሆንም በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ነገር ሁሉ በሥርዓት ይሁን ብሎ ሐዋርያው እንዳስተማረን በቤተክርስቲያናችን የበዓላት ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ በኋላ ፶ኛው ቀን በዓለ ጰራቅሊጦስ/በዓለ ሃምሳ/በዓለ ጰንጠቆስጢ ወይንም የቤተክርስቲያን የልደት ቀን በመባል ይታወቃል ወይንም ይከበራል። በግሪክ ቋንቋ ጰራቅሊጦስ ማለት አጽናኝ ማለት ነው።

መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ሥላሴ አንዱ ሲሆን ከአብ የሰረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በመለኮት በስልጣን በአገዛዝ በመሳሰሉት እኩል ወይንም አንድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አብ እና እንደ እግዚአብሔር ወልድ(ኢየሱስ ክርስቶስ) መንፈስ ቅዱስ በራሱ የተለየ አካልና ግብር አለው። ዮሐ.፲፭፥፳፮። መንፈስ ቅዱስ ከዘመናት አስቀድሞ ከአብና ከወልድ ጋር ዓለማትን የፈጠረ ነው። ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር ፴፪፥፮ ላይ <በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ> ሲል ተናግሯል።

መንፈስ ቅዱስ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን አላማ አበክሮ የሚገልጽና ጌታችንም ወደ ቀደመ ክብሩ በምስጋናና በእልልታ ካረገ በኋላ በ፲ኛው ቀን ለሐዋርያት ጸጋውን በማፍሰስ የተገለጸ የቤተክርስቲያን ጠባቂና መሪዋ፤ በእግዚአብሔር ልጅ ያመኑትንና በስሙ የተጠሩትን ክርስቲያኖች የሚያጽናና፣ በኃይማኖት በምግባርና በተጋድሎ የሚያጸና፣ ጥበብንና ማስተዋልንም የሚያድል ነው (ኢሣ.፲፩፥ ፪)። ክርስቲያኖች ከጌታ የተማሩትን መልካም የሆነውን የጽድቅ ሥራ እንዲሠሩ ዘወትር በልቦናቸው አድሮ የሚያሳስብ እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው። <አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔ የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል> ዮሐ. ፲፬፥፳፮ በማለት ሐዋርያት/ክርስቲያኖች በሚሠሩት ሥራ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደማይለያቸው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል።

መንፈስ ቅዱስ በእምነት ጸንተው በጸሎት ለሚተጉ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚሰጥ ኃብት ነው። በተለይም በአንድ ልብ ሆኖ በኅብረት በሚደረግ ጸሎት ምልጃና ጉባዔ መንፈስ ቅዱስ በቶሎ ይሰጣል/ይወርዳል/ይገኛል፤ ለሁሉም እንደ ችሎታውና እንደ አቅሙም ፀጋንና ስጦታን ያድላል። <በዓለ ኀምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበረበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው
በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር> ሐዋ.ሥ. ፪፥ ፩-፬

መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ሰዎች መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠሩና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር እንዲስቡ እነርሱም በረከትን እንዲቀበሉ ነው። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ልዩ ልዩ እነደሆነ ሐዋረያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንዲህ በማለት ዘርዝሮታል፦ የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው አሠራርም ልዩ ልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ ለአንዱም ትንቢትን መናገር ለአንዱም መናፍስትን መለየት ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። (፩.ቆሮ.፲፪፥፬-፲፩)

እዚህ ላይ በተለይ በልሳን የመናገር ስጦታ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ልሳን ማለት በአንደበት የሚነገር ትርጉሙንም ቋንቋው ሲነገር የቋንቋው ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የሚረዱት የሰው ልጆች ልሳን/ቋንቋ ነው። አንዳንዶች የተለየ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች የማይረዱትን ነገር እንደሚያውጡት ያለ ድምጽ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል። በዚህ የተታለሉ እኅቶችና ወንድሞች አሉና። ሐዋርያት በልሳን በተናገሩ ጊዜ በዙሪያቸው የነበሩ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች የእነርሱን ሃገር ልሳን/ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተው ተገረሙ ነው የሚለው ቅዱስ ሉቃስ ( ሐዋ.፪ ፥፭-፲፫ )

ለሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዋናው ምክንያት ሐዋርያት ዓለምን ዞረው አሕዛብን ሁሉ በየቋንቋቸው በማስተማር የክርስቶስ መንግሥት ተካፋይ እንዲሆኑ ዕድል ፈንታ ይኖራቸው ዘንድ ነው። ሌላው በእምነትና በጽናት ተስፋ ለሚያደርጉት ሁሉ ሳይሳሳ በልግስና የሚሰጥ ቸር አምላክ መሆኑን ሲያስተምረን ነው። በዮሐንስ ወንጌል ፫፥ ፴፬ ላይ <እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና> ተብሎ እንደተጠቀሰው። በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ <ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም> ዮሐ.፲፬፥፲፰ ያለውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው።

መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ ሲባል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ሥጋ ለብሶ እንደተገለጸው ያለ አገላለጽ ሳይሆን ጸጋውን አደላቸው ማለት ነው። እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከደሟ ደምን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ እግዚአብሔርን አሳይቶናል፤ አይተነዋል። ለዚህም <...እኔን ያየ አብን አይቷል...> ዮሐ.፲፬፥፰ ብሎ በቅዱስ ቃሉ በሕገ ወንጌሉ አስተምሮናል። መንፈስ ቅዱስ ግን የማይታይ የእውነት መንፈስ ነው። የሚታየው/የሚገለጸው በሚያሠራው በጎ ሥራ ነው። ዘወትር በምንሠራው የጽድቅ ሥራ ወይንም በደልና ኃጢአትን በሠራን ጊዜም በውስጣችን ሆኖ ሲወቅሰን መንፈስ ቅዱስ ከኛ ጋር እንዳለ እናውቃለን። <እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለም ከእናንተ ጋር እንዲሆን ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይችለው የእውነት መንፈስ ነው ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሰጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ> ዮሐ.፲፬፥፲፭-፲፯።

መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖች በድፍረት የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት እንዲመሰክሩ የሚያደርግ ነው ፩ቆሮ. ም.፲፪፥፫ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት መመስከር ሲባልም በዘመናችን እንደምንሰማውና እንደምናስተውለው በብዙ ክሕደት ውሰጥ ሆኖ ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን የእርሱን አምላክነት በማመን ጌትነቱ አምላካዊ የሆነና እርሱ ራሱ ምልጃን ተቀባይ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ በማመን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ክርስቲያኖችም ዘወትር በተሰጠን ፀጋና ችሎታ ቤተክርስቲያንን፣ ሌሎች ወንድሞችና እኅቶችን፣ ኅዙናንን ማገልገል ባጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ተብለው በሐዋርያው በቅዱስ
ጳውሎስ የተማርነውን ለመፈጸም መትጋት ይኖርብናል። እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የተባሉትም ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ናቸው (ገላ.፭፥፳፪-፳፫)። መንፈስ ቅዱስን የተቀበልን ሲባልም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን በ፵ እና በ፹ ቀን በጥምቀት የተቀበልነውን ነገር ግን በውስጣችን ተዳፍኖ ያለውን መንፈስ በበጎና በጽድቅ ሥራ መቀስቀስ ማለት ነው ። አንዳንድ የዋሃን እንደሚሉት አዲስ መንፈስ እስኪወርድልን እንደ ሐዋርያት በአንድ ቦታ ተሰብስበን ቤት ዘግተን እንቀመጥ ማለት እንዳልሆነ ልናውቅ ያስፈልጋል። እርሱም የሚያረጋጋና የሚያስደስት እንጅ የሚያስገዝፍና የሚያስጮህ እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባናል ።

ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሥራውን በኛ ላይ እንዲሠራ በሃይማኖት ጸንተን ራሳችንን ከክፉ ገነር በማቀብ እንድንኖር ያሻል። የያዕቆብ ወንድም ይሁዳም በመልዕክቱ እንዲሁ እንድናደርግ ነው የሚያሳስበን <እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስ እየጸለያችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ> ይሁዳ ፩፥፳። በቤተክርስቲያናቸን ትምህርት መሠረት መንፈስ ቅዱስ የሚወርደው /የወረደው በተለያዩ ምሳሌዎች ነው። በሰው ተመስሎ የተገለጸበት ጊዜ አለ (ዘፍ. ፲፰፥፩) ፣ በርግብ ተመስሎ የወረደበት ጊዜ አለ (ማቴ. ፫፥፲፮)፣ በእሳት የተመሰለበት ጊዜ አለ (ሐዋ.፪፥ ፫፤ ማቴ. ፫፥፲፮)ስለሆነም ዘመናችን ብዙ የሐሰት ትምህርት የሞላበት በተለይም መንፈስ ቅዱስ ወረደልኝ፤ ይወርድልሃል፤ ይወርድልሻል፤ በሚል ማጭበርበርና ማደናገር ብዙዎች ከእውነት የተለዩበት በሐሰት መንፈስ የተወሰዱበት በመሆኑ እውነተኛውን መንፈስ ከሐሰተኛው መንፈስ ለይተን እንድናውቅ ያስፈልጋል። 

በመጨረሻም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ <የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን>ብሎ በ፪ኛ.ቆሮ.፲፫፥፲፬ ላይ አንድ እንሆን ዘንድ በኃይሉ እንዲያበረታን እንደጸለየልን እውነትን አውቀንና ተረድተን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያስተማረችንንና የምታስተምረን ተገንዝበን እንድንኖር እርሱ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር

Source: ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሰ/ት/ቤ/ት/ክ

LIKE OUR PAGE >>>

No comments:

Post a Comment