Tuesday, August 18, 2015

ደብረ ታቦር ትምህርቱ፣ ምስጢሩና ትውፊቱ



ደብረ ታቦር ትምህርቱ፣ ምስጢሩና ትውፊቱ



በፊልጶስ ቂሣሪያ ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ ጌታችን እንዲህ በማለት ጠየቃቸው፡፡ "የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?" ሐዋርያትም "ሙሴ፣ ኤልያስ ... ከነቢያትም አንዱ ነው ይላሉ" አሉት፡፡ ጌታችንም "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" አላቸው፡፡ ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስም ፈጥኖ አንተ "የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ" አለው፡፡ "ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህም" በማለት ደቀ መዝሙሩን አደነቀ፡፡

ይህ በሆነ በስድስተኛ ቀን ጌታችን ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስን አስከትሎ ወደ ረዥም ተራራ ወጣ፡፡ /ማቴ 17÷18፤ ማር 9÷28፤ ሉቃ 9÷28-36/፡፡

ለምን ይዟቸው መጣ? 

ስለዚህ ትምህርት ሁለት ምክንያቶች ማየት ይቻላል፡፡ ሞትን ስለማይቀም** ሰው ደቀ መዝሙር አስተምሮአቸው /ነግሮአቸው/ ነበር እና ኤልያስን አሳይቶ የደቀ መዝሙሩ የፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወትም እንዲሁ መሆኑን ለመግለጥ፡፡ /ማር. 9/ እንዲሁም በፊልጶስ ቂሣሪያ "እኔ ማን ነኝ" ባላቸው ጊዜ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ጴጥሮስ የመሰከረውን እውነት በባሕርይ አባቱ በእግዚአብሔር አብ ለማስመስከር ነው፡፡

በዚህ እለት ምስጢረ ሥላሴን እንዲረዱ የሦስትነት ምስጢር ተገልጧል፡፡ ወደ ተራራውም ፊልጶስ ቂሣሪያ የጠየቃቸውና የመለሱለት ትምህርት ብዙም ሳይዘነጋ በ7ኛው ቀን አውጥቷቸዋል፡፡ 

ረጅሙ ተራራ 

ይህ ተራራ ማን ነው? ወንጌላዊው ማቴዎስ "ረዥሙ ተራራ" በማለት የጠራውን ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ "ቅዱስ ተራራ" በማለት ጠርቶታል፡፡ ሥርዓተ ሐዋርያትን የያዘው ሲኖዶስ የተሰኘው መጽሐፍም በስሙ "ታቦር" በማለት ጠርቶታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ረዥሙ እና ቅዱሱ ተራራ በማለት ቅዱስ መጽሐፍ የገለጠው ደብረ ታቦር / የታቦር ተራራ/ ነው ማለት ነው፡፡

የታቦር ተራራ ትንቢት የተነገረለት ምሳሌ የተመሰለለት ደብር ነው፡፡ ትንቢት "ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሁ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል" በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ተናግሮአል፡፡ /መዝ.** /፡፡ ምስጢረ ብርሃንን /መለኮትን አይተዋልና፡፡

በነቢይነትና በምስፍና ሕዝበ እግዚብሔርን ያገለገሉት ዲቦራና ባርቅ ጠላታቸው ሲሳራን ድል ያደረጉት በዚህ ተራራ ነው፡፡ የእስራኤል ጠላት ክፉ ሰው ሲሳራ በዚህ ተራራ ድል እንደሆነ በልበ ሐዋርያት ይፈታተን እና በክፉ አሳብ ያጠራጥራቸው የነበረ ክፉ ጠላት ሰይጣንም በዚህ ተራራ ድል ተነሥቷል፡፡ ምሳሌው ተፈጸመ፡፡

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ለምን? 

ወደ ረዥሙ ተራራ ይዟቸው ወጣ የተባሉት ደቀ መዛሙርት ሦስት ናቸው፡፡ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ጴጥሮስ፡፡ ለምን ተመረጡ?

እግዚአብሔር በልዩ ልዩ ምክንያት ይመርጣል፡፡ ለአገልግሎት ይለያል፣ ምስጢር ይገልጣል ወዘተ ሦስቱን ደቀ መዛሙርት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሙሴ ለምን መስፍን እንደሆነ አይታወቅም፤ አሮን ለምን ካህን እንደሆነ አይታወቅም "ሰው ፊት ያያል እግዚአብሔርን ግን ልብን ያያል" ዳዊትን ሊቀባ የሄደውን ሳሙኤል የእሴይን ልጆች እያየ ሲያሳልፍ የዐይኑን አምሮት ይሄ ይሆንን ይል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ወንድሞቹን እያሳለፈ ብላቴናው ዳዊትን ለመንግሥት የመረጠበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተመረጡበትን ምክንያት ሲያትቱ የዳሰሷቸውን ጥቂት ነጥቦች እንመልከት፡-

ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ሹመት ሽልማ ክብር ፈላጊዎች ነበሩ፡፡ ከዚህ ሃሳብ እንዲወጡ ከብልየታቸው እንዲታደሱ ለይቶ አውጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ለድኀነተ ዓለም የመጣው በሕማማቱ በሞቱ ቤዛ የሚሆነን አምላክ "ልሰቀል ነው" ባላቸው ጊዜ "አይሁንብህ" ብሎት ነበር፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳብ የጠላት እንጂ የሰው ልጆች ሊሆን አይችልም ከሞቱ በቀር ድኀነት ሊያስገኝልን የሚችል የለምና፡፡ ደቀ መዝሙሩ ግን ከሞተ ክብሬ ምንድን ነው ብሏልና "አይሁንብህ" አለ፡፡ /ማቴ. 16/ በሌላም ስፍራ እንዲሁ "ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲስ ምን እናገኝ ይሆን?" በማለት ይጠይቃል፡፡ /ማቴ.19/፡፡ ጌታ ግን ዋጋችሁ ሰማያዊ ክብራችሁ ዘላለማዊ ነው ሲል እስከ ፍጹማን መዓርግ ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ አድርሶ ብርሃነ መለኮትን ገልጦ ተስፋውን ነገራቸው፡፡

ሁለቱ ወንድማማች ደቀ መዛሙርትም እናታቸውን ልከው ሹመት ሽልማት መዓረግ ለምነዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን በደብረ ታቦር "በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ነገር" ስለሞቱ እንዲነጋገሩ አደረገ፡፡ ሞቱ እርግጥ ሆነ ማለት ነው፡፡ አባቱም "ኦሆበልዎ ለክርስቶስ"፤ እሺ በሉት እርሱን ስሙት፡፡ ሞቱ እርግጥ በመሆኑ ከልባቸው እንዲጠፋ መርጦ ወደ ቅዱስ ተራራ ይዟቸው ወጥቷል፡፡

"እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም" እንዲል፡፡ በእርሱ ዘንድ ወረት የለም፡፡ አስቀድሞ ከተዓምራቱ ከምሥጢሩ አይለያቸውም ነበርና ብርሃነ መለኮትን ለማየት አበቃቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ለማወቅ፣ ለመማር፣ ለመጠየቅ ያሳዩት ትጋት ምስጢር ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህ ምስጢር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦ የሚቀር አይደለም፡፡ እስከ ዓለም ፍፃሜ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሲገለጥ፣ በመረጣቸውም ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ ኪዳኑን የሚጠብቅ አምላክ ምስጢሩን ይግለጥልን፡፡

ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ "አልክድህም አልተውህም" የሚለው ቢወድደው አይደለምን? ፍቅሩን መግለጡ ለክብር አብቅቶታል፡፡ ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም "ጥዋዬን ልትጠጡ አትችሉም" ቢላቸውም አንዳችን በቀኝ ሌላችን በግራ ሆነን አብረንህ እንሞታለን ሲሉ በምስጢር ለምነዋል፡፡ ሞታቸውን ከሞቱ ጋር መደመራቸው ፍቅራቸውን መግለጣቸው ነው፡፡

ከተራራው ግርጌ 

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ "አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል" በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ "... በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ ... በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ...." በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14÷1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረውነ ይሁዳ ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡

"የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ" የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ሊለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል ጥበብ ይህን አደረገች፡፡ 8 ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም "ልበ ንጹሐን ብፁአን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና" /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ "ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና" እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡

የተራራው ምስጢር



ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ጌታችን ብርሃንነት "በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ" "ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃን ተመላለሱ" "እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" "በሞት ጥላ መካከል ላሉ ብርሃን ወጣላቸው" ... በማለት መስክሯል፡፡ ፀሐየ ጽድቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች የተስፋ ብርሃን፣ የእውቀት ብርሃን፣ የዓይን ብርሃን፣ የሕይወት ብርሃን ነው፡፡ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትንም ብርሃን ያለበሰ እርሱ ነው፡፡ ለመላዕክት፣ ለጻድቃን ለቅዱሳን ሁሉ የጽድቅ ብርሃንን ያደለ የማይጠፋ ብርሃን እርሱ ነው፡፡

በጻድቁ አባት በገብረ መንፈስ ቅዱስ ገድል እንደምናነበው ለጻድቁ የጽድቅ ምስክር ሆኖ ለረዥም ጊዜ የቆየውን ዓይነት ብርሃን አይደለም፡፡ አባ አትናቴዎስ ስለ ንስሃውና እመቤታችንን ስለ መውደዱ ካገኘው ብርሂት እድ ጋር እንዴት እናነጻጽረዋለን? ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከተራራው በወረደ ጊዜ የእስራኤልን ዐይን የበዘበዘ ገጸ ብርሃን ምሳሌው ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ ለቅዱሳን ብርሃንን የሚሰጥ የብርሃናት አምላክ፣ ሙሴን ብሩህ ያደረገ፣ ለአባ አትናቴዎስም ብርሂት እድን የሰጠ... ነው እንጂ፡፡ በቅዱሱ ተራራ ማደሪያውን ያደረገ አምላክ በዚህ ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ገለጠ፡፡

ይህን ልዩ ምስጢር በገለጠባት ቅዱስ ተራራ ደጋግሞ የአብን ምክር ሰማን አብ በደመና "የምወደው የምወልደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት" ብሏልና፡፡ በከዊን /ከዊነ ቃል ከዊነ ልብ ከዊነ እስትንፋስ/ ሦስት ሲሆኑ በኩነት አንድ ናቸውና በደብረ ታቦር ልብሱ እንደ በረዶ ነጥቶ በአካለ ሥጋ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠው ወልድ ቃልነት አብ በደመና "የምወደው የምወልድ ልጄ" በማለት መሰከረ፡፡

ሙሴ ወ ኤልያስ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋንም የሙታንም አምላክ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ያስመሰከረውም ይኸንኑ ነው፡፡ ወንጌልም ስለምስክርነታቸው ሲናገር "በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው ተነጋገሩ" ይላል፡፡ አስቀድመው በፊልጶስ ቂሣርያ ሙሴ፣ ኤልያስ ይሉሃል ብለውት ነበር፡፡ ሙሴ "የኔን የሙሴን አምላክ እንዴት ሙሴ ‹‹ሰው፣ ሩቅ ብእሲ፣ መዋቲ..../ ነህ ይሉሃል ? እኔ ባሕር ከፍዬ ባሻግር፣ ከዐለት ውኃ ባፈልቅ.... እስራኤልን ከዳግመኛ ሞት ላድናቸው ያልተቻለኝን፡፡ አንተ ከዘለዓለም ሞት የምትቤዥን ነህ" በማለት መስክሮለታል፡፡

ኤልያስም የእኔን የኤልያስን አምላክ እንዴት ኤልያስ /የሕያዋን ብቻ፣ የነፍስ ገዥ ብቻ/ ነህ ይሉታል? እኔ እሳት ከሰማይ ባወርድ ከሰጠኸኝ ነው፡፡ አንተ በሞትህ ዓለምን የምታድን ነህ ሲል መስክሮአል፡፡

ከዚህ ምስክርነትና መገለጥ የተነሣ አንተ ስንሞት እያስነሳኸን፣ ሕብስት እያበረከትህ እያበላኸን፣ ሙሴ መና እያወረደ ደመና እየጋረደ ከጠላት እየተጋደለ፣ ኤልያስ እሳት እያዘነመ ቤት /ዳስ/ ሠርተን በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ የሚጠይቁን ሰዱቃውያን፣ የሚያሳድዱን ጸሐፍት ጋር ምን አጣላን በዚህ እንቆይ በማለት እስኪመኝ አደረሰው፡


ትውፊቱ

ቡሄ

ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን፡፡

ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፤ የመሸጋገሪያ ወቅት ነው፡፡ "ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" እንዲሉ፡፡ በሌላ በኩልም "ቡኮ/ሊጥ" ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት "ሙልሙል" የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ ተብሏል፡፡

ጅራፍ

በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በኢየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን ምስጢራዊ ሞቱ ነው፡፡ ጅራፍ መገመድ እና ጀራፍ ማጮኸ ሁለት ዓይነት ምስጢር ይዞ የሚከወን ትውፊታዊ ተግባር ነው፡፡ የመጀመሪያው ግርፊቱን እና ሞቱን እናስብበታለን፡፡ እንዲሁም ድምፁን ስንሰማ የባሕርይ አባቱን የአብን ምሰክርነት ቃል፣ እንደ ነጎድጓድ ድምፅ ያስታውሰናል፡፡

የጅራፍ ትውፊታዊነት /ውርስ/፣ መጽሐፋዊ ትምህርትና ምስጢር ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጨዋታውን በተራራማ አካባቢ፣ ከመኖሪያ ቤት ርቆና፣ በሜዳ ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ጅራፍን በርችት መቀየር የሚያመጣውን የምስጢር ተፋልሶ ብቻ መመልከት ከማኀበራዊ ጎጂ ገጽታው በላይ እንድናስወግደው ያስገድደናል፡፡


ችቦ

ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን፡፡ የዚህ ትውፊታዊ የት መጣ ግን በብርሃኑ ድምቀት የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደዋልና ታሪኩን እያዘከርን በዓሉት እናከብራለን፡፡

የችቦው መንደድም ሌላ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ምእመን ለሌላው ምእመን መካሪ አስተማሪ መሆኑን፣ መከራ እየተቀበለም አርአያ ምሳሌ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ በሃይማኖትም አርአያ ምሳሌ ይሆንላቸዋል፡፡

ሙልሙል

በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል፡፡ ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው፡፡ ወደ ቤታችን "ቡሄ" እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ "ሙልሙል" ዳቦ አለ፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያት ምስራች ሊነግሩን፣ ወንጌል ሊሰብኩን በደጃፋችን ቆመው "ቡሄ በሉ" የሚሉንን አዳጊዎች የሚበሉትን መስጠታችን ምሳሌያዊ /መጽሐፋዊ/ ነው፡፡ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ባስተማራችሁበት፣ በደረሳችሁበት ተመገቡ ብሏቸዋል፡፡ /ማቴ 10÷12/ ሕፃናቱም ሊዘምሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሕፃናቱ የደቀመዛሙርት ምሳሌ ናቸው፡፡ መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት "የምስች" ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ሐዋርያት በገቡበት አገር አስተምረው አጥምቀው የጸጋ ልጅነትን አሰጥተው በረከት አድለው እንደሚሔዱም፣ ልጆችም ዘምረው፣ አመስግነው፣ መርቀው "ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ...." ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ በዓለ ደብረ ታቦር ከነዚህ ምስክር ካላቸው ትምህርቶቹ፣ ምስጢር ከሚራቀቅባቸው ትርጓሜያቱና ከትውልድ ትውልድ በቅብብል በተላለፈው ቅዱስ ትውፊት ጋር ሃይማኖታዊ ባሕል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን አዳጊዎች ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ይዘው እንዲያድጉ ጥቆማ በመስጠት፣ ግጥም በመግጠምና ምስጢሩን በማብራራት የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚሰሙ ግጥሞች ስድብ፣ ፌዝና ሥላቅ የተቀላቀለባቸው ይሆናሉ፡፡ ሕፃናቱም ዝማሬውን ሲጀምሩ "ከሰጡን እንነሣ ከነሱን እናርዳ" ብለው ይጀምሩታል፡፡ ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን በማለት፡፡ አሳሳቢው ነገር ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛነት የቀየሩ ሁኔታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ዳቦ /ሙልሙል/ ትምህርቱንም፣ ምስጢሩንም፣ ትውፊቱንም በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ቤተክርስቲያን የምስጢር ግምጃ ቤት ናት የምታከናውነውን ሁሉ ከበቂ መረጃ ጋር ነው ተግባራዊ የምታደርገው፡፡ በተለይ ወጣቱ ክፍል ይህንን አውቀን ተረድተን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፋ እንችል ዘንድ ከክፉ ጠላት ከሰይጣን ፈተና፣ በሽታ ከመሳሰሉት ችግሮች ለመዳን ወደ ተራራዋ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሸሽ ከክፉ ነገሮች ሁሉ ማምለጥ ይቻላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚጠለሉ ሁሉ ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ አስተዋዮችም ይሆናሉ ሁሉን ማየትና የሚጠቅማቸውን መምረጥ ይችላሉ በሥነ-ምግባር የታነፁ አገርንና ወገንን የሚጠቅሙ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመጠጋት ከክፉ ሁሉ የሚያመልጡ ይሆናሉ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

1 comment: