Tuesday, December 5, 2017

ወበዛቲ ዕለት... ኅዳር ፳፮


እንኳን ለጻድቃን ቅዱሳን ኢየሱስ ሞዐ ወአቡነ ሃብተ ማርያም እና ለናግራን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
<3 ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ እንዲያነቡት ተጋሩት(share it) <3
በዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ

<3 አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ <3

እግዚአብሔር በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ባያስነሳ ኑሮ ምናልባትም ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በምናያት መንገድ ላናገኛት እንችል ነበር። እውነተኛ አባቶቻችን ፈጽሞ ከሚቆረቁራቸው ነገር አንዱ የጻድቅና ሐዋርያዊ አባት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መዘንጋት ነው።

እርሳቸው ፍሬ ሃይማኖት ሆነው ከጽድቅ ፍሬአቸው አዕላፍ ቅዱሳንን ወልደው ሃገራችን በወንጌል ትምህርትና በገዳማዊ ሕይወት እንድታሸበርቅ አድርገዋል። እስኪ በዕለተ ዕረፍታቸው ስለ ጻድቁ ጥቂት ነገሮችን እናንሳ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ የተወለዱት ጐንደር የድሮው ስማዳ (ዳኅና) አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው ዘክርስቶስና እግዚእ ክብራ ይባላሉ። የተወለዱት በ፲፪፻፲ ዓ/ም ነው። ነገር ግን አንዳንድ ምንጮች በ፲፩፻፺፮ ዓ/ም ያደርጉታል።

ጻድቁ ከክርስቲያን ወላጆቻቸው ጋር እንደሚገባ አድገዋል። በልጅነታቸው በብዛት ወላጆቻቸውን ያግዙ ነበር። በትርፍ ጊዜአቸው ደግሞ ትምሕርተ ሃይማኖትንና ሥርዓቱን ያጠኑ ነበር። በ፲፪፻፵ ዓ/ም ግን (ማለትም ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው) ይህቺን ዓለም ይተዋት ዘንድ አሰቡ።

አስበውም አልቀሩ ፈጣሪን እየለመኑ ደብረ ዳሕሞ ገቡ። በወቅቱ ዳሞ የትምህርትና የምናኔ ማዕከል ከመሆኑ ባሻገር የአቡነ አረጋዊ አምስተኛ የቆብ ልጅ ካልዕ ዮሐኒ ነበሩና የእርሳቸው ደቀ መዝሙር ሆኑ።

አቡነ ኢየሱስ ሞዐ በደብረ ዳሞ በነበራቸው ቆይታ ቀን ቀን ሲታዘዙ፣ ሲፈጩ፣ ውኃ ሲቀዱ ውለው ሌሊት እኩሉን በጸሎት በስግደትና የቀረውን ሰዓት ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ አሳለፉ።

በመጨረሻም ልብሰ ምንኩስናን ለበሱ። ይህን ጊዜ ሠላሳ ሰባት ዓመታቸው ሲሆን ዘመኑም ፲፪፻፵፯ ዓ/ም ነው። ወዲያውም በዳሞ ሳሉ መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ "ወደ ወሎ ሐይቅ ሒድ፤ ብዙ የምትሠራው አለና።" አላቸው።

በአንዴም ከዳሞ (ትግራይ) ነጥቆ ሐይቅ እስጢፋኖስ (ወሎ) አደረሳቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ መቅደስ በተጋድሎ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በማዕጠንትና ሐይቁ ውስጥ ሰጥሞ በመጸለይ ኖሩ።

ቅድስናቸውን የተመለከቱ አበውም በግድ አበ ምኔት አድርገው ሾሟቸው። ይህ ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ መሠረት የተጣለበት አጋጣሚ።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
ስም አጠራሯ የከፋ ዮዲት ጉዲት ለአርባ ዓመታት ሃገሪቱን እንዳልነበረች ብታደርጋት ክርስትና ተዳከመ፤ ባዕድ አምልኮም ነገሠ። አቡነ ኢየሱስ ሞዐ (ትርጉሙ ኢየሱስ ክርስቶስ አሸነፈ ማለት ነው።) ደግሞ ሃይማኖታቸው የቀና ከስምንት መቶ በላይ ክርስቲያኖችን ሰበሰቡ።

በሃገሪቱ ትልቅና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ቤተ መጻሕፍት አደራጁ። እነዚያን አርድእት በቅድስናና በትምህርት አብስለው አመነኮሱና "ሒዱ! ሃገሪቱን ታበሩ ዘንድ ተጋደሉ።" ብለው አሰናበቷቸው።

ከእነዚህ መካከልም ታላላቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን፣ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልን እና የኋላውን ፍሬ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን መጥቀስ እንችላለን። በዚህም ምክንያት ጻድቁ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን - አእላፍ ቅዱሳንን የወለደ" ሲባሉ ይኖራሉ።

ጻድቁ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን ንጉሥ አፄ ይኩኖ አምላክን በማስተማር ለሃገርና ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሰው አድርገዋል። በግላቸው ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ የብርሃን ምሰሶ ይወርድላቸው ነበር። ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምንም ከጠፋ ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ አቅንተዋል።

እንዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሲተጉ በተለይ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው አርባ አምስት ዓመታት ለዓይናቸው እንቅልፍን አላስመኙትም። ጐድናቸውም ከመኝታ ጋር ተገናኝቶ አያውቅም።
"እንዘ የኀሊ ዘበሰማያት ዐስቦ
መጠነ ዓመታት ሃምሳ ኢሰከበ በገቦ።" እንዲል።

ከዚህ በኋላ የሚያርፉበት ዕለት ቢደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። በተወለዱ በሰማንያ ሁለት ዓመታቸው (በሰማንያ ስድስት ዓመታቸው የሚልም አለ።) በ፲፪፻፹፪ ዓ/ም በዕለተ ሰንበት ዐርፈው ተቀብረዋል።
ጻድቁ ስም አጠራራቸው እጅግ የከበረ ነው!

<3 አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ <3

እኒህ ጻድቅ ደግሞ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው። "ጽድቅና ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው። ባሕር ከሆነ ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል።

ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን አባታቸው ፍሬ ቡሩክ እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና ትባላለች። በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ፣ ምጽዋትን ወዳጅ፣ ቡርክት ሴት ነበረች። እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር።

ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማኅጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ አለና ተመለሽ።" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች። ጻድቁን ወልዳ አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ ሰባት አክሊላትን ተቀብላ ዐርፋለች።

ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና ሕፃን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ። ይህችን ጸሎት በሕፃን አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?" እያሉ ይሰግዱ ነበር።

የአምስት ዓመት ሕፃን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት ይደንቃል። ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ። ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል። የፈጣሪውን ስም ያቃለለውን አንድ እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል።

ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ትምህርት ቤት ገብተው መጻሕፍትን አጥንተው መንነዋል። በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ ከመነኮሱ በኋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም።
ባሕር ውስጥ ሰጥመው አምስት መቶ ጊዜ ይሰግዳሉ።
በየቀኑ አራቱን ወንጌልና መቶ ሃምሳውን መዝሙረ ዳዊት ይጸልያሉ። (መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው።)
በአርባ ቀናት ቀጥሎም በሰማንያ ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ።
ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው።
በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ። (ካህን ናቸውና)
ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ፤ ክቡር ደሙን ይጠጣሉ።
በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን፣ መከፋትን አላሳደሩም።

በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር። ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በኋላም የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን አስከትሎ መጥቶ አላቸው።
"ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ፣
ስለ ምናኔህ፣
ስለ ተባረከ ምንኩስናህ፣
ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣
ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ፣
ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ፣
ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ ሰባት አክሊላትን እሰጥሃለሁ።"

"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን አምስት መቶ የእንቁ ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ። በስምህ የሚለምኑ፣ በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ! በርእስየ!' ብዬሃለሁ።" አላቸው።

ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ አቀፏቸው። ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ ታያቸውና አቅፎ ሦስት ጊዜ ሳማቸው። ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች፤ በዝማሬም ወሰዷት።

<3 የናግራን ሰማዕታት <3

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ናግራን (የአሁኗ የመን) የክርስቲያኖች ሃገር ነበረች። የሳባ ግዛትን የእኛ ነገሥታት ሲተዋት የተተካው ፊንሐስ ደግሞ ጨካኝ አይሁዳዊ ነበርና ናግራንን ሊያጠፋት ተመኘ። ቀጥሎም "ሃገራችሁን ልጐብኝ።" ብሎ በማታለል ገባ።

ወዲያውም ሕዝቡንና ካህናትን ሰብስቦ "ክርስቶስን ካዱ።" አላቸው። ጽኑ ክርስቲያኖች ግን "አይደረግም!" አሉት። እርሱም ሊያስፈራራቸው አስቦ አራት ሺህ ያህል ካህናት፣ ዲያቆናትና ምሑራንን ጨፈጨፋቸው።

ይህንን አድርጐ "አሁንሳ?" አላቸው። ሕዝቡ ግን አሁንም "ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም።" አሉት።
(ሮሜ. ፰፥፭)
ጨካኙ ፊንሐስም እንደ ገና ከሕዝቡ መካከል ከአራት ሺህ አንድ መቶ በላይ የሚሆኑትን ጨፈጨፈ።

ታላቁን ቅዱስ ሒሩትንም (የሕዝቡ መሪ ነው።) ብዙ አሰቃይቶ ሰየፈው። ሚስቱን ቅድስት ድማሕንም ሁለት ሴት ልጆቿን ሰይፈው የልጆቿን ደም አጠጧት፤ ከዚያም ሰየፏት። ይህንን የተመለከቱ የናግራን ክርስቲያኖች ግን ስለ መፍራት ፈንታ በፈቃዳቸው እየተሯሯጡ ወደ እሳትና ሰይፍ ተሽቀዳደሙ።

ከተማዋም እየነደደችና ደም እየፈሰሰባት ለአርባ ቀናት ቆየች። ይህንን የሰማው ቅዱሱ አፄ ካሌብም ደርሶ የተረፉትን ሲታደግ ፊንሐስን ከነ ወታደሮቹ አጥፍቶታል።

አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን፣ ክብራቸውን፣ ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን።

ኅዳር ፳፮ ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
፩.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
፪.አቡነ ሃብተ ማርያም ንጹሕ
፫.ቅድስት ዮስቴና ቡርክት
፬.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
፭.ቅዱስ ሒሩት አረጋዊ
፮.ቅዱሳን ቢላርያኖስ፣ ኪልቅያና ታቱስብያ (ሰማዕታት)
፯.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘደሴተ ሰንሲላ

ወርኀዊ በዓላት
፩.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
፪.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

"እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና።ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና። ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።.....
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል። አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው። በእርምጃውም አይሰናከልም።"
(መዝ ፴፮፥፳፰-፴፩)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

LIKE OUR PAGE >>>
https://www.facebook.com/pages/ተዋህዶ-ሀይማኖታችን/117298008428339?ref=hl

Tuesday, May 2, 2017

ዐሥራት በኩራት


Source: http://eotcssd.org/ethiopian-orthodox-tewahedo-church-sunday-schools-/62-writings/172-2011-10-11-13-26-38.html

https://www.youtube.com/watch?v=lFutCjXsXmg

Thursday, April 20, 2017

መላእክት ‹‹ያድናሉ››


ለመሆኑ መላእክት ማዳን ይችላሉ ማለት ስሕተት ነውን? ዛሬ ዛሬ ብዙዎች መናፍቃን መላእክትን ‹‹ያድናሉ›› ማለት እንደ ስሕተትና እንደ ክህደት ቆጥረውት ሲናገሩ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምን ሲባሉም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› በማለት ያለ አገባቡ ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም›› ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መላእክት አያድኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዕድሜ ይስጠን እንጂ ራሱን በቻለ ርእስ በሌላ ጊዜ በሰፊው እንመለስበታለን፡፡ ለዛሬ የመላእክትን ማዳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መረጃ እየጠቀስን እንመልከት፡፡

ቅዱስ ዳዊት በግልጥ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል›› ይላል፡፡ (መዝ33.7) ጥቅሱ ‹‹ያድናቸውማል›› ማለቱን ልብ በሉ፡፡ መላእክት የማያድኑ ቢሆኑ ኖሮ ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ ግልጥ አድርጎ ‹‹ያድናቸውማል›› ይል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ከመሰከረው እውነት የሚበልጥ ዕውቀት አለንን? እርሱ ‹‹ያድናሉ›› እያለ እኛ ‹‹አያድኑም›› ብንል ምን ማለታችን ነው? ይህ ጥቅስ ውሸት ነውን? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንታዘዘዋለን? እናምነዋለን? ወይስ ልናርመው እንወዳለን?

በሌላም የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባብ ውስጥ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ›› በማለት ያዕቆብ የልጅ ልጆቹን እንደባረከ እናነባለን፡፡ (ዘፍ48.16) በዚህ ጥቅስ ውስጥ መልአክ ‹‹ከክፉ ነገር ሁሉ›› እንደሚያድን በግልጽ ተጽፏል፡፡ መላእክት ‹‹ያድናሉ›› ላለማለት እነዚህን ግልጽ ቃላት መላእክት ይጠብቃሉ፤ ይራዳሉ፤ ያግዛሉ በማለት ማድበስበስ ይኖርብን ይሆን? ይህ ሁሉ ዝርዝሩ ሥራቸው ቢሆንም እንደሚድኑም ተጽፏልና ማመን ያስፈልጋል፡፡

በዚህ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ የተናገረውን ቃል እናቶችና አባቶች በስእለታቸው ‹‹ቅዱስ ሚካኤል አድነኝ፤ ቅዱስ ግብርኤል ድረስልኝ›› እያሉ በመድገማቸው የዋሃን ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማያውቁ ነው መባል አለባቸው? ቅዱስ ዳዊትና ቅዱስ ያዕቆብ የመላእክትን አዳኝነት በግልጽ ያወጁት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው ስላልተማሩ ይሆን? ወይስ አንድ ሰባኪ የመላእክትን አዳኝነት ስላስተማረ ‹‹ገድል ጠቃሽ›› በሚል መጥላላት አለበት? ዘማርያኑስ በዚህ መልኩ መዘመራቸው ሊያስወቅሳቸው ይገባ ነበር?

መላእክት የእግዚአብሔር ናቸው፡፡ የፈጠራቸው እርሱ ነው፡፡ የሚፈጽሙትም የእርሱን ፈቃድ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእርሱ መሆናቸውን በሚያሳይ አገላለጥ ‹‹መልአኩ፣ የጌታ መልአክ፣ መላእክቱ›› እያለ ይጠራቸዋል፡፡ ‹‹የጌታ መልአክ በሕልም ታየው›› እንዲል፡፡ (ማቴ1.20) መላእክት ሲያድኑ ፈጣሪ ሥራ አልሠራም ማለት አይደለም፡፡ መላእክት ያለ እርሱ ፈቃድ ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ሥራ እንዲሠሩ የሚፈቅድላቸውና የሚያዛቸው እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ የሠሩትን ይዘን ‹‹ፈጣሪ ይህን አደረገ ማለት እንችላለን›› እርሱ አዟቸውና ፈቅዶላቸው እስከሠሩት ድረስ እርሱ ሠራ ማለት ነውና፡፡ የሚቀጥሉት ሦስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች ይህን ሐሳብ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ለምሳሌ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ጅራፍ እንዲሠሩ አዘዛቸው፡፡ ራሱ ግን ጅራፍ አልሠራም፡፡ ቢሆንም ግን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደሠራ አድርጎ ‹‹የገመድ ጅራፍ አበጅቶ›› ይላል፡፡ (ዮሐ2.15) ዳግመኛም ኢየሱስ ክርስቶስ ማንንም አላጠመቀም ሐዋርያቱ ግን እንዲያጠምቁ አዟቸዋል፡፡ ያዘዛቸው እርሱ በመሆኑ ‹‹ያጠምቃል እጅግም ደቀመዛሙርት ያደርጋል›› የሚል ወሬ በፈሪሳውያን ዘንድ ተሰምቷል፡፡ ራሱ ግን ማንንም አላጠመቀም ነበር፡፡ (ዮሐ4.1-3) ሌላ ምሳሌ ለመጨመር እነ ሐና እና ቀያፋ ራሳቸው ኢየሱስ ክርስቶስን አልሰቀሉትም፡፡ ነገር ግን ተባባሪዎችና ትእዛዝ ሰጪዎች ስለነበሩ ቅዱስ ጴጥሮሰ ‹‹እናንተ በሰቀላችሁት›› ሲል ሰቃዮች መሆናቸውን ጠቅሶ ወቅሷቸዋል፡፡ (የሐዋ4.10)

በአንጻሩ ደግሞ ሥልጣኑ የፈጣሪ ነው ማለት መላእክት ‹‹ይህን ሠሩ›› አይባልም ማለት አይደለም፡፡ ፈጣሪ በመላእክት ሲሠራ መላእክትን እንደ ቁስ ቆጥሮ ይሠራባቸዋል ማለት አይደለም፡፡ መላእክት ሕያዋን ናቸው፡፡ የማዘንና የመደሰት ስሜት አላቸው፡፡ ባይሆን ኖሮ ንስሐ በሚገባ ኃጢአተኛ ደስ እንደሚላቸው አይጻፍም ነበር፡፡ ስለዚህ መላእክት ደስ እንደሚሰኙ ሁሉ ያዝናሉ ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ ሲያዛቸው በፈቃደኝነት ይታዘዛሉ፡፡ ፈጣሪ በእነርሱ ይሠራል ማለት ያለፈቃዳቸው ይልካቸዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ሰው ልጅ ነጻነት አላቸው፡፡ ቢሆንም በእርሱ ፈቃድ ደስ ስለሚላቸው ከፈቃዱ ፈቀቅ አይሉም፡፡ ነጻ ፈቃድ ባይኖራቸው ኖሮ ሰይጣን በደለኛ ሆኖ አይገኝም ነበር፡፡ የሰይጣን ወደ ገዛ ፈቃዱ ማዘንበል ለመላእክት የተሰጣቸውን ነጻነት ያሳያል፡፡ ታዲያ ሥራቸውን ወደው የሚሠሩ ሆነው ሳለ ፈጣሪ ልኮአቸው መላእክት ቢያድኑ ‹‹አላዳኑም›› እንዴት እንላለን? ለማዳን ፈቃደኛ ሆነው እስካዳኑ ድረስ ‹‹አድነዋል፣ ያድናሉ›› ማለት የሚገባ አይደለምን?

መላእክት እግዚአብሔር ስለፈቀደላቸው የሠሩትን ሥራ እነርሱ አልሠሩትም ካልን ሰይጣን የፈጸመውን የጥፋት ተግባር ማን ሠራው ልንል ነው? መቼም እግዚአብሔር ሳይፈቅድለት ሰይጣንም ቢሆን ያሰበውን ማከናወን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ ሰይጣን የሠራውን ፈቃጁ አካል እግዚአብሔር ስለሆነ ፈጣሪ ይህን አደረገ እንጂ ሰይጣን ይህን አልሠራውም እንላለንን? እንዲሁም ፈቃጁና አዛዡ ምንም ፈጣሪ ቢሆን ቅዱሳን መላእክት የሠሩትን እንደሠሩት ማመንና መመስከር ይገባል፡፡ ለክፉ ሥራው ሰይጣን ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም ለሥራቸው ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ቂርቆስንና ኢየሉጣን ስላዳነ ‹‹ቅዱስ ገበርኤል አዳናቸው!›› የሚገባ ነው፡፡

በቅዱሳን መላእክት ማዳንና ተራዳኢነት ውስጥ የእግዚአብሔር ሥልጣንና አዛዥነት በረቂቅ አለበት፡፡ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን በምንም መንገድ ቢሠራ በዛ ውስጥ የእርሱ ሥልጣንና ሥራ የማይጠረጠር ነው፡፡ መላእክት ያለ ፈጣሪ ትእዛዝና ፈቃድ አንዳች ሊሠሩ አይችሉም፡፡ ፈጣሪ ግን ያለ መላእክት አጋዥነት የፈለገውን የሚሠራ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ፈጣሪ ይህን ሠራ ስንል መላእክትን ላይጨምር ይችላል፡፡ መላእክት ይህን አደረጉ ስንል ግን በምንም ተአምር ከፈጣሪ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ መናፍቃን ‹‹ጌታ፣ እግዚአብሔር ይህን አደረገ›› ብቻ እንድንል የሚፈልጉት ቅዱሳንን ላለማስገባት ነው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ቅዱሳን መላእክትንና ቅዱሳን ሰዎችን ይህን አደረጉ የምንለው እግዚአብሔርን ከማመን ጋር ስለ ቅዱሳን ክብር ለመመስከር ነው፡፡

እሳት በባሕርይው የሚፋጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንጨትና ብረት ግን ብቻቸውን ሳሉ ቢነኳቸው አያቃጥሉም፡፡ ነገር ግን ከእሳት ጋር ከተዋሐዱ /ከጋሉ/ በኋላ ቢነኳቸው ይፋጃሉ፡፡  እሳት የተዋሐደው ብረት የማያቃጥልበት ምንም ሁኔታ የለም፡፡ ካላቃጠለ ወይ እሳት አልተዋሐደውም ወይም ደግሞ እሳቱ ራሱ አያቃጥልም ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር በባሕርይው አዳኝ ነው፡፡ መላእክት አያድኑም ካልን ወይ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር አይደለም ማለት ነው ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ አያድንም እንደማለት ይቆጠርብናል፡፡ ስለዚህ ‹‹መላእክት ያድናሉ›› ስንል የሚያድን እግዚአብሔር ከእነርሱ እንደማይለይ እየመሰከርን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

 More about sile melaket


የእግዚአብሔር ቸርነት
የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አይለየን!

ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ሌሎቹን ጽሑፎች ለማንበብ ከፈለጉ በዚህ ሊንክ http://www.facebook.com/hibrety?sk=notesይፈልጓቸው!