Sunday, July 13, 2014

ሐምሌ 3

በዚህች ቀን ታላቁ የቤተክርስቲያን ሊቅ አባ ቂርሎስ አረፈ። ይህ ሊቅ አገሩ ሶርያ ነው፤ ግን ልብ በሉ የእስክንድርያ 23ኛ ጳጳስ ሆኖ ተሹሟል። ልክ ነው እንደዚያ ነበራ በደጉ ዘመን ከየት ነህ ከወዴት መጣህ አይሉም አጥንት አይቆጥሩም ደም አያንቆረቁሩም ነበር፤ ቅድስናው እውቀቱ ስንምግባሩ ከተመሰከረለት፤ ለመሾም የአዳም ዘር ብቻ መሆን ይበቃል። እሺ አባ ቂርሎስ መናፍቁ ንስጥሮስን ተከራክሮ የረታ ድንቅ አባት ነው፤ ቀድሞ ንስጥሮ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ ነበር፤ መቼም አያድርስ ነው ይህ ጳጳስ ሳተ ተሳሳተ አሳሳተ እመቤታችን ወላዲተ አምላክን ወላዲተ ሰብ እንጂ ወላዲተ አምላክ አይደለችም አለ፤ ለዚህም ጉባዬ በኤፌሶን ከተማ ተደረገ፤የወቅቱ ንጉስ ቴዎዶስዮስ ነበር፤ የተሰበሰቡት ሊቃውንት ደግሞ 200 ናቸው ሊቀ መንበሩ ቂርሎስ ነው፤ ክርክሩ ተጀመረ፤ አባ ቂርሎስ እንደ ሰይፍ የሚቆራርጡ ቃላትን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሰ መወርወር ጀመረ፤ ንስጥሮስ የሚመልሰው አጣ ተረታ፤ ወደ ቀደሞ ሃይማኖትህ ተመለስ አሉት አልመለስም ብሎ ወደ ላይላይ ግብጽ ይሰደዳል፤ ቂርሎስ መልካም ባልንጀራው ነበርና ተከትሎት ሄዶ ይመክረዋል ወንድሜ ንስጥሮስ የያዝከው መንገድ ስህተት ነው፤ እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ ነች ልጇም የባህርይ አምላክ ነው በል ይለዋል፤ መቼም ያዲያቆነ ስየጣን ነውና አልልም ብሎ ይመልስለታል፤ እንግዲያውስ ለኔ እንዳልታዘዘክ አንደበትህ አይታዘዝህ ብሎ ይረግመዋል ወዲያውኑ ምላሱ ተጎልጉሎ ወጣ ደምና መግል እየተፋ ተቀብዝብዞ ሞቷል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የአሁኑ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቀውስጦስ በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ተአምር አድርገዋል ቦታው በዚሁ በምዕራቡ የአገራችን ክፍል በአንድ ቤተክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ ቆመው ሲያስተምሩ አንድ መናፍቅ ተንደርደሮ አውደ ምህረቱ ላይ ይወጣና በልሳነ መናገር ይጀምራል አቡነ ቀውስጦስም ወንድሜ መስበክ ከፈለክ ሁላችንም በምንሰማው ቋንቋ ተናገር ይሉታል መረበሽ ጀመረ ቢመክሩት እምቢ አለ እንግዲያውስ ወላዲተ አምላክ አንደበትህን ትዝጋው ይሉታል ወዲያው አንደበቱ ተያዘ መናገር ተሳነው፤ ከዚያ በኃላ የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው እግራቸው ላይ ወድቀው አባታችን ይማሩት አሏቸው፤ ጸሎት አድርገው አንደበቱን ፈተውታል፤ ይህ እውነት ነው፤ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፤ አባ ቂርሎስ በርካታ መጽሐፍትን ጽፏል ከነዚህም አንዱ ቅዳሴ ቂርሎስ ነው ሃይማኖተ አበው ላይም ስለ መለኮት ገራሚ ገራሚ ነገሮች ተናግሯል፤ 32 ዓመት በማርቆስ መንበር መንጋውን በፍቅር ጠብቆ ሐምሌ በባተ በ 3ኛው ቀን አርፏል። በረከቱ ይደርብን፤ ቅዳሴ አንድምታ፤ ስንክሳር። በረከቱን ይደርብን።

No comments:

Post a Comment