Monday, September 26, 2016

ግሸን ደብረከርቤ ዳግማዊት ጎልጎታ - የግማደ መስቀሉ መገኛ


ግሸን ማርያም ደብር በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፤ በደላንታ፤ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ በርዋ አንድ ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡ በትግራይ እንደ ደብረ ዳሞ በበጌምድር እንደዙር አምባ በመንዝ እንደ አፍቅራ ናት ፡፡




ወደዚህች ደብር ለመሔድ በረሐ አቋርጦ በሸሎን በመሻገር ፫ ሰዓት መንገድ አቀበት በመውጣት አንድ ቀን ሙሉ ተጉዞ ማታ ፲፪ ሰዓት ይገባል ፡፡ግሸን ማርያም በፊት ደብረ እግዚአብሔር ትባል ነበር ፡፡ይህ ደብረ እግዚአብሔር የሚለው ስያሜም በጻድቁ ንጉሥ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ ከዚያም በዓጼ ድግናዣን ዘመን መንግሥት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብር ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች ፡፡


ከዚያም በ ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር፡፡ ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡ 


የግማደ መስቀሉ መምጣት ታሪክ

ዓለምንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ፍጡር ፈጥሮ የሚገዛውን አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤተ እሥራኤል በቀራንዮ ላይ በመስቀል ሰቀሉት ፡፡ መድኃኔዓለም በዕለተ ዓርብ ከቀኔ በዘጠኝ ሰዓት ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየ በኋላ በኋላ ከመስቀሉ አውርደው ቀበሩት ፡፡በ፫ኛው ቀን ሲነሣ ተሰቅሎ የነበረው የእንጨት መስቀል ሌት ተቀን በሙሉ ሳያቋርጥ እንደፀሐይ ሲያበራ በተጨማሪም አጋንንት ሲያባርር ድውይ ሲፈውስ ሙት ሲያነሣ ቤተ እሥራኤል አይሁድ ቀንተው በዓዋጅ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በመቅበር የቤት ጥራጊና አመድ ጠቅላላ የቆሻሻ መከማቻ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ ከዚያ ዘመን ጀመሮ እስከ ሦስት መቶ ዘመን ድረስ የተከማቸው ቆሻሻ እንደተራራ ሆነ፡፡ 

ከዚያ በኋላ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ ንግሥት የተባለች ደግ ሴት የክርስቶስን መስቀል መስከረም ፲፯ ቀን ፫፻፳ ዓ.ም. ላይ በዕጣን ጢስ ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር አስቀመጠችው ይህ መስቀልም ከዚያ ዘመን ጀምሮ እንደ ፀሐይ እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ተአምራትን እየሠራ ሙት እያነሳ ዕውር እያበራ ተአምራቱን ቀጠለ፡፡ ይህንንም ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምዕመናን የሮማውን ንጉሥ ሕርቃልን ዕርዳታ በመጠየቅ እንዲመለስ አድርገው በኢየሩሳሌም ብዙ ዘመን ሲኖር እንደገና ኃያላን ነገሥታት ይህን መስቀል እኔ እወስድ እኔ እወስድ እያሉ ጠብ ፈጠሩ፡፡

በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ፤ የቁስጥንጥንያ ፤ የአንጾኪያ ፤ የኤፌሶን ፤ የአርማንያ ፤ የግሪክ ፤ የእስክንድርያ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን አበረዱት ከዚህም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የክርስቶስ መስቀል ከ፬ ከፍለው በዕጣ አድርገው በስምምነት ተካፍለው ከሌሎቹ ታሪካዊ ንዋያት ጋር በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳት ጋር በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ በክብር አስቀመጠው፡፡

ይህ ግማደ መስቀልም ለብዙ ዘመን በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው እየጠነከረ ሔደ በእስክንድርያ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው መክረው ለኢትዮጵያዊ ዓፄ ዳዊት እንዲህ የሚል መልዕክት ላኩ “ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግሥልን ብለው ጠየቁት” ዳግማዊ ዓፄ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ኃይማኖት ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶአቸው ፳ ሽህ ሠራዊት አስከትለው ወደ ግብፅ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብፅ ያሉ ኃያላን ፈሩ ተሸበሩ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል መልዕክት ለእስላሞች ላኩ በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት ክርስቲያኖች ጋር ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋዋለሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ላኩ ፡፡የንጉሡ መልዕክት ለእስላሞች እንደደረሳቸው ፈርተው እንደጥንቱ በየሃይማኖታቸው ፀንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡

መታረቃቸውን ዳግማዊ ዳዊት ሰሙ በዚህም ጉዳይ ንጉሡ በጣም ደስ አላቸው እገዚአብሔርንም አመሰገኑ በግብፅ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው ንጉሡም የደስታውን ደብዳቤ ተመልከተው ደስ ኣላቸው ፤ ወርቁን ግን መልሰው በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ፃፉ በግብፅ የምትኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ሆይ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝን ፲፪ ሺህ ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ የእኔ ዓላማ ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ አሁንም የምለምናችሁ በሀገሬ በኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረውን መስቀልና የቅዱሳንን አፅም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ ነው የሚል ነበር፡፡ 

በእስክንድርያም ያሉ ምእመናን ይህ መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳቱና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር ውይይት በማድረግ ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል ከቅዱሳን አጽምና ንዋየ ቅድሳት ጋር አሁን በመለሰው ፲፪ ወቄት ወርቅ የብርና የንሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን እንላክለት ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው ባስረከቡአቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ ተቀበሉት ይህም የሆነው መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ታለቅ ብርሃን ሌት ተቀን ፫ ቀን ሙሉ ሲበራ ሰነበተ፡፡

ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት ዓፄ ዳዊት ስናር ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዘርአ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ሥናር ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅድሳት ጋር አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ ቤተ መቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማቸው አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል ወዳጄ ዘርአ ያዕቆብ ሆይ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ የሚል ሕልም አዩ ፡፡ ንጉሡም መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ መስቀለኛ ቦታ በመፈለግ ከብዙ ቦታ ላይ አስቀምጠውት ነበር ለምሳሌ በሸዋ በደርሄ ማርያም ፤ በመናገሻ ማርያም ፤ በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን የመጨረሻውን ቦታ ያላገኙ በመሆኑ በራዕይ እየደጋገገመ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡

ዓፄ ዘርአያዕቆብም ለ፯ ቀናት ያህል ሱባዔ ገቡ በዚያም የተገለፀላቸው መስቀልኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምድ ብርሃን ይመጣል አላቸው እርሳቸው ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ የሚመራ ዓምደ ብርሃን ከፊታቸው መጥቶ ቆመ በዚያ መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን ከምትባል መርቶ አደረሳቸው ፡፡በርግጥም ይህች ግሽን የተባለች አምባ ጥበበኛ ሰው እንደቀረፃት የተዋበች መስቀልኛ ቦታ ሁና ስለአገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው ፡፡ በዚያችም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡

v ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ዝርዝር 

v ጌታ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳው 

v ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ 

v ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል

v ቅዱስ ሉቃስ የሣላቸው የእመቤታችን ስዕሎች 

v የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር 

v የዮርዳኖስ ውሃ 

በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ነው፡፡ የነዚህንም ዝርዝር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሼን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩ ሺ ፬፻፵ ዓ.ም. ላይ ተናገሩ ፡፡በመጀመሪያም ይህ ግማደ መስቀል ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ነው ወደ ኢትዮጵያም የገባው በመስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ አሁንም በመጨረሻ ግሸን አምባ የገባው መስከረም ፳፩ ቀን ሲሆን ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና አፄ ዘርዓያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በፅሑፍ በመዘርዘር የገለፁበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ 

ስለዚህ ከዚህች በግሸን ደብር የክርስትና እምነት ያላቸው የኢትዮጵያ ምእመናን ከበረከተ መስቀሉና ከቅዱሳን አፅም በረከት ለማገኘት በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን እየመጡ ያከብራሉ፡፡ በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የነበሩት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምህረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ በሱባዔአቸውም በመጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን በዚች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች ጠለ ምህረቴንም አይለይባትም ፤ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ መጥቶ የተቀበረ ኢየሩሳሌም እንደተቀበረ ይሁን የሚል የምህረት ቃል ኪዳን ተገልጾላቸው በዚህ ለተገኙት ምዕመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋያተ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ጤፉት ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለግሸን እግዚአብሔር አብ ሰጡ፡፡

አፄ አርዓ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እሌኒ እኅታቸው የተሰኘችው በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ ዓፄ ዘርአ ያዕቆብም ይህችን ደብር ደብረ ከርቤ ብለው በመሰየም እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ ፤ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሀሏ ገነት ትሁን ብለው ደንብና ሥርዓት በጤፉት መጽሐፍ ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታትና የተሾሙ ጳጳሳት መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትንና መጻሕፍትን የወርቅንና የብርን ሰን ፤ ብርና ጻሕል ጽዋን መስቀልን የመሳሰሉትን የሰጧት ምዕመናንም በየዓመቱ መስከረም ፳፩ ቀን በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዓመት ወደ ዓመት እየበረከቱ ሔደዋል፡፡ 

በመስከረም 10 ፤ መስከረም 17 በዓለ መስቀል እና መስከረም 21 የግሸን በዓል ታሪክ ከረጅም በአጭሩ ይህንን ይመስላል ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ምዕመናን የሆናችሁ ሁሉ ከበረከተ መስቀሉ ለመሳተፍ ወደ ግሸን ገሥግሱ፡፡ 

ልዑል እግዚአብሔር ከበረከተ መስቀሉ ያሳትፈን 

አሜን

መልካም የመስቀል በዓል


ስምዓት

v ትንሣኤ መጽሔት

v መለከት መጽሔት



Soruce: www.melakuezezew.info/2011/09/blog-post_23.html



እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ



ደመራ

መስከረም 16 ቀን እኛ ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ ደመራ እንሠራና ችቦ ይዘን፡

"በወንጌሉ ያመናችሁ 

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ" 



እያልን በታላቅ ዝማሬ ብዙ መዘምራን ከየቤተ ክርስቲያኑ (ከየአድባራታቸው) ተሰባስበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና ሕዝበ ክርስቲያን በተሰበሰቡበት በዝማሬ ይከበራል፡፡

ደመራ - ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡

የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌሊ ልጇ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና ሃይማኖት በተመለሰ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡ ደርሳም ስለከበረ መስቀል ጠየቀች (መረመረች) ቦታውንም የሚያስርዳት አላገኘችም፡፡ በኋላ ስሙ ኪራኮስ የሚባል አንድ ሽማግሌ መስቀሉ ወዳለበት ወደ ጐልጐታ ኮረብታ እያሳያት «አባቶቻችን ከነዚህ ተራራዎች ውስጥ በአንዱ አይሁድ መስቀሉን እንደቀበሩት ነግረውናል» አላት፡፡ እሌኒም ለምን ቀበሩት? ብላ ጠየቀች፡፡ የጌታችን መስቀል ሙታን ሲያስነሳ፣ በሽተኛ ሲፈውስ አይተው አይሁድ በክፋትና በቅናት ተነሳስተው ነው የቀበሩት፡፡

ከዚያም የተቀበረበትን ቦታ ክርስቲያኖች እንዳያገኙት ሁሉም አይሁዶች ከየቤታቸው የሚወጣውን ቆሻሻ እንዲጥሉበት ተደረገ፡፡ የጌታችንን መስቀል የቀበሩበትን ቦታ ቆሻሻ መጣያ አደረጉት ያም ቆሻሻ ሲጠራቀም ከሁለት መቶ ዓመት በላይ አልፎት ትልቅ ተራራ ሆነ፡፡ ኪርያኮስም ንግሥት እሌኒን እንዲህ ሲል መከራት «ደመራ አስደምሪ ብዙ እጣን አስጨምረሽበት ወደ ፈጣሪ ብታመለክች የእጣኑ ጢስ መስቀሉ ያለበትን ተራራ ያመልክትሻል፡፡» አላት፡፡ እሌኒም ኪርያኮስ እንደ መከራት በመስከረም 16 ደመራ አስደምራ ብዙ እጣን አስጨምራ ወደ ፈጣሪ ብታመለክት የእጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ በተቀበረበት ተራራ ላይ አረፈ፡፡ ከዚያም መስከረም 17 ቀን መስቀሉን ለመፈለግ ተራራውን መቆፈር ጀመሩ፡፡

ከስድስት ወር በኋላ በመጋቢት 1ዐ ቀን መስቀሉን አግኝተውታል፡፡ መስቀሉንም አምጥተው በሞቱ ሰዎች ላይ አስቀመጡት ያን ጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ ሌሎች ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም አደረገ ንግሥት እሌኒም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል መሆኑን አውቃ ሰገደችለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡

ከክርስቶስ መስቀል አንዱ ክፍል የሆነው ግማደ መስቀሉ በኢትዮጵያ አለ.. ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ይገኛል



ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Thursday, April 28, 2016

ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት



በዓቢይ ጾም ከሰርከ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፤ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለመሳሳም፤ አክፍሎት፤ ቄጤማ ማሰር፤ ጥብጣብ፤ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ 

+ አለመሳሳም፡-

በሰሙነ ሕማማት ምእመናን መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፤ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንስቀለው . . . እንግደለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያንን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፤ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡ ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው፤ ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት /የተቀደሰ ስጦታ/ አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሄዋንን ሰላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት የሰላምታ ልውውጥ አይደረግም፡፡

+ ሕጽበተ እግር፡-

የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት፤ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው፡፡ ሕጽበተ እግር ጌታችን እናንተ ለወንድማችሁ እንዲህ አድርጉ በማለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ / ዮሐ.13፡16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡ ጌታ በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አለ፡፡ ደቀመዛሙርቱም ማን ይሆን? አሉ፡፡ ጌታም ኅብስት ቆርሼ፤ ከወጡም አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው አላቸው፡፡ ደቀመዛሙርቱም ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው ግን አልገባቸውም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመስጠት የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ ትኩሴ፤ በጎንደር ደግሞ ሙገራ ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸውን ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡

በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስበከት በቅዱስ ላሊበላ አጠገብ በሚገኘው የይምርሐነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጣርያ ላይ ካህኑ ትኩሴ ዳቦ ሲባርክ የሚያሳይ ሥዕል አለ፡፡ በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ጸጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ ኃጢአት ይሆንበታል ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል የለም፡፡ ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ተብሎ ይነገራል፡፡

እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት

አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፤ የዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራና የወይን ቅጠል በውኃ በመዘፍዘፍ ነው፡፡

+ አክፍሎት፡-

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከአርብ እስከ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ብዙዎች ያከፍላሉ፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፤ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡ ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፤ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ፤ ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉም ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ

እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡

+ ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፤ ከስንዴ ወይም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባንእንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም አብዛኞቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይታሰባል፡፡

+ ጥብጣብ፡- 

በሰሙነ ሕማማት ዕለት ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማት ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ፤ ሲጸልይ፤ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ለማሰብ ነው፡፡ ማቴ.27፡26፤ 19፤1-3/

+ ቄጤማ፡-

በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላም እንደሰጠን እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ገጸ በረከት ያቀርባሉ፤ ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጤማ ተሸክመው፤ ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቁ ምእመናን ትልቅ ብስራት ነው፡፡



ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ (ማህበረ ቅዱሳን)

Thursday, April 7, 2016

መጋቢት 29

መጋቢት 29 

ቀን በዕለተ ዕሁድ እግዚያብሔር ዓለምን መፍጠር ጀመረ። እነሆ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ 7508 ዓመት ሆነው፤ ዘፍ 1፤1። ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን ዓለምን ለማዳን የድህነት ስራውን መስራት የጀመረበት ቀን ነው፤ ይህም ጽንሰቱ ነው። መጋቢት 29 በዕለተ ዕሁድ ከቀኑ ሦስት ሰዓት ሲሆን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጎንበስ ቀና እያለ ተፈስሒ ኦ ምል...ዕተ ጸጋ ተፈስሂ ኦ ምልዕተ ክብር...ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ እያለ ሲያመሰግናት ሲያረጋጋት ቆይቶ ልክ "እነሆ ትፀንሻለሽ" ሲላት አካላዊ ቃል በማህጸኗ አደረ፤ ሉቃ 1፤28። ከላይ ሳይጎድል ከታችም ሳይጨመር እሳተ መለኮት በማሕጸኗ አደረ በማይመረመር ግብር ፍጹም ስጋንም ተዋሃደ። ይህ ቀን እጅግ ታላቅ ዕለት ነው፤ ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ ነው አራት ኪሎ በዓለወልድ ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ ወጥቶ ይነግሳል። ዳግመኛ በዛሬዋ ዕለት ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ቀን ነው፤መጋቢት 29 በዕለተ ዕሁድ ከሌሊቱ 6 ሰዓት። ይህንንም ቀን ጥንተ ትንሳኤው ብላ ቤተክርስቲያን አስባው ትውላለች። ሰውን ለወደደ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን። ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን።

Thursday, March 31, 2016

ደብረ ዘይት- አምስትኛው ሳምንት



ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ:-ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) በመሰኘት ተገኝቷል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደብረ ዘይት በዓል ሆኖ የሚከበርበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።

ጌታችን “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያዉቅ የለም” ማቴ. 24፡36 ብሏል። ይህን ማለቱም በየዘመኑ የሚነሱ ክርስቲያኖች ሩቅ ነዉ ብለዉ እንዳይዘናጉ ጊዜዉ ሲቀርብ የሚነሱት ደግሞ ደረሰብን ብለዉም እንዳይሸበሩ/እንዳይታወኩ ለመጠበቅ ነዉ። ከላይ እንደጠቀስነው ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸዉ ወደ እርሱ ቀርበዉ “የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድር ነዉ? አሉት።” ማቴ. 24፡3 እርሱም በስፋትና በጥልቀት ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ ዳግም ምጽአቱ ምልክቶች አስተማራቸዉ። ከነዚህምዋና ዋና የሆኑትን ምልክቶች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታቸዋለን።

1. የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ይታያሉ

ምጥ ሲመጣ አስቀድሞ የምጡ መጀመሪያ ሕመም (ጣር) እንዳለ ሁሉ የዓለምም ፍጻሜ በጣር ነዉ የሚጀምረዉ። ይህንንም ጌታችን በግልጽ አስረድቶናል፦ ጦርና የጦር ወሬ መሰማት፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ መነሳት፣ ርሃብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ መታየት ለዓለም ፍጻሜ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸዉ። እነዚህ ነገሮች በሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ ላይከሰቱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በልዩ ልዩ ቦታዎች ለብዙ ዘመናት ታይተዋል፤ እየታዩም ናቸዉ።

2. ስለ ስሜ በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ስሜ (የክርስቶስ ተከታዮች/ ክርስቲያኖች በመሆናችሁ) በዓለም ዘንድ ትጠላላችሁ ብሎናል። ዓለም ክፉ ስለሚሠራ የጥሩ ነገር ተቃራኒ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። ጌታችን “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸዉ ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነዉ። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ሥራዉም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እዉነትን የሚያደርግ ግን ሥራዉ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።” ዮሐ. 3፡19-21 እንዳለንበክፉ ሥራ ዉስጥ ያለዉ ይህ ዓለም በጎ ሥራ የሚሠሩትን የክርስቶስን ተከታዮች ይጠላል። ጨለማ ብርሃንን ብርሃንም ጨለማን እንደሚጠላ፤ይህ ዓለም እኛን እንዲጠላን፣እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህንን ዓለም ልንጠላው ይገባል።

አሁን ባለንበት ዘመን ክርስትና እየተጠላ፣ እየተናቀ ነዉ ያለዉ። “ባደጉት” ዓለማት ባዶ አብያተ መቅደሶች ቀርተዉ እነሆ እንመለከታቸዋለን፤ ትዉልዱ በዓለም ስሜትና በሥጋ ፈቃድ ብቻ እየሄደ ነዉ።ክርስቲያን ነን በሚሉትም አውሮፓውያን ዘንድ የአንገት በላይ (የማስመሰል) ክርስትና እንጂ እንደ ቅዱስ ቃሉ የሚጓዝ አማኝ ማግኘት አይቻልም። እዉነተኞች አይወደዱም፤ ይገፋሉ፤ ይናቃሉ። ሁኔታዉ የዘመኑ ፍጻሜ እጅግ እየቀረበ መምጣቱን በእርግጥ ያስረዳል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ፦ ስለ ስሜ ለመከራ አሳልፈዉ ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል ብሏል። ክርስቲያን በመሆናቸዉ ብቻ ማንንም ሳይበድሉ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በልዩ ልዩ ሀገራት ክርስቲያኖች ሰማእትነትን እስከ አሁን ድረስ እየተቀበሉ ነው፡፡ቅዱስ ጳዉሎስ “ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ” ሮሜ 8፤36 እንዳለዉ። ይህ በቅዱሱ በክርስቶስ ስም መጠላትና መከራ መቀበል ከዓለም የሚጠበቅ የፍጻሜዉ ዘመን ምልክት መሆኑን አዉቀን መዘጋጀትና ከሐዋርያዉ ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።” ሮሜ 8፤37 እያልን በእምነታችን ጸንተን መጋደል ይገባናል።

የክርስቲያኖች ቁጥር እያነሰ መምጣት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መዘጋት፣ ሰዉ ሰዉ የሚያሰኘዉን ክብርና ሞገስ ትቶ በግብሩ እንስሳትን ሲመስል፦ የቅድስና ሕይወት ሲጠላና ሲናቅ፤ በአንጻሩ ደግሞ የሰዉ ልጅ ለረከሰዉ ለዚህ ዓለም ምኞትና ፈቃድ ሲገዛ ስናይ የዚህ ዓለም ፍጻሜ ጊዜዉ እየደረሰ መሆኑን አዉቀን፤ ኖኅ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ቢኖርም ራሱን በቅድስና ጠብቆ እንደኖረ (ዘፍ.6-8)፤ ሎጥም እንዲሁ በብዙ ኃጢአተኞች መካከል ሲኖር በነርሱ ኃጢአት እንዳልተባበረ (ዘፍ. 19) ከዚህ ዓለም ክፉ ሥራ ተለይተን ራሳችንን በቅድስና በመጠበቅ እንጋደል።ዓለሙ ስለ እምነታችን ቢጠላንም እኛም ስለ ክፉ ሥራዉ ንቀነው መኖር የግድ መሆኑን እንወቅ እንጂ ስለ እምነት፣ ስለ ቅድስናም ከዓለም በጎ ነገር አንጠብቅ። በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሱብንን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግስት እንቀበላቸዉ እንጂ በማማረር አንዘን፤ ምክንያቱም ስለ ስሜ በዓለም ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ ተብለናልና።

3. የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰዉ ስፍራ ይቆማል

ዓለም እራሱን በማርከስ ብቻ ሳይወሰን በፍጻሜ ዘመን በተቀደሰዉ ስፍራ እንኳን ሳይቀር የጥፋትን ርኩሰት ያቆማል። የተቀደሰዉ ስፍራ የተባለዉ በተቀደሰ ሃይማኖት የሚኖሩትን ሀገራት፣ ሕዝቦች የሚመለከት ነዉ። እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሀገራት ዲያብሎስ በመልእክተኞቹ ላይ አድሮ በብዙ ርኩሰት ተፈታትኗቸዋል፤ እየተፈታተናቸውም ነው። የየሀገራቱን እምነትና ታሪክ ለማጥፋት ጥሯል፤ ብዙዉንም የቅድስና ሥርዓት በርዞአል፤ የቻለዉንም ከነጭራሹ አጥፍቶታል። አሁን እንኳ አምልኮተ እግዚአብሔር በሚፈጸምባቸዉ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት ሳይቀር በልዩ ልዩ ምክንያት የጥፋት ርኩሰት አዉጇል። ይህም የፍጻሜ ዘመኑ አንዱ ምልክት ስለሆነ አንባቢዉ ያስተዉል እንደተባለ የዘመኑን መፍጠን የጊዜዉን መድረስ በመረዳት መዘጋጀት ይገባናል።4. ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉ


ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት በየዘመኑ ተነስተዉ እዉነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን ታግለዋታል፤ ሊያጠፏት ባይችሉም እንኳን ብዙ ልጆቿን ነጥቀዉ አጥፍተዋቸዋል። የነዚህን ሐሰተኞች ሠራተኞች አመጣጥ ከባድ የሚያደርገዉ በተኣምራትና በድንቅ ምልክቶች መምጣታቸዉ ነዉ። ጌታችን እንደተናገረ “ቢቻላቸዉስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” ስለዚህ በምትሐታዊ ምልክቶቻቸዉ የብዙ የዋሐንን ልብ በማታለል ከተቀደሰ እምነታቸዉ እያስኮበለሉ አጥፍተዋቸዋል፤ በማጥፋትም ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም ሐዋርያዉ ቅ/ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፦ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነዉ እንደሆነ መርምሩ “ 1ዮሐ. 4፡ 1-3 አለን። ቅዱስ ጳዉሎስም “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸዉን እየለወጡ ዉሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞ ሠራተኞች ናቸዉ። ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለዉጣልና።” 2ቆሮ. 11፡13-15 ብሏል። ሐዋርያት ሁሉ በየመልእክቶቻቸዉ ከሐሰተኞች አስተማሪዎች እንድንጠበቅ ደጋግመዉ አሳስበዋል። ብዙ ሰዉ ግን በየዋሕነት ስለሚጓዝ የነዚህ ተኩላዎች ሰለባ ሆኗል።

ጊዜዉ ክፉ ነዉና የሐሰተኞች ነቢያት መረብ ጠልፎ ወደ ሐሰተኞች ክርስቶሶች እንዳይወስደን በጥንቃቄ መጓዝ ይጠበቅብናል። ሐዋርያዉ ቅዱስ ይሁዳም በመልእክቱ ቁ .3 “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።“ ሲል እንደመከረን በተቀደሰ እምነታችን እስከመጨረሻ ለመጽናት እንጋደል።

5. የሰዉ ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ይመጣል

ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ ኃይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል(ማቴ. 25፡31 እስከ ፍጻሜ)።

በዚህ ዓለም ፈቃድ የተጓዙ ኃጥአን ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና ይጣላሉ። በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መንፈሳቸዉን እያስጨነቁ በእምነትና በቅድስና የኖሩ ጻድቃን ደግሞ በደስታ እየዘመሩ ወደማታልፈዉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይገባሉ።

ከዚያ በኋላ ሐዘን የለም፤ ሀብታምና ድሃ የለም፤ኃይለኛና ደካማ የለም፤ በማያልቅ ደስታ ለዘላለም እንደ ቅዱሳን መላእክት ሕያው ሆኖ መኖር እንጂ።

ያን ጊዜ የእኛ እጣ በየት ይሆን?

በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን ዛሬ እንጋደል። የቅዱሳን ሐዋርያት መልእክት ፦

“ወደ እግዚአብሔር መንግስት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል…” ሐዋ. 14፡22 እንዲሁም፦

“ጻድቅ በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመጸኛዉና ኃጢአተኛዉ ወዴት ይታይ ዘንድ አለዉ?” 1ጴጥ.4፡18 የሚል ነዉ!

እንግዲህ እጅግ ባጭሩ የደብረ ዘይትን በዓል የምናከብረዉ እነዚህን እንድናስታዉስና “ድልዋኒክሙ ንበሩ:- ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” በተባልነው መሰረት ንስሐ ገብተን፤ ሥጋወ ደሙን ተቀብለን፤መልካም ፍሬ አፍርተን ሁልጊዜም የተዘጋጀን ሆነን እንድንጠብቅ ነው።

በቀኙ ለመቆም እንዲያበቃን የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የርኅርኂተ ኅሊና የድንግል ማርያም አማላጅነት፣የቅዱሳን ሁሉ ረድኤት አይለየን፤ አሜን።

Source : http://www.mkeurope.org/am/spirituality/21-debre-zeit

Sunday, March 13, 2016

መጋቢት 5

ቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!


በየዓመቱ መጋቢት 5 የምናከብረው በዓል አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያረፉበት በዓል ነው፡፡ በዚኽ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋም በትምህርቷም ኹሉ እኒኽን ታላቅና ቅዱስ አባት ታነሣለች፤ ታወድሳለች፤ ተጋድሎአቸውንም ለልጆቿ ታስተምራለች፡፡
ሀገራቸው ንሒሳ (ግብጽ) ሲኾን አባታቸው ስምዖን እናታቸውም አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዓመታት ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ እኛ አንድ ነገርን ለምነን በእኛ አቈጣጠር ካልተመለሰልን ስንት ቀን እንታገሥ ይኾን? ዛሬ በልጅ ምክንያት የፈረሱ ትዳሮች ስንት ናቸው? ለመኾኑ እግዚአብሔርን ስንለምነው እንደምን ባለ ልቡና ነው? ጥያቄአችን ፈጥኖ ላይመለስ ይችላል፡፡ ያልተመለሰው ለምንድነው ብለን ግን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “የምንለምነውን የማናገኘው በእምነት ስለማንለምን ነው፤ በእምነት ብንለምንም ፈጥነን ተስፋ ስለምንቆርጥ ነው” ይላል፡፡ ሰውን ብንለምነው እንደዘበዘብነው፣ እንደ ጨቀጨቅነው አድርጎ ሊቈጥረው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ “ለምኑ ታገኙማላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል” ያለን ርሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ የሚያስፈልገን ከኾነ ያለ ጥርጥር ይሰጠናል፡፡ መቼ? ዛሬ ሊኾን ይችላል፤ ነገ ሊኾን ይችላል፤ ወይም እንደ ስምዖንና እንደ አቅሌስያ የዛሬ 30 ዓመት ሊኾን ይችላል፡፡ ጭራሽኑ ላይሰጠንም ይችላል፡፡ አልሰጠንም ማለት ግን ጸሎታችን ምላሽ አላገኘም ማለት አይደለም፡፡ የለመንነው እኛን የሚጎዳን ስለኾነ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጥ ስለ ፍቅሩ፤ ሲነሳም ስለ ፍቅሩ ነውና፡፡

ስምዖንና አቅሌስያ ጥያቄአቸው የተመለሰው ከ30 ዓመት በኋላ ነበር፤ ከሥዕለ ሥላሴ ወድቀው እግዚአብሔን ሲለምኑ፡፡ በዚኽም መሠረት አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት 29 ተጸንሰው ታኅሳስ 29 ቀን ተወለዱ፡፡ እንደተወለዱም፡- “ስብሐት ለአብ፣ ስብሐት ለወልድ፣ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ለዘአውጻእካኒ እምጽልመት ውስተ ብርሃን” ብለው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ አባታችን በዚኹ ዕለት ተወልደው እንዲኽ ማመስገናቸው ሊደንቀን ይችላል፡፡ ይኸውም ብዙዎቻችን ሕፃናት እግዚአብሔርን ዐያውቁትም ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ይኽ ግን ስሕተት ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ገና በእናቱ ማኅፀን ሳለ ያመሰገነው እግዚአብሔርን ስላወቀው ነበር፡፡ የሆሣዕና ሕፃናት እግዚአብሔርን በዕልልታ ያመሰገኑት መላእክትንም የመሰሉት አምላካቸውን ስላወቁት ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተወለዱ በሦስተኛው ቀናቸው “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብለው ያመሰገኑት አምላካቸውን ስላወቁት ነው፡፡ የሆሣዕና ድንጋዮች እግዚአብሔርን ዐውቀዉት ካመሰገኑ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩት ሕፃናት ቢያመሰግኑማ ምን ይደንቃል?
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሔዱት በሦስት ዓመታቸው ነበር፤ በቅዱስ ገብርኤል አማካኝነት፡፡ አበምኔቱ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕፃኑን ተቀብለው መዝሙረ ዳዊትንና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ በኋላም ማዕርገ ምንኩስና ተቀብለዋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ዛሬ ሕፃናትን የምንወስዳቸው ወዴት ነው? ዓለማዊ ትምህርት ብቻ ነውን? መንፈሳዊ ትምህርትም እናስተምራቸው፡፡ ልጆቻችን ጥበበኞች፣ ባለጸጎች፣ ዐዋቂዎች እንዲኾኑ የምንሻ ከኾነ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እናስተምራቸው፡፡ ሕፃናት ልጆቻችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደው ቅድሚያ የሚማሩት “አባትህንና እናትህን አክብር” የሚል ነው፡፡ ስለዚኽ ቀድመን የምንጠቀመው እኛው ነን፡፡ ልጆቻችን ወደ ገበያ ቦታ፣ ለነፍሳቸው ምንም ወደማይጠቅማቸው ስፍራ ለመውሰድ የማናቅማማ ከኾነ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመውሰድማ እንዴት? አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲኽ ስማቸው በሰማያት ብቻ ሳይኾን በምድርም ላይ ገንኖ የምንሰማው ከልጅነታቸው አንሥተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ስለተማሩ ነው፡፡ በሦስተኛው ዓመታቸው እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስለሔዱ ነው፡፡ ለመኾኑ ለልጆቻችን በቤት የምንከፍትላቸው ፊልም ምንን የተመለከተ ነው? የቶምና ጄሪ የተንኮል ሥራ ወይስ የነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የነ ቅዱስ ቂርቆስ፣ የነ ሠለስቱ ደቂቅ የቅድስና መንገድ?

አባታችን ማዕርገ ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ሰጥቷቸዋል፡፡ ብዙ ዕውራንን፣ ብዙ ሐንካሳንንም ፈውሰዋል፡፡ እኛም ከተጠቀምንበት እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ለእያንዳንዳችን ሰጥቶናል፡፡ ኃጢአት ለማድረግ የሚፋጠኑትን አንካሳ እግሮች እንድናቀና፣ በዘፈንና በማይጠቅም ወሬ የደነቆሩትን ዦሮዎች እንድንከፍት፣ በስድብ በርግማን ዲዳ የኾኑትን አንደበቶች እንድንፈታ እግዚአብሔር ሀብተ ፈውስን ሰጥቶናል፡፡ ከምንም የሚበልጠው ሀብተ ፈውስም ይኸው ነውና የአባታችንን አሰረ ፍኖት ተከትለን ብዙ ድውያነ ነፍስን ማዳን ይቻለናል፡፡
አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በትእዛዘ እግዚአብሔር በበረኻ ሲኖሩ 60 አናምርትና 60 አናብስት አብረዋቸው ይኖሩ ነበር፡፡ ሊደንቀን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚኽ እንስሳት ከዥምሩም የእኛ ጠላቶች አልነበሩም፡፡ በበደላችን ምክንያት ከእኛ ስለተለዩ እንጂ፡፡ ሔዋን ከእባብ ጋር የተነጋገረችው እባብ የሰው ባርያ ስለ ነበር ነው፡፡ እንስሳት ኹሉ የሰው አገልጋዮች ናቸው፡፡ የእኛ የቅድስና ማዕርግ እንጂ እነዚኽ እንስሳት ከሰው ጋር ጠብ የላቸውም፡፡ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ እነ አቡነ አረጋዊ፣ እነ ነቢዩ ዳንኤል እነዚኽን እንስሳት ያዘዝዋቸው ድሮውንም የእኛ ችግር እንጂ እነዚኽ እንስሳት ለእኛ ክፉዎች ስላልኾኑ ነው፡፡ “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና አንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል፡፡ ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል” እንዲል /ኢሳ.11፡6-7/፡፡ እኛ ግን ከበረኻ አውሬዎችስ ይቅርና ከሰውም ጋር ተስማምተን መኖር አቅቶናል፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዕድሜአቸው 300 ዓመት ሲኾን ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ እንደመጡ የሔዱት ወደ ሮሐ ነበር፡፡ በዚያም ከቅዱስ ላሊበላ ጋር ተገናኝተው ሥራዉን ባርከዉለታል፡፡ በመላዋ ኢትዮጵያ ተዘዋውረው ከማስተማራቸው በላይም የዝቋላንና የምድረ ከብድን ገዳማት መሥርተዋል፡፡
አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድ ቀን ከምድረ ከብድ ተነሥተው ወደ ዝቋላ ሲሔዱ ሥላሴን በሽማግሌዎች አምሳል በጥላ ስር ዐርፈው ያገኟቸዋል፡፡ “በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል፡፡ አዝለህ አንዳንድ ምዕራፍ ሸኘን” አሏቸው፡፡ አባታችንም ሥላሴን አዝለው “ሸኟቸው”፡፡ በኋላ ግን በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ አባታችን ደንግጠው ወደቁ፡፡ ወዮ! እግዚአብሔር ስንት ጊዜ ተሸከሙኝ ብሎ ለምኖን ይኾን? ስንት ጊዜ አልፈነው ሔደን ይኾን? እግዚአብሔር የሚሸከም እንጂ የሚሸከሙት አይደለም፡፡ ግን አባት ነውና ከልጆቹ ጋር መጨዋወት፣ ልጆቹን መባረክ፣ ልጆቹ ርስቱን መንግሥቱን የሚወርሱበት መንገድ ያዘጋጃል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ወዳጄ ሆይ! እግዚአብሔር ነዳያንን የሚልክልህ መስጠትን እንድትለማመድ ነው፡፡ ዛሬ በነዳያኑ አድሮ የሚለምንህ ለኋለኛይቱ ቀን ስንቅ እንዲያስቀምጥልህ ወድዶ ነው፡፡ ታድያ ንጉሥ ወደ ቤቱ መጥቶ የሚያባርር ሰው እንደምን ያለ ጎስቋላ ሰው ነው? እንግዲያውስ ነዳያንን ስታይ ወደ አንተ የመጣው ንጉሠ ሰማይ ወምድር ክርስቶስ እንጂ ሰው አይደለምና አትግፋው፡፡ በረከትህንም ከቤትህ አውጥተህ አትሸኘው” ብሎ ያስተማረው ምንኛ ግሩም ነው?
በሌላ ጊዜ ወደ ዐረብ ሀገር ሔደው ነበር፡፡ በጣዖታቱ ያደሩ አጋንንትም ፈርተው ሸሹ፡፡ ጣዖታቱ ተሰባበሩ፡፡ የዐረቡ ንጉሥም ይኽን ዐይቶ “አንተ ፀጉር ልብሱ ምንድነህ? ሰው ነህን?” አላቸው፡፡ ርሳቸውም፡- “አዎ! ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በኢየሱስ ክርስቶስ የማምን ሰው ነኝ” አሉት፡፡ ንጉሡም “አይሁድ ሰቅለው በገደሉት ሰው ታምናለህን?” አላቸው፡፡ “አፍርበት መስሎሃልን? አንተም ብታምንበት የዘለዓለም ሕይወት ባገኘህበት ነበር” ብለዉታል፡፡ “በወንጌል አላፍርም” እንዲል /ሮሜ.1፡16/፡፡ እንዲኽ ማለታቸው ነበር፡- “ርግጥ ነው በአፍአ ስታየው ጌታዬ በአይሁድ ተሰቅሏል፡፡ መሰቀል ብቻ ሳይኾን ሞቷል፡፡ መሞት ብቻ ሳይኾን ወደ ምድር ልብ ወርዷል፡፡ ነገር ግን የሞተው ስለበደሉ አይደለም፤ ስለ እኔና ስላንተ በደል እንጂ፡፡ የሞተው የእኔንና የአንተን ሞት ለመግደል ነበር፡፡ የተሰቀለው የኔንና የአንተን ኃጢአት በመሸከም ነበር፡፡ ወደ መቃብር የወረደው ርደተ ገሃነምን ያስቀርልን ዘንድ ነው፡፡ ሞት አገኘሁ ብሎ የሚታየውን ሥጋዉን ዋጠ፡፡ በማይታየውም ድል ተደረገ፡፡ ሞት አኹን ድል ተደርጓል፡፡ መቃብር ድል መንሣቱ ቀርቷል፡፡ አንተም ይኽን ብታምን ደግሞም ብትጠመቅ የዘለዓለምን ሕይወት ታገኛለህ፡፡” በእውነት የአባታችን በረከታቸው፣ ቃል ኪዳናቸው ከእኛ ጋር ትኹን፡፡

አባታችን እንዲኽ ለመስማት ዕፁብ ድንቅ በኾነ ግብር ቆይተው 262 ዓመት በኢትዮጵያ ኖረው፣ ስለ ኢትዮጵያ ጸልየው፣ በቃል ኪዳናቸው ያመነውን የተማፀነውን ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው መጋቢት 5 ቀን ለእሑድ አጥቢያ ቅዳሜ ማታ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲኾን በ562 ዓመታቸው ዐረፉ፡፡ መላእክትም በአክናፈ እሳት ኢየሩሳሌም ወስደው በየማነ ምሥዋዕ ቀብሯቸዋል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ” እንዳለን በምግባር በሃይማኖት አባቶቻችንን መስለን እንድንጸና የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የጻድቁ የአባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቃል ኪዳን ይርዳን አሜን!!!


Source : (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 03 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)



Thursday, March 10, 2016

መጋቢት 1


እነሆ የተባረከ የመጋቢት ወር ባተ ይህ ወር ልክ እንደ መስከረም ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው ከዚህ በኃላ ግን ቀኑ እየጨመረ ይሄዳል። መጋቢት ወር እጅግ ታላላቅ የጌታችን የማዳኑ ስራ የተከናወነበት ወር ነው፤ ዓለም የተፈጠረው በዚህ ወር በሃያ ዘጠነኛው ቀን ነው፤ ጌታችን ጽንሰቱም በዚሁ ቀን ነው። ሆሳህና 22 ስቅለቱ 27 ትንሳኤው 29 ነው ይህ ታዲያ ጥንተ በዓሉ ነው፤ በኃላ ዘመን የተነሳው ዲሜጥሮስ ስቅለት ከዓርብ ሆሳህና፤ ደብረ ዘይት፤ ትንሴኤና ጰራቅሊጦስ እሁድን እንዳይለቁ ቀመር ከሰራ ባህረሐሳብን ካዘጋጀ በኃላ ቀናቱ የሚለያዩ ቢሆንም ቅሉ ጥንተ በዓላቱ ታስበው ይውላሉ። ... የመጋቢት ወር ታላቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ያረፉበት ወር ነው። የዲሜጥሮስ ቀመር እንዳለ ሆኖ አባቶቻችን ሌላም ስርዓት ሰሩ በዓቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ የለምና የመጋቢት አቦን ለጥቅምት 5 የመጋቢት መድሐኒያለምን ለጥቅምት 27 እንዲሁም የመጋቢት ጽንሰቱን ለታህሳስ 22 ቀን አዙረው እንዲከበር አደረጉ፤ ዛሬ መጋቢት 1 ቀን በምድር ላይ ረጅም ዓመት የኖረው የሄኖክ ልጅ ማቱሳላ አረፈ፤ ዕድሜው 969 ነው ዘፍ 527 እርሱም ቢሆን አንድ ቀን አልኖረም 1000 ዓመት በጌታ ዘንድ አንድ ቀን ናትና፤ ስለዚህም በምድር ላይ አንድ ቀን የኖረ ሰው የለም አይኖርምም ምነዋ ቢባል፤ የጌታችን ቃል አይሻርምና "ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ" ዘፍ 217 ስለዚህም አንድ ቀን ሳይኖር ሰው ይሞታል ከአባቶቻችን በረከት ያሳትፈን። 

ቅዳሴ


ቅዳሴ በሥርዓተ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በኅብረት የሚጸለይ የኅብረት ጸሎት ነው፡፡ ከፀሎቶች ሁሉ የላቀ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ፭ቱ ምሥዋዕቶች ተሞልተው ይገኙበታል እዚህንም ፭ቱን መሥዋዕቶች ማንኛውም ክርስተያን ለፈጣሪው የሚያቀርበው ነው፡፡
፩. የቁርባን መስዋዕት፡- በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ውስጥ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋ መለኮት ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት የሚሆነው በቅዳሴው ፀሎት ነው ሳናስቀድስ አንቆርብምና የቁርባን መስዋዕት የሚፈጸመው በሥርዓተ ቅዳሴ ብቻ ነው፡፡ መስዋዕቱም በቤተልሔም ይዘጋጃል በቤተክርስቲያን ውስጥ በቤተ-መቅደስ ውስጥ ደግሞ ይቀርባል ወይም ይታደላል፡፡ ጌታችን ሲወለደ በቤተልሔም ተወልዶ ቀራንዮ ለዓለም ሁሉ መስዋዕት ሆኗልና ቀራንዮ በተባለች በቤተክርስቲያን ቅዱሱ መስዋዕት ለሕዝብ ይታደላል፡፡

፪. የከንፈር መስዋዕት፡- ካህኑ፣ ዲያቆኑና ሕዝቡ በመቀባበል በአንድነት ምስጋና ለፈጣሪያቸው የሚያቀርቡበት የከንፈራችን ፍሬ የሚሰዋበት የፀሎት ክፍል ፀሎተ ቅዳሴ ነው፡፡፫. የመብራት መስዋዕት፡- በቅዳሴ ጊዜ የሚበራው ጦፍ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የሚሰጥ የመብራት መስዋዕት ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው ይህውም ጌታችን ጨላመ ለሆነ ዓለም ብርሃን ሆኖ ብርሃንን ሊያበራ ወደ ዓለም መቷልና ነው፡፡

፬. የዕጣን መስዋዕት፡- የዕጣን ፀሎት ካህኑ ብቻ የሚያጥነው ሲሆን ይህውም በማዕጠንቱ አማካኝነት ቅዱሱን እጣን በመንበሩ፣ በቅዱሳን ስዕላቱ፣ በሕዝቡ መካከል ያጥናል ይህውም የሕዝቡን ፀሎት ወደላይ በደሥላሴ መንበር ይዞ ይወጣል በሰማይም ያሉ ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሥላሴን መንበር እንደሚያጥኑ ሁሉ በምድርም ያለው ካህን የሰማያዊው ምሳሌ ነውና በምድር ያውን መንበር በማጠን ለእግዚአብሔር የዕጣን መስዋዕት ያቀርባል፡፡

፭. የሰውነት መስዋዕትነት፡- በቅዳሴ ጊዜ አብዛኛውን ሰዓት ሙሉውን ማለት ይቻላል በመቆም የሚፀለይ የፀሎት ክፍል ነው፡፡ በመሐል 2 ጊዜያት ብቻ የስገዱ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ሕዝቡ ሁሉ ፊቱን ወደ ፈጣሪው አዞሮ እራሱን አዋርዶ ይሰግዳል በእግዚአብሔር ፊት መቆምም ሆነ መስገድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ የሰውነት መሥዋዕት ነው፡፡


ይህ የፀሎት ክፍል (ቅዳሴ) በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላ
፩. የዝግጅት ክፍል
፪. የንባብና የትምህርት ክፍል
፫. ፍሬ ቅዳሴ እዚህ ፍሬ ቅዳሴያት እንደየበዓሉ ይለዋወጣተሉ ብዛታቸውም ፲፬ ናቸው እነዚህም፡-

፫.፩. ሥርዓተ ቅዳሴ
፫.፪. ቅዳሴ ዘሐዋርያት
፫.፫. ቅዳሴ እግዚእ
፫.፬. ቅዳሴ ማርያም
፫.፭. ቅዳሴ ዘዮሐንስ ወልደ ነጓድጓድ
፫.፮. ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት
፫.፯. ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ
፫.፰. ቅዳሴ ባስልዮስ
፫.፱. ቅዳሴ ጎርጎርዮስ
፫.፲. ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ
፫.፲፩. ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
፫.፲፪. ቅዳሴ ዘቄርሎስ
፫.፲፫. ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
፫.፲፬. ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ


የጌታችን በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ እግዚእ)
የጌታችን ምጽአት፣ ጶጉሜ እሁድ ቀን ከዋለች ሰንበት … (ቅዳሴ አትናቴዎስ)
የእመቤታችን በዓል ከሆነ ቅዳሴ ማርያም … (ጎሳ ልብየ ቃለ ሰናየ)
የመላእክትና የሐዋርያት በዓል ከሆነ … (ቅዳሴ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ)
ከዘመነ ልደት እስከ ዘመነ ግዝረት … (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ካልዕ)
ቅዳሴን ለመቀደስ ብዙ ጊዜ ፭ሆነው ይቀድሳሉ ይህው የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሣሌ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከዚያም በሚያንስም ሆነ በሚበዛ ሰው ቅዳሴን መቀደስ ይቻላል ለምሳሌ ፯ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይመስላሉ ፲፫ በ12ቱ ሐዋርያት እና በጌታችን ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ፤ 24 በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ይህ የሚሆነው እንደ ካህናቱ ብዛት ነው ጭራሽ ካህን ከጠፋ ደግሞ 1 ቂስና 1 ዲያቆን ሆነው መቀደስ ይችላሉ ሁለትነታቸው የመለኮትና የትስብዕት (የሥጋ) ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ በሦስት ከሆነ በሦስቱ ሥላሴዎች አራት ከሆኑ በ4ቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ ከሁለት ባነሰ ግን 1 ሆኖ ግን ቅዳሴ አይቀደስም ቀኖናው የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ይከለክላል፡፡
“ጸልዩ” ይህ የቅዳሴው የፀሎት ዓይነት ሲሆን ለ13 ጊዜያት ይባላል፡፡ በሦስተኛው ክፍለ ቅዳሴ 4 ጊዜ ይባላል ፀልዩን ዲያቆኑ ሲያውጅ ፊቱን ወደ ህዝቡ ይመልስና እንዲጸልዩ ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜ ተሰጥዖ ካለ ተሰጥዖ ይመለሳል ከሌለ ግን “አቡነ ዘበሰማያት” ሕዝቡ እንዲደግሙ ያውጃል፡፡
ለምሳሌ፡-
ንፍቁ ዲያቆን “ፀልዩ በእንተ እለያበዕኡ መባዕ … መባን ስለሚያገቡ ሰዎች ፀልዩ” ሲል በዚህ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት አይደገምም ምክንያቱም የራሱ ተሰጥዖ ስላለው “ተወከፍ መባዖሙ ለአሃው ወተወከፍ መባዖን…” ይህ አቡነ ዘበሰማያት የሚተካ ፀሎት ነው፡፡
ድርገት ሲወርዱ “ፀልዩ በእንቲአነ” በሚባልበት ጊዜ እንድንጸልየው የሚያዘው የዳዊትን መዝሙር 150ኛውን መዝሙር ነው፡፡ ፀልዩ ብሎ ያዘዘው በዚህ ክፍል ያል የዳዊትን 150ኛውን የመዝሙር ክፍል ነው ማለት ነው፡፡
እኛ ክርስቲያኖች ቅዳሴን ባስቀደስን ቁጥር 1ኛ የኃጢአት ሥርየት ይገኛል ምክንያቱም በአንቃዕዶ ሕሊና ይቅርታን ስለሚጠይቅ፣ 2ኛ በነፍስም በስጋም በረከትን ያገኛል፣ 3ኛ ጸሎቱም ይደመጣል፣ 4ኛ የመላእክትን በረከት በቀጥታ እንሳተፋልን ቅዳሴን አስቀድሶ ሥጋ ወደሙ ሲቀበል የዘለዓለምን በረከት ያገኛል፡፡ በተጨማሪም ቅዳሴ በማስቀደስ 4 ነገሮች ይገኛሉ እነዚህም፡-

፩. ትምህርት
የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማ እና የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ትምህርት በቅዳሴ ገዚ ያገኛል፡፡ ለምሳሌ የማርያምን ቅዳሴ አባ ሕርያቆስ የደረሰውን ይህን ቅዳሴ ሲቀደስ በውስጡ ምሥጢረ ሥላሴ፣ እና ምሥጢረ ሥጋዊ እና ነገረ ማርያምን አምልቶ ይነግራል፡፡

፪. ታሪክ
14ቱንም ቅዳሴ የሚያስቀድስ ሰው የቤተክርስቲያንን ታሪክ በቅዳሴ ውስጥ እንማራለን፡፡

፫. ምክር
በቅዳሴ ውስጥ ተፋቀሩ፣ መጽውቱ፣ ተስማሙ፣ ጹሙ፣ ጸልዩ እየተባለ በቅዳሴ ውስጥ ሰፋ ባለመልኩ ምክር ይሰጣል ስለዚህ ቅዳሴን በማስቀደስ ምክርን ማግኝት ይቻላል ማለት ነው፡፡

፬. ተግሣጽ
ቅዳሴ ውስጡ ተግሣጽን ይዞ እናገኝዋለን ለምሳሌ በቅዳሴ እግዚእ ላይ ከወንድሙ ጋር የተጣለ ቢኖር ይተውለት ይላል በዚህ የቅዳሴ ክፍል ውስጥ ራሳችንን ምን ላይ እንደቆምን ከሰዎች ጋር ያለንን ኅብረት ስምምነት ለፈጣሪ ራሳችንን ማስገዛታችንን እየገሠፀ ይነግረናል፡፡ እነዚህን መሠረታዊ የሆኑትን ለሰው ልጆች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ቅዳሴ በማስቀደስ እናገኛቸዋለን፡፡
ቅዳሴ ንባብም ዜማም የሚቀርብበት የፀሎት ክፍል ነው፡፡ ሁላችንም የምንሳተፍበት ቄሴም ዲያቆኑም ምእመኑም የሚሳተፉበት ነው፡፡ “ኢትቁም እራቀከ ቅድመ ነቢየ እግዚአብሔር … በእግዚአብሔር ነብይ ፊት ራቁትህን አትቁም” ይህ ማለት በቅዳሴ ጊዜ ሰው ካለ መባ፣ ካለ እጅ መንሻ በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንደሌለበት ያጠይቃል፡፡ ምንም ባይኖረን እንኮ ያለንን አነሰ ብለን ሳንሳቀቅ ደግሞም ሳንንቃት ይዘን በፊቱ መቅረብ አለብን ከቻልን እጣኑን፣ ዘቢቡን፣ ጦፉን ሌላም ሌላሜ ይዘን መሄድ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ካህኑ በቅዳሴው መሃል ምዕናን ስለሚያስገቡት መባ የሚፀልየው ፀሎት አለ ምዕመኑም መባን ይዞ የማይመጣ ከሆነ ይህ ፀሎት ለማን ነው? ብሎ መጠየቅም ይገባል፡፡ ስለዚህ ቅዳሴን የምናስቀድሰው አስቀድመን ተዘጋጅተንበት መሆን አለበት፡፡ ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ጊዜ ባይኖረን ለቅዳሴ ግን ጊዜ መድበንለት ልናስቀድስ ይገባል፡፡ ቅዳሴ ለማስቀደስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ራሳችን 1ኛ ቆምን ለማስቀደስ 2ኛ የሚነበቡትን መጻሕፍቶች ከሕይወታችን ጋር እያዛመድን ለማዳመጥ ለመስራት 3ኛ ቅዱስ ቁርባን ለመውሰድ የዘለዓለም ሕይወትንም ለማግኝት አምኖ መምጣት አለበት በቅዳሴው የመግቢያ ክፍል ይህንኑ በዜማ “እስመጨረሻው ቅዳሴውን ያላስቀደስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲነበቡ ቆሞ ያላዳመጠ በመጨረሻም ቅዱስ ቁርባን ያልተቀበለ ከቤተክርስቲያን ኅብረት ልጅነት ይሰደድ” ይላል ስዚህ ራሱን አዘጋጅቶ መምጣት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ሰው ለቅዳሴ ሲቆም 5ቱን የሥሜት ሕዋሳቶቹን ሰብስቦ ወደ ቅዳሴው ትኩረት ሰጥቶ በንቃት ለቅዳሴ መቆም አለበት ለዚህም ዲያቆኑ በመሃል በመሃል “ለፀሎት ተነሱ” እያ ያውጃል ምዕመኑም ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አዋርዶ ይቅርታን በመጠየቅ “አቤቱ ይቅር በለን” ይላል፡፡ አምስቱ የስሜት ሕዋሳት የሚባሉት አይን፣ ጆሮ፣ አፍንጫ፣ እጅ እና ምላስ በአንድት በፀሎተ ቅዳሴ ጊዜ ያስቀድሳሉ ለምሳሌ፡-
ዐይን፡- ካህኑ ቅዳሴን ሲቀድስ በመንበሩ አጠገብ ቆሞ ብቻ አይደለም የተለያዩ ዓይነት እንቅስቃሴዎች አሉ እነዛን እንቅስሴዎች ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ መንፈሳዊ ምሥጢራዊ ትርጓሜዎች አሉዋቸው እነዚህን እንቅስቃሴዎች አይን ያያል ስለዚህ ዐይን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ጆሮ፡- ካህኑም ዲያቆኑም ምእመኑም በአንድትም ሆነ በተናጠል የሚያዜሙትን ዜማ፣ የሚያነቡትን ንባብ ይሰማል በዚህ ጊዜ ጆሮአችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
አፍንጫ፡- የዕጣኑን መዓዛ በማሽተት አፍንጫችን ያስቀድሳል
ምላስ፡- ቅዱስ ቁርባን በመውሰድ፣ የቅዳሴውን ፀበል በመጠጣት በዚህ ጊዜ የመቅመስ ስሜታችን ያስቀድሳል፡፡
የመዳሰስ፡-የመዳሰስ ስቀሜታችንም ስግዱ በተባለ ጊዜ፣ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ወንጌሉን ሲስም በመጨረሻም ሰዓት የካህኑን እጅ ለመባረክ ስንስም የመዳሰስ ስሜታችን ያስቀድሳል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አምስቱም የስሜት ሕዋሶቻችን በተሟላ መንገድ ከእግዚብሔር ጋር የሚገናኙበት መንገድ ምንድን ነው ቢባል ቅዳሴ ነው በቅዳሴ ውስጥ የምናገኘው ትምህርት በአውደምህረት በከኮርስ ከምናገኝው ትምህርት የተለየ ነው ይኽውም በዜማ የታሸ ብዙ ሊቃውንት የደከሙበት መንፈስ ቅዱስ እንደገለፀላቸው ለሰው በቀላሉ የሚገቡ ትምህርቶች ናቸው ሌላው ደግሞ ወንጌል ይነበባል መልዕክታት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ከዓለም አቀፍ ከሆኑ ሁሉ እና በዜማ ስለሆነ ነው እንጂ (ምስባክ) የምንለው ከመዝሙረ ዳዊትም ውስጥ ይነበባል ስለዚህ 1 ሰው ቅዳሴን ሲያስቀድስ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን ከብሉይ እስከ ሐዲስ ድረስ ይማራል ማለት ነው ረጅም ዘመን ያስቀደስ በሕይወቱ ውስጥ ምሁር ማለት እርሱ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንዳልነው ነው፡፡ የመላእክትን ህይወት በምድር ላይ መኖር ማለት ነው፡፡
በቤተክርስቲያናችን ትልቁ ሱታፊ ቅዳሴን ማስቀደስ ነው ይህንንም ከራስ አልፎ ወገኖቻችን ይህን ምሥጢር እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል ልጆቻችን ከቅዳሴው እንዲሳተፉ ተሰጥዖ እንዲመልሱ፣ መባን ይዘው እንዲመጡ፣ ቅዳሴ ለማስቀደስ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበሉ ማድረግ ተገቢ ነው ያለበለዚያ የምሰጠውን የምናጣበት ደረጃ ላይ እንዳንደርስ የቀደመውን ሥርዓተ አምልኮ የሚፈፀምበት ሥርዓት እንዳይጠፋ የሚረከበን እንዳናጣ የቀደመው ለተተኪው ትውልድ ሚስረከብ መቻል አለበት
ሰማያዊ ምሥጢር በምድረ ከተሰራባት ከማልእክት ጋር አንድ ሆነን ፈጣሪን ከምናመሰግንባት ከቅድስት ቤተክርስቲያን ሳያናውጥ ያኑረን አሜን፡

source : https://elianaaddis905.wordpress.com