Monday, July 14, 2014

ሐምሌ 8 እንኳን አደረሳችሁ

በዚህች ቀን ከሮም ነገስታት ወገን የሆነው አባ ኪሮስ አረፈ፡፡ አባታቸው በሞተ ጊዜ ታላቅ ወንድማቸው ቴዎዶሲዎስ በሮም ነገሰ፡፡ አባታችን አቡነ ኪሮስ ግን ሀብት ንብረታቸውን ትተው ወደ ገዳም ሄዱ ከአባ በቡኑዳ እጅም ምንኩስናን ተቀበሉ በታላቅ ተገድሎ ኖረው በዛሬዋ ዕለት በክብር አረፉ፡፡ አባታችን አቡነ ኪሮስ በመዲናችን አዲስ አበባ በኮተቤ መስመር በስማቸው ታላቅ ቤተክርስቲያን አላቸው ሐምሌ 8 ታቦታቸው ወጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል፡፡ ልጅ የሌላቸው እናትና እህቶቻችን ገድላቸውን አዝለው ልጅ እንዲሰጧቸው ስለት ይሳላሉ በዓመቱም ልጅ አዝለው መጥተው ስለታቸውን ይከፍላሉ፡፡ ይህንንም በአይናችን አይተን በጆሯችን ሰምተን ይኸው እንመሰክራለን ፡፡ በረከታቸው ይደርብን

LIKE OUR PAGE >>>

Sunday, July 13, 2014

ሐምሌ 7 እንኳን አደረሳችሁ


በዚህች ቀን አጋዕዝተ ዓለም ስላሴ በአብርሃም ቤት ተገኝተው ቤቱን የባረኩበት የአንድነታቸውንና ሶስትነታቸው ሚስጢር የገለጹበት ታላቅ በዓል ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን ሐምሌ 7 ዕረፍቱ ለአባ ሊባኖስ
ሲኖዳ ማለት ተአምኒ ምለት ነው። ሀገሩ እስክንድርያ ነው። አባት እናቱ ሠንላል የሚባል ቦታ ይኖሩ ነበር። አንድ ቀን እናቱ ውሃ ልትቀዳ ስትሄድ አባ ክርስሳርዮስ ደቀመዛሙርቱን አስከትሎ ሲሄድ አገኛት ቡርክት አንቲ ወቡሩክ ፍሬ ከርስኪ ለቀደሙት ቅዱሳን ወንድማቸው ለኋለኞችም አባታቸው የሚሆን ቡሩክ ፍሬ በማኅፀንሽ አለና የተባረክሽ ነሽ ብሎ 3 ጊዜ ራሷን ሳማት። ደቀመዛሙርቱ አባታችን ሴት አነጋግሮ አያውቅም ነበር ዛሬ ምን ሆኗል? አሉ ይህን አውቆ የልጇን ክብር ነግሯቸዋል።
ያደገው ያባቱን በጎች ሲጠብቅ ነው። ሌሊት መንጋውን አሰማርቶ እሱ ከጉድጓድ ገብቶ ሲጸልይ ያድር ነበር። አንድ አረጋዊ ከጉድጓድ ገብቶ ሲጸልይ አሥሩ ጣቶቹ እንደ ፋና ሲያበሩ አይቶ አባት እናቱን እንዲህ ያለ ደግ የወለዳችሁ ምን ብጹዓን ናችሁ አላቸው። እንዲህማ ከሆነ የእግዚአብሔር እንጂ የኛ አይደለም ብለው ለመምህር ሰጡት ሲሰጡትም ናሁ ይሰመይ አርስመቅሪዶስ ለኩሉ ዓለም እነሆ የባሕታውያን ራስ ይባላል የሚል ድምጽ ከወደላይ ተሰምቷል። ከዚህ በኋላ እየተማረ እያገለገለ በጾም በጸሎት ተወስኖ በትኅርምት ኗሪ ቢሆን መልአኩ የኤልያን አስኬማ የዮሐንስን ቅናት ሲሰጠው መምህሩ በራዕይ አየ በማግስቱም የሰጠሁህን ለሲኖዳ አልብሰው አለው መዓረገ ምንኩስና ሰጥቶታል።
በ431 ዓ.ም ለአውግዞተ ንስጥሮስ በቁስጥንጥንያ በተደረገው ጉባዔ ቅዱስ ቄርሎስን ተከትሎ ተገኝቷል። ንስጥሮስን አውግዘው ሃይማኖት መልሰው ሲመለሱ መርከበኞች ሊቀ ጳጳሳቱ በተሳፈረበት መርከብ አትሳፈርም ብለው ከለከሉት ጌታ ብሩህ ደመና አዞለት በዚያ ተጭኖ ሲሄድ በመርከቡ አንጻር ሲደርስ የመርከቡ ጣሪያ እንደመስታወት ሆኖላቸው እሱና ሊቀጳጳሳቱ ተያይተው እጅ ተነሣስተዋል። እኒያም ክብሩን አይተው ደግ ሰው አስቀይመናል ብለው ተጸጽተዋል። በመጨረሻም በስሙ ጥርኝ ውኃ ለደኃ እስከመስጠት ድረስ በጎ የሠራውን እንደሚምርለት ጌታ ቃል ኪዳን ሠጥቶት ሕማም ድካም ሳይሰማው በተወለደ በ120 ዓመቱ ዐርፏል። የጻድቁ ምልጃና በረከት በሁላችን ላይ አድሮ ይኑር አሜን።

ሐምሌ 6

በዚህች ቀን ዕዝራ ሱቱኤል ልክ እንደ አባቶቹ ሄኖክና ኤልያስ ሞትን ሳይቀምስ ወደ ብሄረ ህያዋን የተወሰደበት ቀን ነው፤ይህ ነብይ ቅዱስ ኡራኤል እሳት የመሰለ የጥበብን ጽዋ ካጠጣው በኃላ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ጠፍተው የነበሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በ 40 ቀናት ውስጥ በድጋሚ ጻፋቸው፤ በረከቱ ይደርብን

እንኳን አደረሳችሁ፤ ሐምሌ 5

በዚህች ቀን የቤተክርስቲያን አዕማድ የዓለም ብርሃን የሆኑት ሊቀ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በሮም አደባባይ በኔሮን እጅ በሰማዕትነት አረፉ፤ ቀዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተሰቅሎ ነፍሱ እስክትወጣ ለህዝቡ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፤ ቅዱስ ጳውሎስን አንገቱን ሰይፈው ገደሉት፤ ሩጫቸውን ጨረሱ ሃይማኖታቸውንም ጠበቁ በዛሬዋ ዕለት የክብር አክሊልንም ተቀበሉ። በረከታቸው ይደርብን


ሐምሌ 4

በዚህች ቀን በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን የነበረው ነብዩ ሶፎንያስ አረፍ፤ ይህ ነብይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ሶፎንያስን የጻፈው ነው፤ ስለ ኢትዮጰያም ደጋግሞ ትንቢቶችን ተናግሯል፤ "ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል" ሶፎ 3 ፤ 9-10። በረከቱ ይደርብን፤

ሐምሌ 3

በዚህች ቀን ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ አባ ቂርሎስ አረፈ። ይህ ሊቅ አገሩ ሶርያ ነው፤ ግን ልብ በሉ የእስክንድርያ 23ኛ ጳጳስ ሆኖ ተሹሟል። ልክ ነው እንደዚያ ነበራ በደጉ ዘመን ከየት ነህ ከወዴት መጣህ አይሉም አጥንት አይቆጥሩም ደም አያንቆረቁሩም ነበር፤ ቅድስናው እውቀቱ ስንምግባሩ ከተመሰከረለት፤ ለመሾም የአዳም ዘር ብቻ መሆን ይበቃል። እሺ አባ ቂርሎስ መናፍቁ ንስጥሮስን ተከራክሮ የረታ ድንቅ አባት ነው፤ ቀድሞ ንስጥሮ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ነበር፤ መቼም አያድርስ ነው ይህ ጳጳስ ሳተ ተሳሳተ አሳሳተ እመቤታችን ወላዲተ አምላክን ወላዲተ ሰብ እንጂ ወላዲተ አምላክ አይደለችም አለ፤ ለዚህም ጉባዬ በኤፌሶን ከተማ ተደረገ፤የወቅቱ ንጉስ ቴዎዶስዮስ ነበር፤ የተሰበሰቡት ሊቃውንት ደግሞ 200 ናቸው ሊቀ መንበሩ ቂርሎስ ነው፤ ክርክሩ ተጀመረ፤ አባ ቂርሎስ እንደ ሰይፍ የሚቆራርጡ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ መወርወር ጀመረ፤ ንስጥሮስ የሚመልሰው አጣ ተረታ፤ ወደ ቀደሞ ሃይማኖትህ ተመለስ አሉት አልመለስም ብሎ ወደ ላይላይ ግብጽ ይሰደዳል፤ ቂርሎስ መልካም ባልንጀራው ነበርና ተከትሎት ሄዶ ይመክረዋል ወንድሜ ንስጥሮስ የያዝከው መንገድ ስህተት ነው፤ እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ ነች ልጇም የባህርይ አምላክ ነው በል ይለዋል፤ መቼም ያዲያቆነ ስየጣን ነውና አልልም ብሎ ይመልስለታል፤ እንግዲያውስ ለኔ እንዳልታዘዘክ አንደበትህ አይታዘዝህ ብሎ ይረግመዋል ወዲያውኑ ምላሱ ተጎልጉሎ ወጣ ደምና መግል እየተፋ ተቀብዝብዞ ሞቷል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የአሁኑ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀውስጦስ በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ተአምር አድርገዋል ቦታው በዚሁ በምዕራቡ የአገራችን ክፍል በአንድ ቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ ቆመው ሲያስተምሩ አንድ መናፍቅ ተንደርደሮ አውደ ምህረቱ ላይ ይወጣና በልሳነ መናገር ይጀምራል አቡነ ቀውስጦስም ወንድሜ መስበክ ከፈለክ ሁላችንም በምንሰማው ቋንቋ ተናገር ይሉታል መረበሽ ጀመረ ቢመክሩት እምቢ አለ እንግዲያውስ ወላዲተ አምላክ አንደበትህን ትዝጋው ይሉታል ወዲያው አንደበቱ ተያዘ መናገር ተሳነው፤ ከዚያ በኃላ የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው እግራቸው ላይ ወድቀው አባታችን ይማሩት አሏቸው፤ ጸሎት አድርገው አንደበቱን ፈተውታል፤ ይህ እውነት ነው፤ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ አባ ቂርሎስ በርካታ መጽሐፍትን ጽፏል ከነዚህም አንዱ ቅዳሴ ቂርሎስ ነው ሃይማኖተ አበው ላይም ስለ መለኮት ገራሚ ገራሚ ነገሮች ተናግሯል፤ 32 ዓመት በማርቆስ መንበር መንጋውን በፍቅር ጠብቆ ሐምሌ በባተ በ 3ኛው ቀን አርፏል። በረከቱ ይደርብን፤ ቅዳሴ አንድምታ፤ ስንክሳር። በረከቱን ይደርብን።

ሐምሌ 2

በዚህች ቀን ከ 12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ሐዋርያው ታዲዎስ አረፈ። ዓለምን ዞራችሁ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ በተባሉት መሰረት ሐዋርያት ዓለምን በእጣ ሲከፋፈሉ ለዚህ ሐዋርያ ሶርያ ደረሰችው፤ ዛሬ የእርስ በእርስ እልቂት ያለባት አገር፤ ይህ ሐዋርያ እጅግ ድንቅ ታአምራት በሶርያ ምድር አድርጓል፤ ነገሩ እንዲህ ነው፤ አንድ ትዕቢተኛ ሰይጣን ያደረበት ባለጸጋ ቀርቦት መምህር ሆይ በመጽሐፍ ቅዱሳችሁ ሀብታም መንግስተሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል ይላል፤ እስኪ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ እውነት ከሆነ አድርገህ አሳየን ይለዋል፤ ሐዋርያው ታዲዎስም መርፌ የሚሰራ ባልንጀራ ነበረውና መርፌ እንዲልክለት ሰው ይሰዳል ያ መርፌ ሰሪም ሐዋርያውን ለመርዳት አስቦ ቀዳዳውን ትንሽ አስፍቶ ይልክለታ፤ ታዲዎስም ፈገግ አለ የመርፌ ቀዳዳ ምን ቢሰፋ እንዴት ግመል ያሳልፋል ስለውለታህ አመሰግናለው ትክክለኛውን መርፌ ላክሊኝ ብሎ ይመልስለታል እርሱ ድጋሚ አስተካክሎ ይልክለታል፤ ከዚህ በኃላ አገሬው በአደባባይ ተሰበሰበ ጭነት የያዘች ግመልና አንድ ነጋዴም ተዘጋጁ ሐዋርያው ዓይኑን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ አምላኬ ሆይ ይህን የማደርገው ክብርህ እንዲገለጽ እንጂ ክብሬ እንዲገለጽ ብዬ አይደለም ጸሎቴን ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለው አለ፤ ጸሎቱን እንደጨረሰ ጭነት የተሸከመችውን ግመል እንድታልፍ አደረጋት ሰው ሁሉ እያያ በመርፌው ቀዳዳ ሾለከች አገሬው እልልታውን አቀለጠው ለሁለተኛ ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜም እንድትሾልክ አደረገ፤ ህዝቡ ይህን የእግዚያብሔር ድንቅ ተአምራት አይቶ ብዙዎች አመኑ ተጠመቁም፤ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ እንደዚህ ያለ ተአምራት ያየ ማን አለ እኛ ግን ከሶርያ ህዝብ ጋር አየን ተመለከትን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንዳለ " በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ያደርጋል ከእኔም በላይ ያደርጋል" ግሩም ነው የፈጣሪ ስራ። ሐዋርያው ቅዱስ ታዲዎስ በብዙ አገር ተዘዋውሮ ሲያስተምር ጣኦት አምላኪዎች ይዘው አሰቃዩት በዛሬዋ ቀንም ገድለውታል እርሱም የሰማዕትነት አክሊል ተቀብሏል። ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም ከሐዋርያው በረከት ያሳትፈን። ስንክሳር፤ ገድለ ሐዋርያት።

ሰኔ 30

በዚህች ቀን የጌታን መንገድ ጠራጊው፤ሐዋርያው፤ነብዩ ሰማዕቱ ቅዱስ ዮሐንስ የልደት ቀኑ ነው፤ መስከረም 2 አንገቱ የተቆረጠበት ነው ሚያዚያ 15 እረፍቱ ነው፤ አንገቱ ከተቆረጠ በኃላ የተቆረጠች አንገቱ ክንፍ አውጥታ ለ15 ዓመት በሳውዲአረቢያና አካባቢው ወንጌልን ሰብካለች፤ የካቲት 30 ቀን የዮሐንስ ራስ የተገለጸችበት ቀን ነው። ከነዚህ አራት በዓላት ሁለቱን ቤተክርስቲያን ታቦተህጉን አውጥታ በደማቁ ታከብረዋለች እነዚህም ሰኔ 30 ልደቱና መስከረም ሁለት አንገቱ የተቆረጠበትን ቀን ነው።ጨካኝ ሄሮድስ የቤቴልሔም ህጻናትን ሲጨፈጭፍ መጥምቁ ዮሐንስ ከአናቱ ከቅድስት ኤልሳቤጥ ጋር ወደ ሲና በርሃ ተሰደደ፤ኤልሳቤጥ በጣም አርጅታ ነበር ያን በርሃ ታዲያ እንዴት ቻለችው ያውም ልጅ አዝላ ልጅ ተሸክማ ረዳት ሳይኖራት ብቻዋን፤አባቱ ዘካርያስ በምኩራብ በመሰዊያው ፊት ልጅህን አምጣ ብለው አንገቱን ቆርጠው ገደሉት። ኤልሳቤጥም ሲና በርሃ ላይ ሞተች ህጻኑ ዮሐንስ ብቻውን ቀረ፤ የእናቱን በድነ ስጋ አቅፎ አለቀሰ፤ሁሉን ቻይ ሁሉን የሚያይ፤ ሁሉን የሚመረምር ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለእመቤታችን እናቴ ሆይ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ በበርሃ አርፋለች እንቀብራት ዘንድ እንሂድ አላት ደመና ጠቅሰው ዮሴፍና ሰሎሜን አስከትለው ሄደዋል ገንዘውም ቀብረዋታል፤ ከዚህ በኃላ እመቤታችን ልጄ ወዳጄ ሆይ ዮሐንስን ይዘነው እንሂድ አለችው የለም እናቴ ፤እርሱ እዚው ይቆያል መንገዴን ጠራጊ ነው፤ ኑሮው በዚሁ በርሃ ነው፤ጊዜው ሲደርስ ወደ ዮርዳኖስ ይመጣል ያጠምቀኝማል ያኔ አንድነቴ ሶስትነቴ ይገለጣል አላት፤ ትተውት ተመለሱ ከመሞቱ በፊት እናቱ ያሰፋችለትን የግመል ቆዳ አገልድሞ አንቦጣ የሚባል ቅጠልና የበርሃ ማር እየበላ በበርሃ ኖረ 30 ዓመት ከ 6 ወር ሲሆነው፤ “የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ” እያለ ከበርሃ ወጣ ሉቃ 3፤3። "እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤" ማቴ 11፤11። ይህ የጌታችን ምስክርነት ነው። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

ሰኔ 29



ይህ ቀን የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ ነው፤ አባቶቻችን ባዘዙት መሰረት የቤተክርስቲያን ልጆች በየወሩ ልክ እንደ እሁድ ሰንበት አክብረውት ይውላሉ፤ልጁን ለላከ ለአብ ለተላከ ለወልድ ማህያዊ ለሚሆን መንፈስ ቅዱስም ክብር ምስጋና ይሁን።

Thursday, July 3, 2014

ሰኔ 27

ሰኔ 27 በዚህች ቀን ታሪኩ በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 9፤10 ላይ የተጠቀሰው ሐዋርያው ሐናንያ አረፈ። ቀድሞ ሳኦል የተባለው ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ ድንገት በደማስቆ ታላቅ ብርሃን ይመታዋል በምድር ይወድቃል ዓይኑም ይታወራል፤ “ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል ይለዋል፤ ለ 3 ቀን 3 ሌሊት ዓይነስውር ሆኖ ይቆያል።ከዚያም የዛሬዋን ቀን መታሰቢያውን የምናደርግለት ሐዋርያው ሐናንያ እጁን ጭኖ ጸለየለት ዓይኑንም አበራለት ከዚያ በኃላ ነው ቅዱስ ጳውሎስ የቤተክርስቲየን ምርጥ እቃ የሆነው። ሐዋርያው ሐናንያ በደማስቆ ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን ወደቀናች ሀይማኖት መለሳቸው፤የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ከዚህ በኃላ አረመኔው ንጉስ ሉክያኖስ ይዞ ብዙ መከራ አደረሰበት፤ አስገረፈው፤ በእሳት አቃጠለው፤ በፍላጻ አስነደፈው፤ በመጨረሻም በዛሬዋ ቀን በድንጋይ አስወግሮ ገድሎታል። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል 16፤20 ታሪኩን የተናገረለት ዓልአዛር አረፈ። እንዲህ ይላል “… አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት ይላል የዚህ ጻድቅ እረፍቱ ዛሬ ነው፤ ይህም ሰኔ 27 የሚነበበው ስንክሳር ላይ ተጽፏል።ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም የአባቶቻችንን በረከት ያሳትፈን። 
LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 25

ሰኔ 25 
በዛሬዋ ቀን ከሰባሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነው የፀራቢው የዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ይሁዳ አረፈ፡፡ ይህ ሐዋርያ በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ምዕራፍ ብቻ ያለው የይሁዳ መልዕክትን የጻፈ ነው፤ በተለያዩ አገሮች በመዞር ህዝቡን ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚያብሔር መለሰ ብዙዎችንም ክርስቲያን አደረገ፤ በመጨረሻም ሐራፒ በሚባል አገር ገብቶ ሲያስተምር ጣኦት አምላኪዎች ይዘው አሰቃዩት፤ሰቀሉት በዛሬዋም ቀን በፍላጻ ነድፈው ገደሉት፤ቅድስት ነፍሱን ሰጠ፡፡ በረከቱ ይደርብን
LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 24

ሰኔ 24 በዚህች ቀን ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አባ ሙሴ ጸሊም አረፈ፡፡ አስቀድሞ ሽፍታ ወንበዴ ዘማዊ ጣኦት አምላኪ ነበር፤ በኃላ እንደ አብርሃም አምላኬ ማን ነው ብሎ ተመራመረ፤ ወደ አስቄጥስ ገዳም ብትሄድ አምላክህ ማን እንደሆነ ይነግሩሃል የሚል ራዕይ አየ ተመለከተ፤ ተነስቶም ሄደ አባ ኤስድሮስን አገኛቸው፤አጽናንተው አረጋግተው ወደ አባ መቃርስ ወሰዱት አባ መቃርስም ንስሃውን ተቀብለው ቀኖና ሰጡት ኃላም አመነኮሱት የሽፍቶች አለቃ የነበረው የመነኮሳት አለቃ እስከመሆን ደረሰ፤ ሰይፉን ወርውሮ ከፍቅር ጋር ተወዳጀ፤ሌሊት እየተነሳ ለሁሉም መነኮሳት ውኃ ይቀዳላቸው ነበር ሉሉም ይታዘዛቸው ነበር ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይህን አድርግሊኝ ይሉታል አርሱም ሁሉንም እሺ ይላል፤ ራሱን ዝቅ አደረገ ትሁትም ሆነ፤ በጸሎቱ ዝናብ ያዘንብ ነበር፤ እድሜው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ሊቀበል ከመነኮሳት ጋር ሆኖ ወደ አባ መቃርስ ሄደ አርሳቸውም ልጆቼ ከናንተ መካከል በሰማእትነት የሚሞት አለ ብለው ትንቢት ተናገሩ ሙሴ ጸሊምም አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ የሚል ቃል አለ ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠባበቀው ነበር አላቸው፤ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ሊያጠፉ መጡ መነኮሳቱ ሲሸሹ ሙሴ እዚያው ቀረ ሌሎች ሰባት መነኮሳት ከአባታችን ጋር እንሞታለን ብለው አብረውት ሆኑ የበርበር ሰዎች ደረሱ ሁሉንም በሰይፍ ገደሏቸው፤ ይህም ሰኔ 24 ቀን ነው፤ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ስጋው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፤ ግብጻውን ቤተክርስቲያን ሰርተውለት ታቦት ቀርጸውለት በደንብ ያከብሩታል ገድሉን ጽፈውለታል ፊልምም ሰርተውለታል ይህን ፊልም የኛ ሰዎች ግሩም አድርገው ወደ አማርኛ መልሰውታል፡ የቻለ ገድሉን ያንብብ ያልቻለም ፊልሙን ይመልከተው፤ የዛሬዋን ቀን ስለ ተክለሃይማኖት ብቻ በለን አንመጽውት ስለ ሙሴ ጸሊምም እያልን ይሁን፤ አምላከ ተከልዬ ጠብቀኝ ስንል አምላከ ሙሴ ጸሊም አትርሳኝ ማለትን አንርሳ ይህ ድንቅ አባት የማይረሳ ነውና፡፡ ሙሴ ጸሊም ማለት ሙሴ ጥቁር ሰው ማለት ነው፤ መልኩ ጥቁር ስለሆነ ነው ጥቁሩ ሙሴ ተብሎ የተጠራው፤ እገሌ ጥቁር ሰው እገሌ ጥቁር ስው አሁን የመጣ አይደለም፤ ኳስ መቶ ጎል ያገባ በሙሉ እገሌ ጥቁር ሰው መባል ጀምሯል፤ ቤተክርስቲን ግን ጥንቱንም ቢሆን አንዱን ቅዱስ ከአንዱ ለመለየት ቅጽል ስም ትሰጣለች ለምሳሌ ዮሐንስ አጺር አጭሩ ዮሐንስ ስምኦን ጫማ ሰፊው ሙሴ ጸሊም ጥቁሩ ሰው ሙሴ……ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 23

ሰኔ 23 
በዚህች ቀን የዳዊት ልጅ የቤርሳቤህ ልጅ ጠቢቡ ሰሎሞን አረፈ። በ 12 ዓመቱ ሲነግስ እግዚያብሔርን አንዲት ነገር ለመነው ፍርድ እንዳልገመድል ደሃ እንዳልበድል ጥበብን ስጠኝ ብሎ የልቡን መሻት ሰጠው ፍጹም ጠቢብም አደረገው፤ለ 40 ዓመት በቅን እየፈረደ በንግስና ቆይቶ በ 52 ዓመቱ በዛሬዋ ቀን አረፈ።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 20

ሰኔ 20 ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ህንጸተ ቤተክርስቲያን ይባላል። የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የታነጸው በዛሬዋ ቀን ነው አናጺውም እራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ቦታው ፊልጰስዩስ ነው፤ ቤተክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው። ጴጥሮስ፤ ዮሐንስ በርናባስና ሌሎችም ሐዋርያት በፊልጰስዩስ ተሰብስበው ሳለ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል እመቤታችን በቀኙ ነበረች፤ 3 ድንጋዮችን አንስቶ ጎተታቸው እንደ ሰም ተለጠጡ እንደ ግድግዳም ሆኑ ዳግመኛም የብርሃን ምሰሶ ወረደ በሰማያዊቷ እየሩሳሌም እምሳያ አድረጎ አነጻት ሁለንተናዋም ተጠናቀቀ፤ ዳግመኛ በበነጋው ሰኔ 21 ቀን እመቤታችንን እና ቅዱሳን መልአክትን አስከትሎ ይወርዳል ቅዳሴ ቀድሶ ለሐዋርያቱ አቆረባቸው ፍጹም ደስታም ሆነ። ከዚህ በኃላ ሐዋርያት ከጌታ እንዳዩት በዓለም ዞረው ቤተክርስቲያን አንጸዋል። ከዚያ በፊት የነበረው የነሶሎሞን ቤተመቅደስ የአይሁድ ምኩራብ የአይሁድ ስርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ እንጂ የአዲስ ኪዳን የቁርባንም ሆነ የጥምቀት ስርዓት መፈጸሚያ አልነበረም፤ ታዲያ ሐዋርያት የት ነበር ህዝቡን የሚያጠምቁት የሚያቆርቡት ካሉ በየሰው ቤት ነበር። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ታላቁ ነብይ ኤልሳዕ አረፈ። ይህ ነብይ በ 12 ጥማድ በሬ ሲያርስ ቴስቢያዊው ነብዩ ኤልያስ ተከተለኝ አለው ምንም ሳያቅማማ ሀብት ንብረቱን ትቶ ተከተለው፤ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ከማረጉ በፊት ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ ይለዋል ባንተ ላይ ያደረ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ድርብ ሆኖ ይደርቢኝ ይለዋል፤ እንደ ቃሉ ሆነለት ተደረገለት፤ ኤልያስ አንድ ሙት ሲያስነሳ ኤልሳዕ ሁለት ሙት አስነስቷል፤ ኤልያስ አንድ ጊዜ ባህር ሲከፍል ኤልሳዕ ሁለት ጊዜ ባህር ከፍሏል። እምቤታችንን የኤልሳዕ ጋን ይላታል ኤልሳ የመረረውን ውኃ እንዳጣፈጠ እመቤታችንም ይህን መራራ ዓለም ጌታን በመውለዷ አጣፍጣዋለች፤ የዚህ ነብይ ድንቅ ታሪኩ 2ኛ ነገስት ላይ በስፋት ተጽፏል ሰኔ 20 ቀን እረፍቱ ነው ቤተክርስቲያን የዛሬውን ቀን እመቤታችንን እና ነብዩን አስባ ትውላለች። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 12

ሰኔ 12 በዚህች ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ከሰይጣን እጅ ያዳነበት ቀን ነው። ዳግመኛም በዛሬዋ ቀን ጻድቁ ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ያረፈበት ቀን ነው። ቅድስት አፎምያ የቅዱስ ሚካኤልን ዝክር ታዘክር ነበር ለድሆችም አብዝታ ትረዳ ነበር፤ በዚህ ሰይጣን ቀናባት በመነኩሴ ተመስሎ ሊያስታት ሞከረ በቅዱስ ሚካኤል ስዕል አሳፍራ መለሰችው ከ 3 ወራት በኃላ ሰኔ 12 ቀን ዳግመኛ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ ብሎ ሊፈትናት መጣ፤ ሚካኤል ከሆንክ መስቀልህ የት አለ አለችው ከዚህ በኃላ አፉን ከፍቶ አይኑን አጉረጥርጦ አንገቷን አነቃት “ቅዱስ ሚካኤል ድረስልኝ” ብላ ተጣራች ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ፈጥኖ ወረደ በበትረ መስቀሉም መታው ጊዜዬ ሳይደርስ አታጥፋኝ ስዕልህ ባለበት፤ ስምህ በተጠራበት፤ ድርሳንህ በሚነበብበት፤ ፈጽሞ አልደርስም ብሎ ማለ፤ ተገዘተ ሸሸም፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ሚካኤል ቅድስት አፎምያን “ወዳጄ አፎምያ ባነቺ ደስ አለኝ ወጋሽ በሰማይ ታላቅ ነው” ብሎ ባርኳት አርጓል። ቅዱስ ላሊበላ (ላልይበላል) ላል ማለት ማር ማለት ነው፤ሲወለድ በንብ ተከቦ ነበርና ማር ይበላል “ላልይበላል” አሉት ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ትባላች እረፍቷ ሐምሌ 27 ነው ልጁ ይትባረክ እረፍቱ መስከረም 24 ቀን ነው ቅዱስ ላሊበላ 40 ዓመት ኢትዮጰያን አስተዳደረ ዓለምን የሚያስደንቅ እጹብ እጽብ የሚያሰኝ ከአንድ አለት ብቻ እጀታ በሌለው መጥረቢያ 12 ውቅር አብያተክርስቲያናትን አነጸ፤ እነዚህ በአንድ ቦታ ስላሉ ነው እንጂ በወሎ በጎንደር በሸዋ ለቁጥር የሚበዙ አብያተክርስቲያናትን አንጿል፤ ታህሳስ 29 ቀን ተወልዶ በ 80 ዓመቱ ሰኔ 12 በዛሬዋ ቀን አርፏል። መጨረሻ ያነጸው ቤተክርስቲያን አዳዲ ማርያምን ነው፤ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ናቸው እንዲያንጽ የጠየቁት እርሱም ጀምሮ ሳይጨርስ አቡነገብረመንፈስ ቅዱስ ወደርሱ ቀርበው ወዳጄ ላሊበላ የእረፍትህ ቀን ደርሷልና ወደ ላስታ ተመለስ አሉት እርሱም ተመለሰ በዚያም አረፈ፤ እራሱ ባነጸው በቤተ ጎሎጎታ ተቀበረ በመቃብሩም ላይ ለ 10 ቀን የማይጠፋ ብርሃን ሲበራ ይታይ ነበር። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።


LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 11

በዚህች ቀን ከሰባቱ ዓበይት ሰማዕታት አንዱ የሆነው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዲዎስ አረፈ። ስንክሳሩ የመልአክት አርአያ ያለው ይለዋል ንጽህናውን ቅድስናውን ሲያጠይቅ፤ የሮም የነገስታት ልጅ ነው ዓለምን ክብሩን ሁሉ ንቆ ወጣ በፍጹም ተጋድሎም ኖረ ለጣኦት አልሰግድም አልሰዋም ብሎ ሰው ሊሰማው የሚከብድ ጽኑ መከራዎችን በትእግስት ተቀበለ በዛሬዋ ቀንም አንገቱን ተቆርጦ በሰማዕትነት አረፈ። ሰኔ 11 ቀን የሚነበበው ስንክሳር ታሪኩን በሰፊው ጽፎታል፤ ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ ይህ ሰማዕት በተለይም በጎንደር ልዩ ክብር እንዳለውና በስሙ ታላላቅ ገዳማት እንደታነጹለት በአጠቃላይ ኢትዮጰያ ውስጥ ከ 16 የማያንሱ አብያተክርቲያናት እንዳሉት “የቅዱሳን ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፤ በነገራችን ላይ በዚሁ ስም የሚጠሩ ታላቅ የኢትዮጰያ ጻድቅ ንጉስም አሉ ዓጼ ገላውዲዎስ ግራኝ መሐመድን ድል የነሱ ናቸው ቤተክርስቲያን መታሰቢያቸውን መጋቢት 27 ቀን ታከብረዋለች። የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን የቤተክርስቲያን ማረጃዎች የሚለውን መጽሕፍ ይመልከቱ ።ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 9

ሰኔ 9 በዚህች ቀን ከተራራማው ከአፍሬም አገር አርማቴም ከተባለ ቦታ የወጣው የሐና ልጅ ታላቁ ነብይ ሳሙኤል አረፈ። ይህ ነብይ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ገልአርታ ውስጥ ታቦት እንዳለው ሊቀ ብርሃናት መርቆርዮስ አረጋ የቅዱሳን ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል። ነብዩ ሳሙኤል በብዙ እንባ በታላቅ ትዕግስት የተገኘ ነብይ ነው ሐና መካን ሆና ለረጅም ዘመን ታለቅስ ነበር ሰዎችም ይዘባበቱባት ነበር ይህች የበቅሎ ዘመድ ቢወልዷት እንጂ የማትወልድ በኃጢያቷ ብዛት እየው እግዚያብሔር ልጅ ነሳት፤ደግሞ እኮ አታፍርም ወደ ቤተ እግዚያብሔር ትሄዳለች ይሏት ነበር፤ ከእለታት በአንዱ ቀን እጇን ወደላይ አንስታ ከንፈሯን እያንቀሳቀሰች በለሆሳስ እያለቀሰች ስትጸልይ ተመልክቶ ካህኑ ዔሊ ሳይቀር አንቺ ሰካራም በሎ ዘለፋት 1ኛ ሳሙ 1፤14። እግዚያብሔር ግን ጸሎቷን ሰማት እንባዋን አበሰላት ከልጅ በላይ ልጅ ሰጣት እርሷም እንዲህ ብላ ግሩም ምስጋና አመሰገነች ይህንን የሐና ምስጋና ቤተክርስቲያን ዘወትር ትጠቀምበታለች መዝሙረ ዳዊት የጸሎት መጽሐፍ ካልዎት ይህንን ምስጋና እዚያ ላይ ያገኙታል፤ ልቤ በእግዚአብሔር ጸና ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ በማዳንህ ደስ ብሎኛል። እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና ከአንተ በቀር ቅዱስ የለም። አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። ኡፈየው እንዴት ያለ ጣፋጭ ምስጋና ነው፤1ኛ ሳሙ 2፤1። ነብዩ ሳሙኤል ሳኦልን ከአህያ ጠባቂነት ጠርቶ በእስራኤል ላይ ያነገሰ ነው ዳዊትን ደግሞ ከእረኝነት ጠርቶ ለእስራኤል ያነገሰ ነው፤ ሳኦልን በእስራኤል ዳዊትን ለእስራኤል “በ” እና “ለ” የእነዚህን ቃላት ልዩነት የሐሙስ ውዳሴ ማርያም አንድምታው ላይ በስፋት ተጽፏል፤ ነብዩ ሳሙኤል በ 98 ዓመቱ አረፈ እስራኤልም ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፥ በአርማቴምም በቤቱ ቀበሩት። 1ኛ ሳሙ 25፤1

LIKE OUR PAGE >>>

ሰኔ 8


ከእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላት አንዱ ነው፤ በዚህ ዕለት ልጇ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ግብጽ በስደት ሳሉ ለህሙማን ድህነት እንዲሆን ውኃን ከዓለት ላይ ያፈለቀበት ቀን ነው፤በዚሁ ቦታ በእመቤታችን ሥም ታላቅ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ የተከበረበትም ቀን ነው፡፡እመቤታችንን ከፍጥረት ዓለም ለይቶ አክብሮ የእናት አማላጅ አድርጎ የሰጠን እግዚያብሔር ይመስገን፡፡
ከተአምር አስቀድሞ ይህ ይነበብ ህዝቡ ዕዝነ ልቦናቸውን ከፍተው ይስሙ፤ በዕብራይስጥ ማርያም የተባለች የእመቤታችንን ተአምር ለመስማት ቀላል አይምሰለው የከበረ ገናና ነውና ወደ ግዝት እንዳይገቡ መስማትን አያስታግሉ ፤ በእመቤታችን ሠላሳ ሦስቱ ባዓላትና እሁድ በተባለች ሰንበት ወንዶችም ሴቶችም ወደ ቤተክርስቲያን ይሰብሰቡ የተአምሯን መጽሐፍም ያንብቡ፤ ዛሬ ሰኔ 8 ቀን ከእመቤታችን 33ቱ በዓላት አንዱ ነው፤ ይህም በስደታቸው ወራት ልጇ ከደረቅ አለት ላይ ውኃን ያፈለቀበት ቀን ነው። ይህ ውኃ እንደ ማር እንደ ወተት የጣፈጠ እንደ ወተትም የነጻ ነው፤ ከዚህ ውኃ የጠጣ ሁሉ ይፈወስ ነበር። ታሪኩ እንዲህ ነው የግብጽ በረሃ በጣም ሲያደክማቸው ከአንድ መንደር ያርፋሉ በዚያም ጌታ ውኃ ይጠማዋል ይህን ባየች ጊዜ እምቤታችን ከመንደሩ ሴቶች ውኃ ልትለምን ሄደች፤ ዮሴፍና ሶሎሜ ግን ደከሟቸው ተኝተው ነበር፤ ውኃ የሚሰጣት የሚመጸውታት ስታጣ ልቧ በሐዘን ተወግቶ ተመልሳ መጣች ጌታን ከተቀመጠበት አንስታ ታቀፈችው ስቅስቅ ብላም አለቀሰች ህጻን ጌታም የእናቱን እንባ ከጉንጮቿ ላይ በእጆቹ ጠረገላት ትንሽዬ ጣቱን (ማርያም ጣት የምንለውን ነው ወደ ምድር አመለከተ ወዲያውኑ ጣፋጭ ውኃ ከአለት ላይ ፈልቆ ጠጡ፤ እንዲህም አለ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለድህነት ይሁነው ብሎ ባረከው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጠጣው ሁሉ ከደዌው ይፈወስ ነበር፤ አሁንስ ይኖር ይሆን ? እንጃ፤ የጠፋ በግ አዳምን የፈለገው ባገኘውም ጊዜ የተሸከመው እውነተኛ ቸር ጠባቂያችንን የወለድሽልን እመቤቴ ማርያም ሆይ ሠላምታ ይገባሸል የሄዋን ጽኑ የሚጎዳ ማሰሪያዋ ባንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ውዳሴም ይገባሻል እኛ ከምንወደው እርሱም ከሚወደን ልጅሽ ይቅርታ ያደርግልን ዘንድ ለምኝልን።

LIKE OUR PAGE >>>